👉የ45 ዓመቷ መነኩሴ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ተመረቁ
ኩዊንስ ኮሌጅ በ2018 ዓ.ም. በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,219 ተማሪዎች በ26ኛው ዙር የምርቃት ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በድህረ-ምረቃ፣ በቅድመ-ምረቃ እና በቴክኒክና ሙያ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፣ በማኔጅመንት፣ በማርኬቲንግና ሴልስ ማኔጅመንት፣ በሂዩማን ሪሶርስ ማኔጅመንት፣ በሴክሬታሪና ኦፊስ አድሚኒስትሬሽን እንዲሁም በሃርድዌርና ኔትዎርኪንግ የሙያ መስኮች የተማሩ ናቸው።
የኮሌጁ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ሞገስ ግርማ በምርቃቱ ላይ በሰጡት መልዕክት፣ ተመራቂዎች በሕይወት ጉዟቸው እውነተኛ ስኬትና ደስታ ለማግኘት የሕይወትን ጥበብና ራስን መግራት እንዲይዙ አሳስበዋል።
ዶ/ር ሞገስ የውስጥ ጥሪንና ሐሳብን መረዳት፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ቅንነትና እውነተኛ ፍቅርን መያዝ፣ የሀገርን ሕግ ማክበር እንዲሁም የማህበረሰብ እሴቶችን መጠበቅ ከተመራቂዎች የሚጠበቁ መሠረታዊ እሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምርቃቱ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ በበኩላቸው፣ ምርቃት የትምህርት መጨረሻ ሳይሆን የቀጣይ የእውቀት ጉዞ መጀመሪያ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ትምህርት የሚቀጥል እንጂ የሚያልቅ አይደለም” ያሉት ሲስተር ዘቢደር፣ ተመራቂዎች በፈጠራና በእውቀት በሀገርና በዓለም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ አዳዲስ ሀሳቦችንና መፍትሔዎችን እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የ45 ዓመቷ መነኩሴ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ተመረቁ
ከ4,219 ተመራቂዎች መካከል የ45 ዓመቷ እማሆይ ዘውዴ ማናለ የምርቃቱ ልዩ ታሪክ ሆነዋል።
እማሆይ ዘውዴ በደብረ አባይ ቅድስት አርሴማ ገዳም እየኖሩና እያገለገሉ በኩዊንስ ኮሌጅ የምሽት ትምህርት በመከታተል በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ተመርቀዋል።
እማሆይ ዘውዴ የ9ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ካቋረጡ በኋላ ለ25 ዓመታት ከትምህርት ርቀው ቢቆዩም፣ በኋላ ወደ ትምህርት ተመልሰው እስከ 12ኛ ክፍል በመማር የኮሌጅ ትምህርታቸውንም ቀጥለዋል።
በገዳሙ ውስጥ የሂሳብ ሥራዎችን የሚያከናውኑት እማሆይ ዘውዴ፣ በአካውንቲንግ ያገኙት ትምህርት የሙያ እውቀታቸውን ለማዳበርና በገዳሙ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ለማጠናከር እንደሚጠቅማቸው ገልጸዋል።
“ትምህርት ዕድሜ አይገድበውም” ያሉት እማሆይ ዘውዴ፣ ሌሎችም ተስፋ ሳይቆርጡ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኩዊንስ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርትና የሙያ መስኮች ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ዘንድሮ 26ኛ የምርቃት ዙሩን አከናውኗል።
