የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር “ከአሜሪካ ይልቅ ዴንማርክን እንመርጣለን” ሲሉ ለትራምፕ ምላሽ ሰጡ ።
የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጄንስ-ፍሬድሪክ ኒልሰን ሀገራቸው ከአሜሪካ እና ከዴንማርክ አንዱን እንድትመርጥ ቢገደዱ “አሁንም ዴንማርክን እንመርጣለን” ሲሉ በይፋ አስታወቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኒልሰን ከዴንማርክ አቻቸው ሜት ፍሬደሪክሰን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ግሪንላንድ በአሜሪካ የመገዛት ወይም የመታቀፍ ፍላጎት እንደሌላት በግልጽ ተናግረዋል። “እኛ የምንመርጠው የዴንማርክን ግዛት፣ ኔቶን እና የአውሮፓ ህብረትን ነው” ብለዋል።
የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜት ፍሬደሪክሰን በበኩላቸው አሜሪካ በግሪንላንድ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የምታስበው ከሆነ “ይህ የኔቶ እና የአትላንቲክ የመከላከያ ጥምረት ማብቂያ ይሆናል” ሲሉ ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ከአሜሪካ ጋር ለመቀላቀል ያላቸውን እቅድ በድጋሚ ያነሱ ሲሆን፣ ደሴቷን ከሩሲያ እና ከቻይና ተፅዕኖ ለመከላከል አሜሪካ “ባለቤት መሆን አለባት” የሚል አቋም ይዘዋል። ዋይት ሃውስ ደሴቷን ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም አስፈላጊ ከሆነ ግን “ወታደራዊ ኃይል” እንደሚጠቀም ማስታወቁ አይዘነጋም።
ዘገባው የሮይተርስ ነው
