117 ሰዎችን ጭኖ ከሊቢያ በመነሳት አውሮፓ ለመድረስ የሞከረ መርከብ ከሰጠመ በኋላ 116 ሰዎች ሲሞቱ በህይወት የተረፈው አንዱ ብቻ ነው።
አደጋው ባለፈው ሳምንት ማጋጠሙ የተዘገበ ሲሆን በህይወት የተረፈው ግለሰብ ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተነግሯል።
በህይወት የተረፈው ግለሰብ የተገኘው አደጋው ከደረሰ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው ሲባል ያገኙት በእንጨት በተሰራ ጀልባ አሳ የሚያጠምዱ ቱኒዛውያን ናቸው።
መርከቧ ከሊቢያ ተነስታ ጥቂት እንደተጓዘች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት መልዕክት ብትልክም በሳተላይትም በአየር ፍለጋም ልትገኝ አልቻለችም።
በህይወት የተረፈው ግለሰብ ከሊቢያ ጥቂት እንደተጓዙ መጥፎ የአየር ንብረት መፈጠሩን ገልጿል።
በወቅቱ በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር የሚነፍስ ነፋስ ነበር ሲባል አደጋውም በዚህ ምክንያት እንደደረሰ ታምኗል።
ዘገባው የዴይሊ ኤክስፕረስ ነው።
