ከዓባይ አድማስ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን ሴራ በሙስጠፋ ሓሚድ ዩሱፍ

Date:

ክፍል አንድ

የሕዳሴ ግድብ ከግንባታው ጅማሮ አንስቶ በርካታ ተቃውሞዎች ከግብጽ በኩል በርካታ ተቃውሞዎችን አስተናግዷል፡፡ የግድቡ መገንባት የእያንዳንዱን የግብጽ ሕዝብ ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል ተደርጎ በግብጽ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች እንዲሁም በተለያዩ የዐረብ የመገናኛ ብዙኃን በእጅጉ ተዘግቧል፡፡ ግድቡን አስመልክቶ ቀዳሚ ተቃዋሚ የሆነች ግብጽም ከግንባታው ጀምሮ የምታሳያቸው አቋሞችና የምትሰጣቸው አስተያየቶች ከጊዜ ወደጊዜ የተለያዩ ናቸው፡፡ በግድቡ ዙሪያ የግብጽ መንግሥት፣ የአል-አዝሀር ዩኒቨርሲቲ፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ሲቪል ተቋማት፣ የማሕበራዊ ገጾች የሚያወጣቸው መግለጫዎችና ከግብጽ የመገናኛ ብዙኃን በኩል የሚሰራጩ መረጃዎችም እንዲሁ ለየቅል ናቸው፡፡ በተለይ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ከፕሬዚዳንት ሒስኒ ሙባረክ የመንግሥት ሥርዓት ጀምሮ በዐረቡ አብዮት በሕዝብ ነጻ ምርጫ የርዕሰ-ብሔሩን መንበር ይዘው ለአንድ ዓመት ከጥቂት ወራት ብቻ ግብጽን ከመሩት ሟቹ ዶ/ር ሙሐመድ ሙርሲ እንዲሁም በመንፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን እስከያዘው ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል-ሲሲ ድረስ የዓባይ ወንዝን እና ኢትዮጵያን አስመልክተው የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች፣ ጽሑፎች፣ ታሪኮች፣ ዜናዎች እንደየፕሬዚዳንቱ አቋም የተለያዩ ናቸው፡፡

እንደየመገናኛ ብዙኃን ተቋምነታቸው እነዚህ ተቋማት በዓባይ፣ በሕዳሴ ግድቡና በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚነሱ ሃሳቦችንና አስተያየቶችን በመገናኛ ብዙኃን  ተቋም የፍትህ ሚዛን ላይ በማስቀመት ለማንም ያልወገነ ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዝባቸው እና ለሌላው የዓለማችን ሕዝብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንጻሩ እነዚህ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃዎችን ከማድረስ ይልቅ ዐረባዊ ዘረኝነትን በመስፋፋት፣ ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ በማሳደር  አፍሪካዊነትን በማጠልሸት እና የመንግስታቸውን መግለጫና አቋም በማሰራጨት ላይ ተጠምደዋል፡፡

የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  ከሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ጀምሮ በግንባታው ላይ በርካታ አመለካከቶችንና የተጋነኑ ምስሎችን ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ከእነዚህ በርካታ አመለካከቶችና የተጋነኑ ምስሎች መካከል የተወሰኑትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

አንደኛ፡- የጦርነት ነጋሪት መምታት

የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  ከሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ጀምሮ የግብጽ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በሕዳሴ ግድቡ ላይ የሃይል እርምጃ እንዲወስድ በርካታ ጥሪዎች አድርገዋል፡፡ የአሁኑ የግብጽ ፕሬዚዳነት ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል-ሲሲ ሟቹን ዶ/ር ሙሐመድ ሙርሲን በመፈንቅለ-መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ የርዕሰ-ብሔሩን ሥልጣን ተቆናጠው ከአንድ አመት በኋላ እሳቸው ብቻ ብቸኛ የምርጫ ተወዳደሪ በነበሩት ሐገራዊ ምርጫ የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ላይ የዓለም አቀፍ እውቅና አግኝነተው ከተደላደሉ በኋላ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር በመግባባትና በመወያየት ለመፍታት ሃሳብና ፍላጎት አሳይተው ነበር፡፡ ነገርግን ይህን የፕሬዚዳንት አል-ሲሲን ፍላጉት በመቃወም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሳይጠናከር በፊት የግብጽ መንግሥት በወታደራዊ ሃይል ከወዲሁ እርምጃ በመውሰድ በአጭሩ እንዲያስቀረው የሚል ጥሪ በተለያዩ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  በኩል ጥሪ ቀረበ፡፡  የግብጽ መገናኛ ብዙኃን  የሐገሪቱ ፕሬዚዳነትን ፍላጎት ተቃውሞንና የወታደራዊ ሃይል እርምጃ የግብጽ ፓርላማ አባለትም ጭምር ይደግፉት፣ ባገኙት አጋጣሚም ያሰራጩት ጀመር፡፡ በፕሬዚዳንቱ ላይ ከተነሳው ተቃውሞ ይልቅ በሕዳሴ ግደቡ ላይ የግብጽ መንግሥት ወታደራዊ የሃይል እርምጃ ይውሰድ፣ ግድቡን እስከወዲኛው ለመደምሰስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የግብጽ የመከላከያ ሃይል ይኑረው የሚሉትን ሃሳቦች የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  ያሰራጩ ጀመር፡፡ ከዚህም አልፈው ዓለም ላይ የተሻሉ ናቸው የሚባሉ ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን ለሕዝባቸው ያሳዩ ነበር፡፡ እነዚሁ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  ፕሬዚዳነት አል-ሲሲ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለመግዛት ከተለያዩ ሐገራት ጋር የሚፈራረሟቸው ስምምነቶች የሕዳሴ ግድብን ለመደምሰስ እንዲሆን የሚገዟቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንደሆኑ አድርገው ዘገባዋል፡፡

እንደዚህ አይነቱን የመገናኛ ብዙኃን  ተቋማት ዘገባንና እንቅስቃሴን በተመለከተ ግብጽ ውስጥ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን  መካከል አንዱ በሆነው የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚቀርበው “ወራአ-ልአህዳስ” /Beyond the Events/ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፎ ነበር፡፡

“ይህ አይነቱ የሃይል እርምጃ ይወሰድ አገላለጽ በሐገር ውስጥና በሐገር ውስጥ ደረጃ ብቻ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ በፕሬዚዳነት ሙርሲ ዘመን አንዳንድ የተቃዋሚ ሃይሎች የመገናኛ ብዙኃን  በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ የሃይል እርምጃ ይወሰድ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ሌሎች ደግሞ ሙርሲ ፈጣን የሆነ ወታደራዊ የሃይል እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ አለመውሰዳቸውን የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደማይፈልጉ አድርገው በማሳየት ይህንንም እንደድክመት ለሕዝብ በመግለጽ በፕሬዚዳን ሙሐመድ ሙርሲ መንግሥት ላይ ተቃዋሚዎችን ያደራጃሉ፡፡  በአል-ሲሲ መንግሰት መጀመሪ ላይ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  በአብዛኛው አል-ሲሲ መንግሰት ፖለቲካዊ አካሄድ ጋር በመጣጣማቸው በሕዳሴ ግድቡ ላይ ወታደራዊ የሃይል እርምጃ ይወሰደበት በማለት ሕዝብንነና መንግሥትና ለጦርነት ከማነሳሳት ይልቅ በየእለቱ የሕዳሴ ግደቡ ስለሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችና የአፍሪካ ሐገራት በየራሳቸው ተፈጥሯዊ ሃብቶች የመጠቀም ነጻነት መዘገብና ለንባብ ማብቃት ጀመሩ፡፡

በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል እንደአውሮፓዊኑ ዘመን አቆጣጠር ፌብሩዋሪ 2015 ላይ በግድቡ ዙሪያ ከተከሰተው አለመግባባት በኋላ ደግሞ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን  ፊታቸውን ከፕሬዚዳንት አል-ሲሲ ወደየአል-ሲሲ ተቃዋሚዎች ወደሙስሊም ወንድሞቻቾች ፓርቲና ስልጣናቸውን በመንፈቅለ-መንግሥት ላጡት ዶ/ር ሙሐመድ መርሲ ደጋፊዎች አዞሩ፡፡ በተቃራኒ  ዶ/ር ሙሐመድ መርሲ ላይ ይዘገቡት የነበረውን የግብጽን ፍላጎትና ደህንነት አለመጠበቅ ፍላጉት በአል-ሲሲ ላይም መዘገብና ይህንኑ ለአል-ሲሲ መንግሥት ድክመት አድርገው ለሕዝብ አሰራጩ፡፡ ይልቁንም ዶ/ር ሙሐመድ ሙርሲ “ለዓባይ ወንዝ የሚከፈለው ገንዘብ ሳይሆን ደም ነው የሚከፈለው” በማለት በአንድ ወቅት የተናገሩትን እንደየሐገር ጀግና አነጋገር ደጋግሚው ያወሱት ጀመር፡፡” (Beyond the Events, 14 December 2015)

የሚገርመው እነዚህ ለየመንግታቶቻቸው አቋም የሚያደሉ፣ የመንግስታቶቻቸው አቋም ከእነሱ አቋምና ፍላጎት ጋር ሲቃረን የሚቀለበሱ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  የሕዳሴ ግድቡን በወታደራዊ ሃይል ለመደምሰስ መንግታቶቻቸውንና ሕዝባቸውን ሲቀሰቅሱ አንድ ያላጤኑት ነገር ከሕዳሴው ግድብ መደምሰስ በኋላ በግብጽ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኢትዮጵያ ምላሽ፣ በአሕጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖር የሚችለውን ተጽእኖ እንዲሁም በግብጽ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች መመናመንና መቋረጥን ብቻ ሳይሆን የግብጽ የመከላከያ ሃይል የቱን ያህል ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ቢታጠቅ የሕዳሴ ግድቡን በመደምሰስ ሄደት ሽንፈትን ሊከናነብ እንደሚችል ነው፡፡

ኹለተኛ፡- የቀኝ አገዛዝ ሥርዓትን መናፈቅ

ግብጽ በአውሮፓውያኑ የቀን አገዛዝ ዘመን አፍሪካ ላይ የነበራትን የበላይነት ለመመለስና ግብጽ ዳግም በቀጠናው የሃይል ባለቤት መሆኗን ለማሳየት የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን  የግብጽ መንግሥት በኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ላይ ወታደራዊ የሃይል እርምጃ እንዲወስድ መወትወታቸውን አልተውም፡፡ የግብጽ ሕዝብ ግደቡን ለማፍረስና ኢትዮያጵያን ለመውጋት እንዲነሳሳ ዘውትር የግብጽ ቀደምት መሪዎች የነበሩት የእነ ሙሐመድ ዓሊ ባሻን፣ የኸደዊ ኢስማዒልን (ካዲፍ ኢስማኤልን)፣ የጀማል አብዱናስርን፣ የአንዋር ሳዳትንና የሑስኒ ሙባረክን ገድል በአርአያነት   ይጠቅሳሉ፡፡ 

የግብጽ ቀደምት የሥነ-ጽሑፍ ውጤቶች እንደሌሎች የአፍሪካ ሐገራት የአውሮፓዊኑን የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት አጠልሽተው ሳይሆን አሞግሰውና አወድሰው ነበር የተጻፉት፡፡ በተለይ ከሙሐመድ ዓሊ ባሻ የመንግሥት ሥርዓት ጀምሮ ያሉት የቅኝ ግዛቱ ሥርዓት ፍቅር ያነሆለላቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት የቅኝ አገዛዝ ሥርዓቱ የተፋፈሱን ሐገራት ጥቅምና ፍላጎት ግምት ውስጥ ሳያስገባ ለግብጽ የዓባይን ወንዝ ዋስትና አረጋጋጭ በመሆኑ ነው፡፡ አሁን ዘመንና ቴክኖሎጂ በሰለጠነበት ዘመንም ቢሆን ግብጽ የዓባይን ውሃ ለብቻዋ ለመጠቀም የሱዳን ሉአላዊት ሐገርነትን በመሰረዝ የራሷ አንድ አካል ለማድረግ ፍላጎት አላት፡፡ ለዚህ ግብጽ ከሱዳን ላይ በወታደራዊ ሃይል የወሰደቸው የሐለብ መሬት እንደምሳሌ የሚቀርብ ነው፡፡ አሁን ላይ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን  የሕዳሴ ግድብን ጉዳይ ሲዘግቡ ሱዳን የግብጽ አንድ አካል ነበረች የሚለው የቅኝ አገዛዝ ታሪካቸውን ከመጥቀስ ወደኋላ ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ ከግብጽ መገናኛ ብዙኃን  ከዚህ በመነሳት ሕዝባቸውን በኋላ የጠለሸ የአውሮፓዊያን ቅኝ አገዛዝ ታረክ የግብጽን ቅዱስነትና የበላይነት እየሰበኩ በሕዳሴ ግድብ ላይ ለመቀስቀስ ሽንጣቸውን ገትር ሌት ተቀን ቢሰሩም በአብዛኛው የግብጽ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኙም፡፡ እነዚህ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን  ቀደምት መሪዎቻቸው የዓባይ ወንዝ ላይ በኢትዮጵያ በከል ምንም አይነት ግድብ እንዳይሰራ የኢትዮጵያ መንግሥታት አንዳስጠነቀቁና እንዳስፈራሩ ዘውትር ይዘግባሉ፡፡ ሲላቸውም በራሳቸው ያልተከሰተ የማይታወቅ የቅርብ ጊዜ ታሪክን በመፍጠር የግብጽን የበላይነት ለሕዝባቸው ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የግብጹ መሪ አንዋር ሳዳት ኢትዮጵያ ግድብ ልትገነባ እንደሆነ በመስማታቸው እውነት እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥትን ይጠይቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሰት ወሬው ሐሰት እንደሆነ ቢያረጋግጥላቸውም እሳቸው የኢትዮያጵያን መንግሥት ባለማመናቸው ከደቡብ ሱዳን ስድስት የጦር ጀቶችን ወደኢትዮጵያ በመላክ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ግድቦች እንዲወድሙ ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡ በሰጡት ትእዛዝም የጦር ጄቶቹ ወደጀቶቹ ኢትዮጵያ ሲደርሱ አንድም የተገነባ ግድብ እንደሌለ ያረጋግጡና ይህንኑ ለፕሬዚዳነቱ ያሳው ቃሉ፡፡ እሳቸውም በሃይላቸው እንደኮሩና በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ድል እንደተቀዳጁ እንደተሰማቸው ዘግበዋል፡፡  ይሁን እንጂ ያ ሁሉ የግብጽ መንግሥታት ፉከራ ከንቱ ሆኖ የሕዳሴው ግድብ ግብባታ በዓባይ ወንዝ መፍለቂያ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተገንብቷል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከባድ ሙስና የተከሰሱትን 4 ተከሳሾችን፤ ፖሊስ ፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይችል ቀረ

በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በፖሊስ የ'ይፈለጋሉ" ማስታወቂያ የወጣባቸው...

ስለመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ውጥረት እስካሁን የታወቁ ጉዳዮች

🔸 ትላንት ምሽት ከኢራን ግዛት የተተኮሰ የሮኬት ጥቃት በሰሜናዊ...

የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕጉ በጋዜጣ እስኪታተም ረቂቅ ሰነዶችን ከመጠቀም እንዲቆጠብ የፍትሕ ሚኒስቴር አሳሰበ

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የፍትሕ ሚኒስቴር አዲሱ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ...

ፔንታጎን የእስራኤል ስለላ እንደሚያሳስበው ተገለጸ

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ፔንታጎን እስራኤል ከፍተኛ ልዑኮችን ጨምሮ የአሜሪካ...