‹‹ከኮቪድ በላይ ዘርፉን የጎዳው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ነው›› አንድነት ፈለቀ

Date:

አንድነት ፈለቀ

(የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዝዳት)

በቅርቡ ፓን አፍሪካ ም/ቤት እና የኢትዮጵያ ንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡ ዘርፉ ባለፉት አምስት ዓመታት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እንደማለፉ መጠን ከሰላም እና ደህንነት ጀምሮ እስከ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች ድረስ መልስ የሚያሻቸው አያሌ ጉዳዮች አሉበት፡፡ በችግሮቹና በመፍትሔው ዙርያ ከወ/ሮ አንድነት ፈለቀ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ እነኾ!   

በመጀመሪያ ራስሽን ለአንባቢያን ቢያስተዋውቁልን?

አንድነት፡- አንድነት ፈለቀ እባለለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ፕሬዝዳት ነኝ፡፡

ከኮቪድ 19 እና በሀገራችን ከተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ የቱሪዝም ዘርፉ ምን ሂደት ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል?

አንድነት፡- ኮቪድ 19 ከመግባቱ በፊት የሀገራችን የቱሪዝም እድገት ትልቅ ደረጃ የደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ በጣም ትልቅ ተስፋ የታየበት ወቅት ነበር፡፡ ኮቪድ በመከሠቱ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ዘርፉ ተቀዛቀዘ፡፡ ከኮቪድ በኋላ ለጥቂት ጊዜያት ማገገም ጀምሮ ነበር፡፡ ኾኖም ጦርነቱ ሲጀመር መልሶ ተዳከመ፡፡ ከኮቪድ በላይ ዘርፉን የጎዳው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ራሳቸውን ከሥራው አግለለዋል፡፡ ግማሾቹ ሥራ ቀይረዋል ፤ ሌሎቹ ደግሞ እስከወዲኛው ዘግተውታል፡፡ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ቱሪዝሙ ተስፋ ሰጪ ነገር ታይቶበት ነበር፡፡ በቅርቡ በተሳተፍንባቸው ክንውኖችም አስጎብኝዎች ከመንግሥት ጋር ተስማምተናል፡፡ ኾኖም ሁኔታው ‹‹ለቱሪዝም ክፍት ነው፡፡ ሰላም ነው፤ ኑ›› ብለን ብዙም ሳይቆይ ዳግም የሰላም እጦት ተከሰተ፡፡ በዚህም ምክንያት የውጪ ወኪሎች ጎብኝዎችን ለመላክ አሁን ያለው ሁኔታ መተማመን አሳጥቷቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከኮቪድ ወዲህ ያለው ሁኔታ ይህን ይመስላል፡፡ ዘርፉም ቀድሞ ከነበረው ደረጃ እጅግ ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡

የአስጎብኚ ተቋማት ከሰላም እጦቱ ባሻገር ያሉባቸው ተግዳሮቶችስ እንዴት ይገለጻሉ?

አንድነት፡- ከፍ ሲል የገለጽኩት ከሰላምና ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ዘርፉ ያጋጠመውን አደጋ የተመለከተ ነው፡፡ ነገር ግን ከኮቪድ በፊት በዘርፉ ዙሪያ ብዙ ያልተፈቱ ቢሮክራሲያዊ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ በዘርፉ ያሉ ተቋማት ኃይላቸውን አንጠፍጥፈው እንዳይሰሩ ማነቆ የኾኑባቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ አስተዳድራዊ ሂደትን የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዲስተካከሉ በርካታ ጊዜ ጠይቀን ነበር፡፡ ለምሳሌ በኮቪድ ጊዜ በዘርፉ ለሚሠሩ ተቋማት እርዳታ ያስፈልግ ነበር፡፡ የተሠጠው ድጋፍ አናሳ በመኾኑ በርካታ የዘርፉ ተቋማት ከሥራው ሊወጡ ችለዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍና ችግሩ የሚፈልገው የድጋፍ መጠን ሊጣጣም አልቻለም ነበር፡፡ ዘርፉ እንዳላገገመ ቢታወቅም ለተቋማቱ የሚደረገው የብድር አገልግሎት ግን ሊራዘም አልቻለም፡፡

መንግሥት አሁን ላይ ቱሪዝም ወሣኝ የኢኮኖሚው አለኝታ እንዲኾን ፍላጎት እንዳለው ሲናገር ይደመጣል፡፡ ከዚህ አንጻር ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል ማለት ይቻላል?

አንድነት፡- አሁን ላይ መንግሥት በመርኅ ደረጃ ዘርፉን ለማገዝ እየጣረ ይገኛል፡፡ እኔ በዚህ ዘርፍ 17 ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ እንደአሁኑ በመንግሥት ደረጃ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ አያውቅም፡፡ በተጨባጭም አንዳንድ የተስተካከሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ዘርፉ እራሱን ችሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ለብቻው ተቋቁሟል፡፡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችም እየተሠሩ ነው፡፡ አሁን የምናየው ችግኝ ተከላውም ለዘርፉ አጋዥ ኃይል ነው፡፡ ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተስፋ የሚሠጡ ቢኾኑም የሚፈለገውን ዓይነት ለውጥ አላመጡም፡፡ መንግሥት ቢያንስ ዘርፉን ከማኅበራዊ ጉዳይ ወደ ኢኮኖሚያዊ ዋልታነት ማምጣቱ በራሱ ለውጥ ቢኾንም አሁንም ብዙ መሠራት የሚገባው ነገር አለ፡፡ ለዘርፉ ከፍ ያለ ትኩረት በመንግሥት ደረጃ ሲሰጠው ለአስጎብኚ ድርጅቶችም ለሌሎችም ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ነገር ግን ለአስጎብኚ ድርጅቶች አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ወይ ሲባል ገና ብዙ ይቀራል፡፡

ምሣሌ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?

አንድነት፡- ለምሳሌ የተስተካከለ የታክስ አዋጅ የለንም፡፡ ራሱን የቻለ የኢንቨስትመንት ሕግ የለንም፡፡ የቱሪዝም ማስፈፀሚያ ደንብና ሕጎች አላወጡልንም፡፡ የገበያ ስትራቴጂ በቅንጅት የምንሠራበት መንገድ አልተቀመጠልንም፡፡ በአጠቃላይ በርከት ያሉ ችግሮችን አሳልፈናል፡፡ በነገራችን ላይ ከለውጡ በፊት የነበሩ የሰላም እጦቶችም በዘርፉ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በተለያየ ጊዜ ችግሮች ይገጥሙናል፡፡ ችግሮቹ እንዳይመጡ የምንከላከልበት፣ ከመጡ በኋላም የምናስተካክልበት ሂደት አልነበረም፡፡ እኛን በትልቁ የሚጎዳን ሚዲያ ላይ የሚወጣ ነገር ነው፡፡ እነዚህን ዐይነት ችግሮችን ለማስተካከልና ለማረም የሚያገለግል የማኔጅመንት አሠራር ደግሞ አልዘረጋንም፡፡ ቱሪዝሙን ለመገደፍ የተለየ የኢንቨስትመንት ሕግ አልወጣም፡፡ ስለዚህ መሬት ላይ አጥጋቢ እገዛ የለም ማለት ይቻላል ፤ ያለው ተስፋ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያሏት መስህቦችን ለዓለም ከማስተዋወቅ አንፃር ያለባትን ክፍተት እንዴት ትገልጪዋለሽ?

አንድነት፡- የፈለገ መስብህ ቢኖር ትልቁ ነገር ማስተዋወቅ ነው፡፡ መስብህን አስተዋውቆ በሚመጣው ቱሪዝም መጠቀም ካልተቻለ መስብህ መኖሩ ጥቅም የለውም፡፡ ለማስተዋወቅ ደግሞ ብዙ የሚያስፈልጉህ ነገሮች አሉ፡፡ የሁሉም ዓይነት ኃይል ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያ ምንድነው ያለህ? በየትኛው ገበያ እናውጣው? መቼ እናውጣው? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብም የሰውም ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ቅንጅት የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይኾን ያለንን መስህብም ለጎብኚ በሚመጥን መልኩ ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲባል ከመሠረተ ልማት አንፃር፣ ከአገልግሎት አሠጣጥ አንጻር፣ ከደህንነት አንፃር ተገቢ የኾነ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የእኛ ሀገር መስህቦች በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንድ ቱሪስት አዲስ አበባ መጥቶ ከአንድ ቀን በላይ ሊያድር ይችላል፡፡

ስለዚህ በክልል የሚገኙ የዘርፉ አካላት ሁሉ ለዚህ ዝግጁ መኾን አለባቸው፡፡ ይሄን እቅድ ውስጥ አስገብቶ መሥራት ይገባል፡፡ ቅርሶቹንም በአግባቡ መጠበቅ ያሻል፡፡ የጎብኚውንም ስሜት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ማስታወቂያ ሲሠራም በተጋጋሚ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ ቱሪስት አንዴ ብቻ መጥቶ የሚቆም ሳይኾን በተጋጋሚ የሚመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ማስታወቂያ እንደመስህቦቹ ዐይነት በተለያየ መልኩ በየጊዜው መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከማስተዋወቅም ባለፈ በጀት ይፈልጋል፡፡ በዘርፉ የተሠማሩት ጎረቤት ሀገራት ብዙ ገንዘብ ለቱሪዝም አፍስሰዋል፡፡ በእኛ ሀገርም ከዚህ ትምህርት ወስዶ ዘርፉን በበጀትም ማጠናከር ይገባል፡፡ አቅም ያለው ገበያ ኾኖ ሳለ የሚያፈልገውን ገቢ እንዲያመጣ አላደረግንም፡፡ ስለዚህ ትልቅ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ተሠማርቷል ማለት ይቻላል?

አንድነት፡- በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማሰማራትም አንጻር ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ሴክተሩን ከሚያስተዳድረው ተቋም ጀምሮ አስጎብኚዎች፣ የአገር ውስጥ አስጎብኚዎች፣ ሌሎችም ጋር አጠቃላይ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመሠማራቱ በቱሪዝማችን ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ መስሕቡን ወደ ገንዘብ ለመቀየር በመጀመሪያ ዕውቀት ይፈለጋል፡፡ መስህቡን ለመጠቀምም እንዲሁ ግንዛቤ ይፈለጋል፡፡ ሆቴሎች አስጎብኚዎች ልዩ ልዩ የዘርፉ አገልግሎት ሰጪዎች ስለዘርፉ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ በዚህ ደረጃ የበቃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማሰልጠኛ ተቋማት አሉን ወይ? የሚለውን ከተገዳዳሪ ጎረቤቶቻችን ጋር ማወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ያን ስናይ ያለንበት ደረጃ በጣም ዝቅ ያለ መኾኑን እንረዳለን፡፡

በዘርፉ እንደ ከፍተት የሚታዩ እና ቢስተካከሉ የሚሏቸው ሌሎች ችግሮች ካሉ?

አንድነት፡- ቱሪዝም ለሀገር የሚጠቅም የኢኮኖሚ ዋልታ ተደርጎ ሲታሠብ የሚወጡ ሕጎች በተቻለ መጠን የቱሪዝም ዘርፉን ደጋፊ ወይም የማያደናቅፉ መኾን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣ የሚወጡ ሕጎች የቱሪዝም ሴክተሩን ምን ያህል ይፈትኑታል የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ አዋጁ የሚወጣው ሀገር አደጋ ላይ ስትኾን ለዜጎች ደህንነት ተብሎ እንደኾነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የሚወጡ ሕጎች የሀገርን ገፅታን በማያበላሽ መልኩ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ቱሪዝም በአንድ ሴክተር ብቻ የሚሠራ ዘርፍ አይደለም፡፡ የሁሉንም ትብብር የሚሻ ነው፡፡ የኢሚግሬሽን፣ የደህንነት፣ የፖሊስ፣ የግብርና ወዘተ ሁሉ ቅንጅትን የሚፈልግ ነው፡፡ አንዳንድ ነገር መቀየር ሲፈለግ ሌላውን ዘርፍ ምን ይነካብኛል ብሎ መታሰብ አለበት፡፡

ለምሳሌ የቪዛ መግቢያ ዋጋ 50 ዶላር የነበረው አሁን ላይ 82 ዶላር ተደርጓል፡፡ ይኼ በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላትን በማማከር የተደረገ አይደለም፡፡ ይህ ሲደረግ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ምን ያመጣል የሚለው አልታሰበም፡፡ ስለዚህ አንዱና ዋናው ነገር የቱሪዝም ዘርፉ ከሁሉም ጋር የሚገናኝ ስለኾነ የሚወጡ ሕጎች ዘርፉን ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ይህን ዘርፍ የሚያሳድገው የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ ለአስጎብኚ ተቋማት አስቸኳይ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ቢሮክራሲውን ማቅለልና መፈተሸ ይገባል፡፡ አንዱ ትልቁ ዘርፉ ያለበት ችግር በመዳረሻ ቦታዎች ላይ ልማት አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ አቅም ያላቸው ሰዎች እዚህ ውስጥ ገብተው እንዲያለሙ የተለየ ማበረታቻ ማድረግ ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚያለማና ክልል ሄዶ የሚያለማ ሰው የሚያገኘው ዋጋ እኩል ከኾነ አልሚውን ሊያነሳሳው አይችልም፡፡ ስለዚህ በተለይ ክፍተት ያለባቸው ቦታዎችን ለማልማት የተለየ መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ አሁን ያለንበት ጊዜ ጥሩ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል የነበረብን የረሃብ ሥዕል ጨርሶ የጠፋ አይደለም፡፡ ይኼን በወጉ ሳናስተካክል ጦርነት ተከስቷል፡፡ አንዱን ጦርነት ሳንጨርስ ሌላ ጦርነት ይከተለናል፡፡ ይህን ችግር ተቋቁሞ የቆየውን ቱሪዝም በተለመደው መንገድ ተጉዘን ስኬታማ ልናደርገው አንችልም፡፡ ስለዚህ ሰፊ ቅስቀሳ፣ በጀት እና መሰል ነገሮች ይፈልጋል፡፡ የዘርፉ ተቋማት ደስ ብሏቸው እንዲሠሩ አሁን ያሉት ነገሮች መቀየር ይገባቸዋል፡፡ በተለይ የታክስ ሕግና የመሳሰሉ ጉዳዮች በደንብ መታየት ይኖርባቸዋል፡፡ በእርግጥ ስለታክስ ማውራት የሚቻለው ገቢ ሲኖር ነው፡፡ ገቢው እንዲመጣ ደግሞ ከፍ ሲል እንዳነሳሁት በደንብ መሥራት ይገባል፡፡ ስለዚህ ጥቃቅን የኾኑ ችግሮች ቢስተካከሉ ጥሩ ነው፡፡ ችግሩን የሚመጥን እቅድ በመንደፍ ከነማስፈፀሚያ መንገዱ መተግበር ቢቻል መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...