ክቡር ሰርፀ ፍሬስብሀት ከሰኔ 25፣ 2017ዓ.ም ጀምሮ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ይፋዊ ትውውቅ አድርገዋል፡፡
ክብርት ሸዊት ሻንካ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ለክቡር ሰርፀ ፍሬስብሀት በተዘጋጀው እንኳን ደህና መጡ መርሃ ግብር ላይ ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ሴክተሩ በመምጣታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀው ወደ ሴክተሩ ከመምጣታቸው በፊት ለባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ሲያደርጉት የነበረው ሙያዊ ድጋፍ የላቀ ነበር በማለት አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም በትብብር መንፈስ የተሻለ ስራ በመስራት መንግስትና ህዝብ የጣለብንን አደራ በትጋት መወጣት ይገባናል ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩም በበኩላቸው ስለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው የተመደብኩበት ተቋም በነሲልቪያ ፓንክረስትና ተክለጻድቅ መኩሪያ የተመራ እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ማንነትና መገለጫ የያዘ ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ ስራ ይፈልጋል ሲሉ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በትጋት እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡
አቀባበሉ ላይ የተገኙ አመራሮችም ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ሴክተሩ በምጣታቸው ደስታቸውን ገልጸው በሙያቸው ሁሉንም ዘርፎች እንዲያግዙ በብዝሀ ታታሪነት መርህ ለሴክተሩ አቅም እንዲሆኑ አንስተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
