ክፍሌ አቦቸር እና ‹‹ይህ ነው ምኞቴ…››

Date:

ሠሎሞን ለማ ገመቹ


ግዮን መጽሔት :- ሻለቃ ከፍሌ አቦቸር ስለ እናት ሃገር ኢትዮጵያ ፍቅር… ሲባል በጥላሁን ገሠሠና በሌሎች ድምፃዊያን በተናጠልም ይሁን በሕብረት ለተዜሙ ብሔራዊ መዝሙሮች፣ ሌሎች ትውልድን የሚያስተምሩና ባለተስፋ ማድረግ የሚችሉ ዘፈኖች ግጥሞችን ከፃፉ ስመ-መልካም የብዕር ሰዎች አንደኛው ነው፡፡


ሻለቃ ክፍሌ እጅግ ታዋቂ ከሆነባቸው ሥራዎቹ መካከል፤ በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይሁን የእናት ሃገር ሠራዊት በፍቅር ይዘምራቸው የነበሩት ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› እና ‹‹የአንድነቱ…›› የተሰኙት የብዕሩ በረከቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ለነዚያ ግጥሞች መከተብም ይሁን ዜማ ተቀምሮላቸው ከአድማስ አድማስ… የሚያስተጋቡ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድነት ያሰለፉ… መዝሙሮች እንዲሆኑ ምክንያት ከሆኑት ቁልፍ ጉዳዮች መካከልም ሊጠቀስ የሚችለው፤ በቀጣዮቹ የዚህ ጽሑፍ አንቀጾች ሊገለጹ የተፈለጉት ጉዳዮች ናቸው፡፡


የአሥራ ዘጠኝ ስልሳ ስድስት አብዮታዊ ወይም መንግሥትን የሻረ ሕዝባዊ ወሃገራዊ ለውጥን ተከትሎ እናት ኢትዮጵያን ከመጥበሻው ወደ እሳቱ ከገፈተራት ከባድና መላወሻ የሌለው ችግር አንደኛው፤ በሰይድ ባሬ የሚመራው የሶማሌያ መንግሥት በሃገራችን ላይ የሰነዘረው መጠነ-ሰፊ ወረራ ነው፡፡


በዚያ ዕብሪት የተመላበት የግዛት ማስፋፋት ወረራ በወቅቱ (ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት) የነበረውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ከአፍ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የሶማሊያ አጥቂ ሠራዊት፤ በምሥራቅ በኩል 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ ገብቶ ነበር፡፡

በዚያም ብቻ ሳይገደብ ወራሪው የሶማሊያ ጦር፤ በሐረርጌ እስከ ከምቦልቻና ሒርና፣ በሲዳሞና በባሌ መስመር ወደ ሻሸመኔና አካባቢው በመገስገስ እስከ ናዝሬት… ያሉትን የሃገራችንን መሬቶች በሙሉ በኃይል ጠቅልሎ የመቆጣጠር ፍላጎቱንም አሳይቷል፡፡


ያን የመሰለውን የወረራ ጥቃትና የግዛት ማስፋፋት የጀብደኝነት ድርጊት… ለመቀልበስ ሲባል በ1968/69 እንዲሁም በ1970 ዓመተ ምሕረት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሕዝብና ሠራዊት በአንድነት በመሰለፍ! ከፍተኛና በደማቅ ድል የታጀበ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ የሶማሌያን ከዕብሪት የመነጨ ዕብጠት በማስተንፈስም!…. በቆሬ፣ በፈዲስ፣ በሐረር ኮምቦልቻ ወዘተ. ግንባሮች የወራሪውን አከርካሪ በመሰባበር!…. በጅጅጋ የካራማራ ተራራ ላይ ተቆናጦ የነበረውን የሰይድ ባሬን ጦር ሙሉ በሙሉ ደምስሶ፤ የማይቀለበሰው ድል ባለቤት የሆነበትን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት የአንድነት፣ የአይበገሬነት፣ የነፃነትና የክብር… ሁነኛ መለያ የሆነውን ባንዲራ በካራማራ ተራራ አናት ላይ ሕዝባዊ ሠራዊቱ (ሚሊሺያው) አውለብልቧል፡፡

በማውለብለቡም ያ የካራማራ አንፀባራቂ ድል እንደ ዓድዋው ድል ሁሉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የውጭ ወራሪዎችን  እና ተስፋፊዎችን የማሳፈርና ልካቸውን የማሳየት… ድል ሆኖ ባለፉት 47 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥም ይሁን በአደባባይ ሲከበር ኖሯል፡፡


ለዚያ ድል መገኘት ግን በየጦር ግንባሩ በተጨባጭ ከተከፈለው መስዋዕትነት ባሻገር በኪነ-ጥበቡ፣ በቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳው፣ የእናት ሃገር ፍቅርን በዜጎች አዕምሮ ውስጥ በማስረጹ… የማንቃትና የማደራጀት ዘርፍ እጅግ በጣም ወደር-የለሽና አስደማሚ የሆኑ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዚህም ታላቅና ፍሬያማ የሆኑ ተግባራት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ፣ ለሕዝባዊ መዝሙሮች ግብዓት መሆን የቻሉትን እጅግ አስደናቂ ግጥሞችን በመፃፍ የበኩሉን ወርቃማ አስተዋጽዖ ያበረከወተው ኢትዮጵያዊ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ነው፡፡   


እኔ 48ኛው የካራማራ ድል በዓል በተመለከተ በተካሄደው፤ ለውዲቱ ኢትዮጵያ የሕይወትና የአካል ብሎም የሞራል መስዋዕትነት የከፈሉ፤ ሕይወት፣ አካላቸውን ያጡ… ጀግኖች በታሰቡበት፤ በዓለም አቀፍ ወንድማማችነት መርህ ከኢትዮጵያውያን ጎን በቁርጠኝነት የተሰለፉና የተሰየፉ! የኩባ፣ የሶቭየት ሕብረት፣ የደቡብ የመን ዜጎች ጭምር ውለታቸው በተመሰከረበት ሥነ-ሥርዓት፡-


‹‹ይህ ነው ምኞቴ፤ እኔ በሕይወቴ!
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ…›› የሚለውን እና
‹‹የአንድነቱ! ድሉ እንዲሰምር የነፃነቱ!


  ወጣ ወረደ፣ ሄደ ነጎደ ሠራዊቱ›› የሚሉ ዜማዎችን በወታደራዊ የማርች ባንድ አባላት አማካይነት አደመጥኩ፡፡ ዜማዎቹንም ከነ ግሩም ድንቅ… ትዝታዎቻቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎችም ያንን ዜማ ከነ ግጥሞቹ በስልት ሲወርዱትና ሲወጡት ሰማሁ፣ ተመለከትኩ፡፡ ከዚያም በመነሳት ይህን ጽሑፍ ለመክተብ ተነሳሁ፡፡ በቅድሚያም የ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› ዜማ ይዘት ከሚናኛቸው መልዕክቶች መካከል አንደኛውን የስንኝ አንጓ እንደሚከተለው አስቀደምኩ፡-


‹‹ወንዝ ጅረቱ – ብርዱ ሐሩሩ
ዳገት ኮረብታው ጉራንጉሩ!
አያግደኝም ይህ ከጉዞዬ፤
ጥምና ረሃብ – እኔን ከዓላማዬ!
ተከብሮ እንዲኖር ዙሪያ ድንበሬ፤
የሞት ሞት ልሙት እኔ ለሃገሬ!››


ታዲያ የዚህን ግጥም ባለቤት የሚያውቁት፣ የሚቀርቡት፣ አብረውትም አቀበት ቁልቁለቱን፣ ጋራ ሸንተረሩን… የወጡትና የወረዱት፣ በአያሌ ድካም… ጭምር ያቋረጡት ጓዶቹ፡- ‹‹ይህ ነው ምኞቴ! እኔ በሕይወቴ…›› የሚለው የእናት ሃገር ኢትዮጵያ የብሔራዊ አንድነትና ቁርጠኝነት፣ ተስፋና ምኞት ዜማ … በአደባባይም ይሁን በየትኛውም ሥፍራና አጋጣሚ ሲዜም፣ ጎላ ብሎም ሲደመጥ፤ ቀድሞ ከነ ተክለ-ሰውነቱ የሚከሰትላቸው ስም ቢኖር፤ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር የሚለው ነው፡፡


የይህ ነው ምኞቴ መዝሙር ግጥም ደራሲ ወይም ዋንኛ ጸሐፊ የሆነው ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር፤ አሰላሳይና ጥንቁቅ ወታደር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነፍስ በደሙ ቀን ከሌት የምትላወስ፤ ሃገሬን! ወገኖቼን ባይ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እሱ… ክፍሌ ኦቦቸር ባለማተብ የታሪክ ሰውም ነው፡፡

ከምንም በላይ ሰውነትን ያስቀደመ፣ ከዜግነትም ኢትዮጵያዊነትን በሕሊናው ያገዘፈ የኢትዮጵያ ውድ ልጅ ነው፡፡ ለኪነ-ጥበብ ባለ አደራ ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣ፣ የሥነ-ግጥም፣ የሥነ-ጽሑፍ ድንቅ ባለሙያም ነው፡፡


ባለሙያነቱ ጥርት ብሎ የሚታየው፣ ተውቦና ከፍ ከፍ ብሎ የሚገኘው፤ በኢትዮጵያዊነቱ ተብሰልስሎት፣ በሰውነቱ ልዩ ጥሞና ውስጥ ሆኖ ብዕሩን በሚያነሳባቸው ሰዓታት ነው፡፡ ለዚህ አባባል ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆኑትም ‹‹አንድ ቀን፣ የእኔ ጋሻ፣ ምስጢሯን ያልገለጠልን›› የተሰኙት የግጥም መድብል መጽሐፎቹ ብቻ አይደሉም፡፡

በርግጥ በመጽሐፎቹ ውስጥ በተሰደሩት ውብና ባለ ግሩም መዓዛ… ሃገር፣ ሃገር፤ ሰው፣ ሰው፤ ታማኝነትና ኢትዮጵያዊ ቀናኢነትን የሚወክሉ፣ የሚገልጹና በጥልቁም የሚያስተነትኑ የብዕሩ በረከቶች የክፍሌ አካላዊ ሳይሆን ውስጣዊ ማንነቱና ምንነቱ እንደ ታላቅ የብርሃን ዐምድ በጉልህ ይታያል፡፡ ነገር ግን የክፍሌን ማንነትና የሥራዎቹን የእናት ሃገር ፍቅር ድምፅነት… ከፍ ሲል በተገለጹት መጽሐፎች ውስጥ በተሰደሩት ሥነ-ግጥሞቹ ይዘት መዝኖ ወይም በይኖ ወይም ደግሞ ፈርዶ ብቻ ማለፍ አይቻልም፡፡


ለምን?… ክፍሌ ከዚያም ባሻገር ኢትዮጵያዊ ንፁህና ረቂቅ ስብዕናውን የሚገልጹ ወይም የሚወክሉ ሥራዎችን ያከናወነ ወታደር! የሥነ-ጥበብ ጥንቁቅ ባለሙያ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ክብርና ማንነት፣ ዕምነት ጽናት፣ ታሪክና ብሩህ ተስፋ ተሟጋችና ተከላካይ ዜጋ ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ የሃገር፣ የወገን፣ የዕውነት፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ክብርና ነፃነት፣ ፍቅርና አንድነት፣ ቆራጥነትና ጀግንነት ልሳን መሆኑንም፤ እንደ ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› እና እንደ ‹‹የአንድነቱ…››

ያሉና ብሔራዊ ድምፅ መሆን በቻሉ ሥራዎቹ ያስመሰከረ፣ የእሱንና የተከታዩን ብቻ ሳይሆን የአዲሱንም ትውልድ ወኔ (ሞራል) በኢትዮጵያዊነት ድንቅ ስሜት ያነፀ የሃገር ባለውለታ ነው – ክፍሌ፡፡  


የሃገሩ ሕመም ዘወትር፤ ያውም ቀን ከሌት የሚያመው፣ ወገኖቹ ያለ አንዳች ልዩነት የእናት ሃገር ኢትዮጵያን አንድነት! ነፃነትና ሉዓላዊነት፣ ዳር-ድንበር… ለማስከበር ሲሉ በአራቱም ማዕዘናት የከፈሉት ይህ ቀረሽ የማይባል መስዋዕትነት በየሰዓቱና በየደቂቃው የሚያብሰለስለው፣ የሚከነክነው… ክፍሌ አቦቸር፤ እንደ፡- ‹‹ለሃገሬ ስዋደቅ ለድንበሯ፤ ተኝቼአለሁ እኔ ካፈሯ፤ ስለ ድል ታሪኬ ስታወሱ፤ ቤተሰቦቼን ግን እንዳትረሱ፡፡ ለሃገሬ ነፃነት ይሟገታል አፅሜ፣ ከመራራው ትግል ከጀግኖች ደም ጀርባ….›› የሚሉትንና ሌሎችንም ግጥሞች በታላቅ ወገናዊና ሃገራዊ ተመስጦ… ጽፎ፤ ታላቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ እንዲጫወታቸው ያደረገ ነው፡፡


ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› ብሎም ‹‹የአንድነቱ…›› የተሰኙትን ግጥሞች ሲጽፍና እነዚያም ግጥሞች እንደ ‹‹ተነሳ ተራመድ›› ሁሉ ዘመንን አልፈውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሻግረው ጭምር ባለ ታላቅ ብሔራዊ ግርማና ሞገስ ባለቤት መሆን የቻሉበት ዜማ ተስማምቶላቸው… ወደ ኢትዮጵያውያን ጆሮ ሲደርሱ፤ በኢትዮጵያ ግዛት ከአድማስ አድማስ ሲናኙ…፤ የነበረው ሁናቴ እጅግ በጣም የተለየ ነበር፡፡ 
እነ ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› ተጽፈው፣ በዜማ ተውበውና፣ በሙዚቃ ልሂቃን ተቀምረው… በብሔራዊ ደረጃ የእናት ሃገር ፍቅር ዜማ፣ የሃገር ልጆች የቁርጠኝነታቸውና የአይበገሬነታቸው መለያ ኃያል ድምፅ ሆነው በኢትዮጵያ ምድርና ሰማይ ላይ ሲሰሙ… በአጠቃላይ ሃገራዊ  ሁናቴው፣ ብሔራዊ ድባቡ፣ የነበረው ጭንቅና ጥብ፣ የሕዝቡ ቁጣና ተነሳሽነት፣ የአብዮታዊ  ስሜቱ ግለትና ትኩሳት፣  የሶማሊያ መንግሥትና ሠራዊት ዕብሪትና ትምክህት፤ በጀብደኝነት ባበጠው! በንቀትና በጥላቻ ሰክሮ የግፍ ድርጊቶችን ሁሉ በመፈፀም ወደ ድሬዳዋ፣ ሐረር ከተሞችና ወደ ሌሎችም አነስተኛ የገጠር መዲናዎቻችን በመገስገስ ላይ የነበረው የወራሪው የሰይድ ባሬ ሠራዊት፣ የሰርጎ ገብ ኃይሎቹና በአጠቃላይ ኢሕአፓን ጨምሮ እንደ እስላሚያ ኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ዓይነት የጸረ-ኢትዮጵያ አንድነት ቡድኖች የአጥፊነት፣ የከፋፋይነት፣ የበራዥነትና የከላሽነት… ብሎም በውክልና ተቀባይነታቸው የአፍራሽነት ሚናቸውን የመወጣታቸው ተግባር በሙሉ፤ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና የግዛትም ይሁን የዜጎቿ አንድነት የማይሰክን የቀናዒነት ስሜትም ይሁን የማይላላ ጽኑ አቋም ያላቸውን ልዩና አስተዋይ ልጆቿን ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከራሱ በፊት የሃገሩን ሕልውና… እንዲያስቀድም የየራሱ መንፈስ ራሱን እንዲያዘው የሚያስገድድበት ወቅት ነበር፡፡


ስለነበርም የክፍሌ አቦቸር ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› እና ‹‹የአንድነቱ›› እንደሌሎች የሃገርና የወገን መውድድ ግጥምና ዜማዎች ሁሉ፤ ታላቅ ምልዓትና ብሔራዊ ጉልበት ብሎም የወኔ መቀስቀሻ ምትሃታዊ ንዝረት ነበራቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ወንድማማችነት መንፈስ የመናውያን፣ ኩባውያን፣ ሩሲያውያንና ሌሎችም ከኢትዮጵያ ወድ ልጆች አጠገብ ተሰልፈው የተሰየፉበት… ሃገርን ከወረራ፣ ከቅሚያና ከዝርፊያ፣ ከአጠቃላይ ውርደትና ጥፋት፣ ከውድመትና ከሁለንተናዊ ባርነት፣ ሞትና ስቃይ…. የመታደግ… ወሰን-አልባ ተጋድሎ የተደረገበት ትግል ንፁሕና ብርሃናማ መስታወት የሆነው የካራ ማራ ድል… ሲታወስ፡-…


የሻለቃ ክፍሌ አቦቸር ንፁሕ ብሔራዊ ቃል የተቀመረበት የጽናት፣ የቁርጠኝነት፣ የጀግንነት ዝግጁነትና የማይደበዝዝ የሃገራዊ ዓርበኝነት መንፈስ መግለጫ የወል ቋንቋ በመሆኑ… ወደ ብሔራዊ ዜማነት መለወጥ የቻለው የ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› መዝሙር ግጥም፤ ታላቅ አክብሮት የሚቸረው ይሆናል፡፡ በዚህ መመዘኛ ረገድም ይሁን በሌሎች የሃገር ባለውለታነት መስፈርቶች ሲታዩ፤ ክፍሌ አቦቸርም ይሁን ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› የተሰኘው ውብና ግሩም የሃገር ባለውለታ ልጆች… መዝሙር፤ መቼም ይሁን መቼ በኢትዮጵያዊነት የተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ወርቃማ ሥፍራ የሚኖራቸው ናቸው፡፡


ይልቁንም ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› ከኢትዮጵያ ሃገራችንም አልፎ አህጉራዊ የነፃነት ተጋድሎን በተመከተም አንድ ዓይነተኛ ሚና የነበረውም ነው፡፡ ለምሣሌ ያህል የዝምባቡዌ ነፃ አውጪ ሠራዊት አባላት በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጠናቸውን ጨርሰው ወደ ሐራሬ ለመጓዝ ዝግጅት ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ይህንኑ ባለ ግርማ ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› የተሰኘውን መዝሙር ‹‹ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ! ከራሴ በፊት ለዝምባቡዌ እናቴ›› በማለት ዘምረውት ነበርና፡፡


ይህን ጽሑፍ ለማጠቃለል ያህል … ይህ ነው ምኞቴ እና ሌሎች የእናት ሃገር ፍቅርን የተመለከቱና ለኢትዮጵያም ፍቅር ሲል የተከፈሉ መስዋዕትነቶችንበመዘከር… በኩል የተሠሩ ሙዚቃ ወይም የኪነ-ጥበብ ሥራዎችንበተመለከተ፤ የሻለቃ ክፍሌ አቦቸርድርሻ ወይም አስተዋጽዖ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ዛሬ አንዳንዶች በሾርኔ ሲመለከቱት… ከምናስተውለው ታላቁ የካራማራ ድል አንፃር፤ የ‹‹ይህ ነው ምኞቴ›› መዝሙር አበርክቶ በቀላል ቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ አይሞከርምም፡፡


ግጥሙ እንዴት ተፃፈ? በምን ዓይነትስ ሃገር የመውደድ መንፈስና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ክብርና ነፃነት የመቆርቆር ስሜት ልሕቀት?… የሚለው ብቻውን ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያሻው ነው፡፡ ለዛሬው ግን ስለ ክቡር ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር እና ስለ ይህ ነው ምኞቴ መዝሙር ጉዳይ በአጭሩ ለማንሳት የፈለኩት ነጥብ በዚሁ ይቋጭ፡፡ ክፍሌ እንደ ብሔራዊ መዝሙርህ ሁሉ ሕያው ሆነው በሚዘልቁት ሥራዎችህና በመልካም ኢትዮጵያዊ ባሕርይህ መቼም ይሁን መቼ ክብር ይገባሃል፡፡ ያሰንብትልኝ!

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 231 መጋቢት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ...

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...