Home ቆይታ “ወረራ እየተፈፀመባቸው ባሉ የአፋር አካባቢዎች ምንም ዐይነት የመከላከያ ሠራዊት የለም”

“ወረራ እየተፈፀመባቸው ባሉ የአፋር አካባቢዎች ምንም ዐይነት የመከላከያ ሠራዊት የለም”

“ወረራ እየተፈፀመባቸው ባሉ የአፋር አካባቢዎች ምንም ዐይነት የመከላከያ ሠራዊት የለም”

“ወያኔ እስካሁን አፋር ክልልን ከ300 ኪ.ሜ በላይ በወረራ ይዟል”

“መንግሥት አማራና አፋርን አግልሎ መደራደሩ የሚያመጣው ፋይዳ የለም”

አቶ ገአስ አሕመድ

ህወሓት መራሹ የጥፋት ቡድን በአፋር ክልል እና ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ እና ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዳግም ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ ህወሓት በአፋር ሕዝብ ላይ ይኽንን የጥፋት ጅራፉን የዘረጋው በዋናነት የሚሌን መሥመር ተቆጣጥሮ ዳግም የኢትዮ ጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት ቢኾንም፣ የአፋር የጸጥታ ኃይል እና ወጣት የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ተጋድሎ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ አሸባሪው ቡድን ከዕለት ዕለት በክልሉ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥፋት ተከትሎ ታዲያ የፌዴራሉ መንግሥት ዝምታን መምረጡ ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳዘነው እንደኾነ፣ የዚህ ሳምንት የመጽሔታችን እንግዳ ያደረግናቸው የአፋር ሰብዓዊ መብት ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገአስ አሕመድ ይናገራሉ፡፡ ለመኾኑ ህወሓት እስካሁን ምን ያህል አካባቢዎችን ተቆጣጠረ? ያደረሰውስ ጥፋት እንዴት ይገለጻል? ከጉዳዩ አደገኛነትና አሳሳቢነት አንጻር የመንግሥትና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ሚና ምን መኾን አለበት በሚለው ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፡- የጦርነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ ከተባለ ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው ሕወሓት ዳግም አፋር ላይ ወረራ የፈጸመው? ህወሓት እስካሁን በአፋር ውስጥ ምን ያህል መንደሮችን ተቆጣጥሯል?

ገአስ፡- ጦርነቱ ተጠናቀቀ በተባለበት ጊዜም አፋር ላይ ውጊያው አልቆመም ነበር፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ ቆመ የተባለበት ጊዜን ጨምሮ እስከ አሁን በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ህወሓት መንደሮችን ሳይኾን አምስት ወረዳዎችን ነው የተቆጣጠረው፡፡ ለምሳሌ ኪልቦቲራሱል የተባለው አካባቢ ወደ ስምንት ወረዳዎች አሉት፡፡ የዚህ ዞን ዋና ከተማ አብአላ የምትባልና ከመቀሌ 45 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝ ናት፡፡ ህወሓት የመጀመሪያውን ጦርነት ያደረገው በዚያች ከተማ ላይ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቀጥሎ ያለው ከተማ መጋሌ የሚባለው ሲኾን ሦስተኛው ደግሞ ኤሬብቲ ወረዳ ነው፡፡ አራተኛው ኮልነባ ሲባል አምስተኛው ደግሞ በራህሌ በመባል ይታወቃል፡፡ ህወሓት በአሁኑ ሰዓት የተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እነዚህ ናቸው፡፡

ግዮን፡- ህወሓት እነዚህን ወረዳዎች ከተቆጣጠረ ምን ያህል ጊዜ ኾነው? ያደረሰውስ ጉዳት ምን ይመስላል?

ገአስ፡- የመጀመሪያው ነገር እነርሱ ያለ የሌላ ኃይላቸውን እና ከባድ መሣሪያቸውን ጨምረው መጀመሪያ የወረሩት አብአላ ከተማን ነው፡፡ አብአላ ከመቀሌ 45 ኪሎ ሜትር ላይ ቢገኝም የአፋር ክልል ድንበር ላይ ለመድረስ ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ ያስኬዳል፡፡ መጀመሪያ ጥሰው ገብተው ከባድ መሣሪያ የተከሉበት ቦታ ስለነበር ከዚያ በኋላ ከተማውን ከባድ መሳሪያ ለመደብደብ ቻሉ፡፡ በኋላም የአፋር ልዩ ኃይል ከባድ መስዋዕትነት ከፍሎ ቦታውን ማስለቀቅ ቻለ፡፡ ህወሓት ግን በድጋሜ ከ80 ሺህ በላይ የሚኾን የሰው ኃይልና መካናይዝድ ጦር በማሰለፍ አብአላን መቆጣጠር ቻለ፡፡ ምንም እንኳን አብአላን መቆጣጠር ቢችሉም ለመያዝ ግን ከ15 ቀን በላይ ውጊያ አድርገው ነበር፡፡ በቀላሉ አይደለም ከተማዋን በእጃቸው ያስገቧት፡፡ ከዚያ በመቀጠል ግን መጋሌና ኤረብቲንን ተቆጣጠሩ፡፡ በራህሌና ኮነባ ከእነዚህ ከተሞች ራቅ ያሉና 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ቦታው ራቅ ያለ ቢኾንም በመሐል ያለው ከተማ ሳይኾን ጫካና ምድረ በዳ በመኾኑ በቀላሉ እነዚህን ከተሞች ሊወሩ ችለዋል፡፡ በዚህም ሻይጉቢ ተብላ የምትጠራውን የበራህሌ አንድ ቀበሌ ሊቆጣጠሩ ችለዋል፡፡ እዚያ ቦታ ላይም ከ15 ቀን በላይ ከፍተኛ ውጊያና ትንቅንቅ ተካሄዷል፡፡ ከዚያ በኋላም በአይሲ በኩል ሌላ ኃይል አስገብተው ከነባን ለመያዝ ጦርነት ከፈቱ፡፡ ለሳምንት ያህል ውጊያ ከተካሄደ በኋላም የኮነባን አንድ ወረዳ መቆጣጠር ቻለ፡፡

ግዮን፡- ህወሓት እነዚህን አምስት ወረዳዎች ከተቆጣጠረ ወደ አፋር ምን ያህል ኪሎ ሜትር ገብቷል ማለት ይቻላል?

ገአስ፡- አፋር ውስጥ በአጠቃላይ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ገብተዋል፡፡ ከመቀሌ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ወደ አፋር ዘልቀዋል፡፡ በኮነባ በኩል ግን መቶ ኪሎ ሜትር አካባቢ ነው የገቡት፡፡

ግዮን፡- ህወሓት ይን ሁሉ ኪሎሜትር ወደአፋር ክልል ሲገባ የማዕከላዊ መንግሥቱ ዝምታ ከምን የመነጨ ነው ማለት ይቻላል?

ገአስ፡- ይኼ የሁሉም የአፋር ሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ የመንግሥት ዝምታ ብዙ ግልፅ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጦርነቱ እንደጀመረ መንግሥት ከባድ መሣሪያዎችን እመታለሁ በሚል የድሮን ጥቃት በህውሓት ላይ ሲሰነዘር ነበር፡፡ በዚህም አንድ ሦስት የሚኾኑ ነገሮችን ከአቃጠለ በኋላ በአንድ በኩል ደመና ከልሎናል በማለት፣ በሌላ በኩል የአራት ኪሎ ሁኔታ ይዞት ነው መሰል ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ለ15 ቀናት እነዚህ ወረዳዎች እንዳይያዙ መከላከያ ድጋፍ ሰጥቶ ህወሓትን ባለበት ማቆም ተችሎ ነበር፡፡ የተወሰኑ ከባድ መሳሪያዎችንም ሲያቃጥል ነበር፡፡ ከዚያ በኋል ግን ህወሓት አዳዲስ መሣሪያዎችን በማስገባትና ከፍተኛ ኃይል በማሰማራት ነው አካባቢዎቹን የተቆጣጠሩት፡፡ እኔ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዳያስፖራ አባላት ስብሰባ ላይ በነበሩ ሰዓት የአፋርን የወረራ ጉዳይ አንስቼላቸው ነበር፡፡ “አብአላ ከተማ በከባድ መሣሪያ እየተደበደበ ነው፤ እርሶ ድርድር ሊያደርጉ ነው የሚል ነገር ይሰማል፣ የአፋር ወጣቶች በአፋርኛ የሚጽትን ስለማያዩ እንጂ በከፍተኛ ሁኔታ እየታሙ ነው፣ ጦርነቱን እላያችን ላይ ጥለውብን ብቻችንን እየተጋፈጥን ነው እየተባሉ ነው” የሚል ጥያቄን አንስቼላቸው ነበር፡፡

እርሳቸው ግን አድበስብሰው ነበር ያለፉት፡፡ በዚህ ሥጋት አይግባህ እኛ የአፋርን ሕዝብ አንጥለውም፣ ወዘተ የሚል ዐይነት ምላሽ ነበር የሰጡኝ፡፡ ነገር ግን በተግባር ሲደረግ አልተስተዋለም፡፡ አሁንም የአፋር ወጣቶች እና ሽማግሌዎች የሚያነሱት ይኼንኑ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው የአፋር ሽማግሌዎች ወጣቱን ሞራል ሲሰጡ የነበረው “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ኖሮባት ስለተቸገረች እንጂ ስብሰባው እንዳለቀ መካናይዝድ ጦር ይገባላችኋል” እያሉ እንደነበር ሰሞኑን ሽማግሌዎቹ መጥተው አግኝቻቸው ነግረውኝ ነበር፡፡ እና ሽማግሌዎቹ የሚሉት ከዚህ በኋላ በውሸት ሕዝብን ማረጋጋትና ወጣቱን ማበረታታት አንችልም ብለው ነው የነገሩኝ፡፡ ሕዝቡም ደግሞ የነበረው ተስፋ እየተሟጠጠ እንደኾነ ነግረውኛል፡፡

ግዮን፡- ጦርነቱ የቆመ ጊዜ በአብአላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት አልነበረም ማለት ነው?

ገአስ፡- በአፋር ክልል ላይ አንድም የመከላከያ ሠራዊት አልነበረም፤ የለምም፡፡ በተለይ አሁን ወረራ እየተፈፀመባቸው ባሉበት አካባቢዎች ምንም ዐይነት መከላከያ ሠራዊት የለም፡፡ በራያ በኩል ግን አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሠፍሯል፡፡ እርሱም ትዕዛዝ ስላልተሰጠው ይሁን በሌላ ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡ እነርሱ ያሉት ህወሓት መጀመሪያ ላይ ጦርነት አደረገበት ባሉት ቦታ ላይ ነው፡፡ ቦታው የመጋሌ አዋሳኝ ወረዳ ነው፡፡ ነገር ግን እዚያ ቢኖሩም እስካሁን አንዳች ያደረጉት ነገር የለም፡፡

ግዮን፡- በአብአላና በመጋሌ በኩል በወያኔ ዘመን የኮንትሮባንድ ንግድ ይካሄድበት ነበር፡፡ አብዛኛው ነዋሪም ከትግራይ ጋር ተጋብቶ የሚኖር ነው የሚባል ነገር አለና ብታብራራልኝ?

ገአስ፡- ኮንትሮባንድ ተሠርቶበት ሊኾን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ይሠራበታል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በእርግጥ እዚያ አካባቢ ያሉት ከትግራይ ጋር የሚዋሰኑ የተወሰኑ ጎሳዎች ናቸው፡፡ የተዋለዱ እንዳሉ ኾነው ያ አካባቢ የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሥዩም አወል መኖሪያ አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ግለሰብ ጋር በተያያዘ የመጣ ካልኾነ ያን ያህል ለውጥ አያመጣም፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ቦታ ላይ መጎራበት የሚባለው ነገር አለ፡፡ ይህ መጎራበት ግን ሁሌ በተለይ በአብአላ ላይ የልዩ ዞንነት ጥያቄን ሲያስነሳ ነበር፡፡ ከፍተኛ የኾነ እንቅስቃሴ ያደርጉም ነበር፡፡ የተሰጣቸው ምላሽም እናንተ የመጣችሁት ትላንትና ነው፣ ስለዚህ ይህን ጥያቄ የማንሳት መብት የላችሁም ተብለው አንዳንድ የውክልና ቦታ በአብአላ ውስጥ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም በአብአላ ከተማ ሁለት ሦስት ሰዎች ውክልና ነበሯቸው፡፡

እነርሱ ግን የራሳቸው አድርገው ነበር የሚቆጥሩት፡፡ በዚያ ምክንያትም ከአፋር ጋር ሁሌ ግጭት ይገጥማሉ፡፡ አሁንም ደግሞ የአብአላ ጦርነት ሲጀመር የኾነው በከተማዋ የነበሩ ትግሬዎች ቤተክርስቲያን ውስጥ መሣሪያ በመደበቅ ጦርነቱ ሲጀመር እነርሱ ወደ ቤተክርስቲያን በመሮጥ ከጀርባ ጦርነት ከፈቱባቸው፡፡ አፋሮች ግን ትግሬዎቹ ወደ ቤተክርስቲያን ሲሮጡ “እነዚህ ሰዎች ምን ነካቸው እኛ አብረውን የኖሩትን ዕኮ አንነካቸውም” እያሉ በነበሩበት ሁኔታ ከጀርባቸው ተኩስ ከፈቱባቸው፡፡ እነርሱ ቤተክርስቲያን የቀበሩትን ቆፍረው በማውጣት ነው አፋር ላይ ያዘነቡት፡፡ እነዚህ ሰዎች ለብዙ ዓመታት በዚያ አካባቢ የኖሩና የተዛመዱ ሰዎች ናቸው፡፡ አፋሮችን በጣም የገረማቸው ነገርም አንድም በትግራይነቱ የተጠቃ ሰው በሌለበት ሁኔታ 30 እና 40 ዓመት የኖሩበትን ማኅበረሰብ መውጋታቸው ነው፡፡ እንዴ ትግሬዎች እኮ በሰመራ በሎግያ በብዛት ነው ያሉት፡፡ በተለይ በወያኔ ጊዜ ሆቴሎች የሠሩትና ትላልቅ ቦታዎችን የያዙት እነርሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድም ሰው ነክቷቸው በማያውቅ ሁኔታ በዚህ ክስተት ይኽን ዐይነት ድርጊት መፈጸማቸው አካባቢውን ያሳዘነ ነው፡፡

ግዮን፡- እነዚህን አካባቢዎች ለመቆጣጠር የአፋር ባለሥልጣኖች ከህወሓት ጋር የሠሩበት ሁኔታ አለ?

ገአስ፡- እኔ ይኼን በእርግጠኝነት መናገር አልችልም፡፡ እነርሱ ባይገቡም በፊትም በወያኔ አመለካከት ያላቸው እና ከጀመሪያው አንስቶ ለእርሱ የታገሉ ሁለት ሦስት ሰዎች በውስጣቸው ይኖራሉ፡፡ እነዚያ እንግዲህ ከሚዛመዷቸው ሰዎች ጋር ምናልባት የተወሰነ መረጃ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አስርገው አስገብተው ነበር የሚባል ነገር አለ፡፡ የመጀመሪያው ጦርነት መጋሌ ላይ ሲደረግ አፋሮች ነን ብለው በአፋርኛ ካናገሯቸው በኋላ አፋሮች ናቸው ተብለው ሲጠበቁ ከቀረቧቸው በኋላ ብዙዎችን መስዋዕትነት አስከፍለዋል፡፡ ይህ አይነት ተጽዕኖ በተወሰነ ደረጃ ነበር፡፡ በተለይ ጁንታው ውስጥ የገቡ ሰዎች በመለመሏቸው ሰዎች አማካኝነት ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ጁንታው ውስጥ የገቡ ሰዎች ጥቅማቸው የቀረባቸው ከሥልጣናቸው የተገፋ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በወያኔ ዘመን ፈላጭ ቆራጭ የነበሩ ከአምስት የማይበልጡ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነርሱ በዝምድና እና መሰል ነገሮች የመለመሏቸው የተወሰኑ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የመጀመሪያው ጦርነት ሲከፈት በአፋርኛ “አፋሮች ነን” ብለው የልዩ ኃይሉን ልብስ ለብሰው ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ግዮን፡- የቀድሞው ባለሥልጣን አቶ ስዩም አወል የተለያዩ የአፋር ልዩ ኃይሎችና ወጣቶችን ይዞ ወደ መቀሌ ገብቷል የሚባል ነገር አለና ስለዚህ ጉዳይ ምን ትለላለህ?

ገአስ፡- ስዩም አወል ማለት ለህወሓት ሲታገል የወጣትነት ዘመኑን የጨረሰ ግለሰብ ማለት ነው፡፡ ማንበብና መፃፍ የማይችል ያልተማረ መሃይምም ነው፡፡ በወያኔ ዘመን ለ22 ዓመታት የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ነበር፡፡ ለአራት ወይም ለአምስት ዓመት ያህል ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት እንዲኾን የተደረገው በእነ አቶ ዓባይ ወልዱ አማካኝነት ነው፡፡ ለውጡ እስኪመጣ ድረስም የክልሉ ፕሬዝዳንት እርሱ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሰውየው የአፋር ትውልድ ይኑረው እንጂ አመለካከትና ሕይወቱን የሰጠው ለህወሓት ነው፡፡ ህወሓትን በጣም የሚፈራ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ የአፋር ደም ስላለው አፋር ይባላል እንጂ ግለሰቡ ሙሉ ለሙሉ አመለካከቱ የህወሓት ነው፡፡ ክልሉን በመከፋፈል ለህወሓቶች በጣም ሲሠራ የነበረ ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰው ይዞ ሄደ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ የተወሰኑ የእርሱ አባላቶች የነበሩትን ከ30 እና ከ40 የማይበልጡ ግለሰቦችን ነው ይዞ የሄደው፡፡ በእንዲዚያ ዐይነት መልኩ የወሰዳቸው ወይም ደግሞ በአፋር የጎሳ ባሕል ምክንያት ተደናግሮ ባለማወቅ ዝም ብሎ የመከተል ነገር ስለሚኖር በዚያ መንገድ የሄደ ካልኾነ በስተቀር ብዙ የሰው ኃይል ይዞ አልሄደም፡፡

ግዮን፡- ይህ የቀድሞ ባለሥልጣን መቼ ነው መቀሌ የሄደው?

ገአስ፡- ወደ መቀሌ የሄደው ሁለተኛው ጦርነት ከመጀመሩ እና ሦስት የአፋር ወረዳዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ወያኔን ተስፋ አድርጎ ነው፡፡ አቶ ስዩም ህወሓት ካሸነፈ አፋር ክልል ላይ ልክ እንደበፊቱ እንዲሾም ይፈልጋል፡፡ ለዚህ እንዲያመችም ቀድሞ ህወሓት ውስጥ የነበሩ ታጋይ ግለሰቦች የአፋር ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲመሰርቱ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሰዎች ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ነበሩ፡፡ በክልሉ ውስጥ አምስት ድርጅቶች ቢኖሩም የእነርሱ ኃይል የበላይነት ስለነበረው ክልሉን ተቆጣጥረው ቆይተዋል፡፡ አሁንም ያንን ተስፋ አድርጎ ነው ወደ እነርሱ የሄደው፡፡

ግዮን፡- ህወሓት በተቆጣጠራቸው አምስቱ ወረዳዎች ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ምን ያህል የሰው ሕይወት አልፏል?

ገአስ፡- በጣም የሚገርመው ነገር ህወሓት በካዛኪስታው ሽንፈት ተዋርዶ እልህና ቁጭቱን ሰንቆ ነበር ለዳግም ወረራ የመጣው፡፡ ይህን እንድል የሚያስችለኝ ያደረሰው ጭፍጨፋ እና እርድ ከፍ ያለ በመኾኑ ነው፡፡ ህወሓት ያረዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ በተለይ መጋሌ፣ ኤረርቲ፣ በራህሌ፣ አብአላና ከነባን ሲቆጣጠር የማረካቸውን ሰዎች አርዷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን ከተማዋ እንድትወድም ተደርጓል፡፡ ትናንት ከአካባቢው የመጡ ሽማግሌዎችን ሳናግር ከተሞቹ ከ500 በላይ መድፍ ተተኩሶባቸዋል፡፡ ሁለት መቶ የከሸፈ መድፍ ማየታቸውንም ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ11 በላይ ነፍሰጡር ሴቶች በድንጋጤ ጽንሣቸው የተጨናገፈበትን ሁኔታ ሰምቻለሁ፡፡ ወደ 12 የሚኾኑ የ110 እና የ120 ዓመት እድሜ ባለፀጋ አዛውንቶች በገመድ አስረው ከትልቅ ተራራ ላይ ጎትተዋል፡፡ ልጆች የጠፋባቸው በርካታ ቤተሰቦችንም ማየት ችያለሁ፡፡ በከባድ መሣሪያው ድንጋጤ ብዙ ቀውሶች ደርሰዋል፡፡ የአፋር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል አድርሰውበታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ “ዕቅዳችንን ያበላሹብን አፋሮች ናቸው፤ ምክንያቱም ልንቆጣጠረው የነበረውን ሚሌ እንዳንቆጣጠረው ያደረጉን እነርሱ ናቸው” የሚል እምነት ያላቸው በመኾኑ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ከደብረጸዮን ጀምሮ እስከ እስታሊን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሰሩበት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

ግዮን፡- ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ በመንግሥት ላይ ያለው ምልከታ ምንድነው? የሚጠብቁትስ ተስፋ አለ?

ገአስ፡- በጣም የሚያሳዝነው የአፋር ሕዝብ አሁን ኢትዮጵያዊነቱን ላይ ቅሬታ እየተፈጠረበት ነው፡፡ ምክንያቱም ብቻውን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ በመኾኑ ነው፡፡ ህወሓቶች ሚሊኔ እንዳይቆጣጠሩ በተደረገው ትግል ላይ ከፍተኛ ርብርብ አድርገናል፡፡ መንግሥትም በወቅቱ ጥሩ የኾነ አቋም ይዞ ነበር ከጎናችን ሲንቀሳቀስ የነበረው፡፡ ዛሬ ግን ጦርነቱ ብቻችንን በላያችን ላይ ሲከፈት የኢትዮጵያ መንግሥት ሰፊ ቁጥር ያለውን ሰራዊት ከክልሉ በማስወጣቱ ምክንያቱም ትልቅ ጉዳት ደርሷል፡፡ ህወሓት መካናይዝድ የታጠቀ በመኾኑ ሌላ ሀገር የወረረ እንጅ ለአንድ ክልል የተዘጋጀ አይመስልም፡፡ መንግሥት ይኼንን እየየ ዝም ማለቱ ከጀርባው ምን ቢኖር ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ወይ? ምክንያቱም የፌደራል መንግሥት በማንኛውም ክልል ላይ ይህ ኃይል ገብቶ ወረራ ሲፈጽም የመከላከልና ሰላም የማስከበር ኃላፊነት ያለው በእርሱ ላይ ነው፡፡

ስለዚህ እኛ ክልል ገብቶ ትላንት ሲሰጠን የነበረውን ድጋፍ መንፈግ የፈለገው ለምንድነው? የአፋር ሕዝብ በእነዚህ ሰዎች እንዲያልቅ ይፈልጋል ወይ የሚል ብዙ አይነት ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡ በተለይ ከመንግሥት ቋሚ ኮሚቴ የመጣ ጊዜ ሽማግሌዎች ግልፅ በኾነ ቋንቋ “እኛ ኢትዮጵያውያን ስላልኾንን ነወይ ድጋፍ የማይደረገው” ብለው አንስተዋል፡፡ በትላንትናው ዕለትም የተመድ ምክትል ፋቲማ እና እንዲሁም ኦባሳንጆ ወደ ክልሉ አቅንተው ነበር፡፡ እዚያም ላይ የተነሳው ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ በመንግስት በኩል ምንም አይነት ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ተናግረዋል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ላይ የማንደራደር ኾነን እያለ ከጀርባው የኾነ ነገር አለ ማለት ነው ወደሚል ጥግ እንደገፋቸው ነው የገለጹት፡፡

ግዮን፡- ከውጭ ከመጡት ከእነኦባሳንጆ የተገኘው ምላሽ ምንድነው?

ገአስ፡- እርዳታን በተመለከተ ለመርዳት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ኮነባና በራህሌ ላይ ያሉ ሰዎች ተቆርጠው መቅረታቸው ነው፡፡ በወያኔ ተከበው መውጣት አይችሉም፤ የአፋር ሽማግሌዎች እነዚህን ሰዎች በተመለከተ የሚሉት ወደ ቦታው በመኪና መግባት ስለማይቻል በአውሮፕላን እርዳታ እንዲደርሳቸው ይደረግ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም መንገዱን ህወሓት ስለቆረጠው መግባት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሰዎቹ በረሃብ ማለቃቸው ነው፡፡ እነዚህ ተቆርጠው የቀሩ ሕዝቦች ሁለት አማራጭ ነው ያላቸው፡፡ ይኸውም ወይ ሞት ወይም ለህወሓት እጅ ሰጥተው ህወሓት ባላቸው መልኩ መኖር ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት በኋላ ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ ምክንያቱም ህወሓቶች ይህን ዞን የእኛ ነው የሚል አጀንዳ ስለነበራቸው በኋላ ቀላል አይኾንም፡፡ እዚያ ተቆርጠው የቀሩ አፋሮች መንግሥት የማይረዳቸው ከኾነ ለምን እንደሚታገሉ ላይገባቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተባብረው በግዴታ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይኼን ማየት ያልቻለ መንግሥት ኃላፊነቱ ምኑ ላይ ነው የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እኔ ኦባሳንጆ እንባ አውጥተው እንዳለቀሱ ሰምቻለሁ፡፡ በተለይ የዩኤኗ ምክትል የነበረውን ሰቆቃ ስቃይ ስትሰማ ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ እንደገባች ሰምቻለሁ፡፡ ሽማግሌዎቹ የነበረውን ሁኔታ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ የሚመጣውን ውጤት እንግዲህ በሚቀጥሉት ቀናት የምናየው ይኾናል፡፡

አሁን ለጊዜው ከዚያ ሸሽተው የመጡ 60 በሚል የሚጠራ እና ከኤፍዴራ ወዲህ የሚገኙ ቦታ ላይ የሠፈራ ጣቢያ ተቋቁሟል፡፡ ግን ቦታው በጣም በርሃማና ከ45 ሴልሸስ በላይ ሙቀት ያለው አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ውሃ በጣም ያስፈልጋቸዋል፤ የምግብ እጥረትም በዚያ በኩል አለ፡፡ በአብዛኛው የተፈናቀሉት ሕፃናትና ሴቶች ከመኾናቸው አንፃር ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ያሳያል፡፡

ግዮን፡- ከውጭ የሄደው የእነኦባ ሳንጆ ቡድን “መንግሥት ድርድር ላይ ስላለ ታገሱ” የሚል ነገርም አንስቷል ይባላልና አንተ ይኼንን እንዴት ታየዋለህ? ድርድሩስ ለአፋር የተለየ ነገር ያስገኛል?

ገአስ፡- በመጀመሪያ ድርድር ማለት ምን ማለት ነው? ሰላም ሁላችንም የምንፈልገው ነው፡፡ ነገር ግን አፋርና አማራን ያገለለ ሰላም ምን ማለት ነው? መንግሥት አማራና አፋርን አግልሎ ከእነርሱ ጋር ቢደራደር ሊያመጣ የሚችለው ፋይዳ ምንድነው? ምክንያቱም ሰላምን ተግባራዊ የሚያደርገው ይኼ ሕዝብ ነው፡፡ እዚህ ሕዝብ ላይ ደግሞ ጦርነቱ እስካሁን አልቆመም፡፡ ለሰላም መጀመሪያ መደረግ ያለበት ወያኔ ትጥቁን እንዲያወርድ ማድረግ ነው፡፡ የአፋር ሕዝብ “ጦርነት ተከፍቶ ሰላም የለም፤ ዝናብ እየዘነበ መንቀሳቀስ የለም” የሚለው ብሂል አለው፡፡ ጦርነቱ ሳይቆም ምን ዐይነት ድርድር ነው የሚደረገው፣ አፋርን ያላካተተ ሰላም በማን ላይ ነው ተግባራዊ የሚኾነው? መንግሥት ምን እንደሰበ ግራ የሚገባ ነው፡፡

መንግሥት ሰላሙን የሚያደርገው ለራሱ ብቻ ከኾነ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ማንም እንደሚረዳው ለሰላም ጦርነት መቆም አለበት፡፡ ጦርነት ላይ ኾኖ የሚደራደር ኃይል ነገ ራሱን እንደመንግሥት ያስባል፡፡ እኔ እዚህ ላይ አስረግጬ መናገር የምፈልገው ዛሬ ይኼ ሕዝብ ጥሪ ባደረገበት ሰዓት ጆሮ የተነፈገው ሕዝብ ነገ ወያኔ ጀርባውን አዙሮ ጦርነት ቢከፍትበት ማንም ሊዋጋለት አይችልም፡፡ ይሄ ደግሞ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ኪሳራ ነው፡፡ ምክንያቱም የአፋር ሕዝብ መንግሥት በጠራው ጊዜ በሞራልና በኢትዮጵያዊነቱ ጠንካራ ኾኖ ሲዋጋ የነበረ ሕዝብ ዛሬ መከራው የእርሱ ብቻ እንዲኾን ተደርጎ ዝም ተብሎ መታየቱ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መንግሥትስ በየትኛው ሞራሉ ነው ነገ ጥሪ የሚያቀርበው? ሕዝቡ በየትኛው ስሜቱ ነው ከመንግሥት ጎን ቆሞ ዙፋን የሚያስጠብቀው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ሰላምና ድርድር ብዙ ነገሮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡ እንደሚታወቀው የአፋር ሕዝብ አስፈላጊነት በጊዜ ሁነት የሚለዋወጥ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገራችን እስካለች ድረስ የአፋር ሕዝብ ስትራቴጂያዊ የኾነ ጠቀሜታ አለው፡፡

ግዮን፡- ህወሓት አፋር ላይ የተለየ ትኩረት ለምን አደረገ?

ገአስ፡- እንደሚታወቀው ወያኔ ባለፈው ጦርነት “እናንተ የእኛ ጉዳይ አይደላችሁም፣ አሳልፉንና ሚሌን እንያዝ” እያለ የአፋር ሕዝብን ሲማፀን አፋሮች ደግሞ “እኛን አልፋችሁ የኢትዮጵያን ጉሮሮ ማነቅ አትችሉም” ብለው ከለክሏቸው፡፡ የአፋር ሕዝብ ያን ጊዜ ለቆ ቢሄድ ምን ይፈጠር እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ህወሓት ከ29 ጊዜ በላይ ነው ሰብሮ ለማለፍ የሞከረው፡፡ በተለይ በካዛኪስታና ጭፍራ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ያኔ ህወሓት አፋሮች ለቀውለት ሰብሮ ቢያልፍ ኖሮ ዛሬ እኔና አንተ እንዲህ ማውራት አንችልም ነበር፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣንም በዚህ ዓይነት መልኩ ሊቀጥል አይችልም ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሚሌ ተያዘ ማለት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝበ ጉሮሮ ተያዘ ማለት ነው፡፡ የነዳጅ፣ የምግብ፣ የቁሳቁስ ወዘተ እጥረት ሊከሰት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዳይከሰት የአፋር ሕዝብ ተከላክሏል፡፡ የአፋር ሕዝብ ዛሬ እራሱ ቢለቀው አሁን ካለበት ወደ ዳሎል ወረዳ ጦርነቱ ሰፍቶ ወደ አፍዴራ ህወሓት ከመጣ ቀጥታ ሰንጥቆ ሰርዶ ወደሚባል ቦታ ይደርስ ነበር፡፡ ህወሓት ሰርዶን ተቆጣጠረ ማለት የጂቡቲ አዲስ አበባ መስመር ተዘጋ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ ሰርዶን ተቆጣጠረ ማለት ከባድ መሣሪያ በገፍ አስገባ ማለት ነው፡፡

ህወሓት ከጅቡቲ መንግሥት ጋር ከፍተኛ የኾነ ግንኙነት አለው፡፡ 33 ቢሊዮን ዶላር አስወጥቶላቸዋል፡፡ ከሌላ በኩል አሜሪካ ትልቅ ቤዝ ያላት እዚያ ጅቡቲ ነው፡፡ ስለዚህ ወያኔ ሰርዶ ተቆጣጠረ ማለት የሚፈልገውን መሣሪያ በቀጥታ ወደ መቀሌ አስገባ ማለት ነው፡፡ ነዳጅ እንደልቡ አገኘ ማለት ነው፡፡ ይኼ ግን በመንግሥት ዘንድ ትኩረት ያልተሰጠው የሚመስል ነገር ግን የሚያውቀው ኾኖ ተሰምቶኛል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የአፋርን ሕዝብ ተስፋ ባያስቆርጠው ይሻላል በኢትዮጵያዊነቱ የነበረውን ጥንካሬ ይዛ እንዲቀጥል ቢያደርገው ይበጃል፡፡ ያለበለዚያ ግን ሊፈጠር የሚችለው ነገር ከባድ ነው፡፡ ወያኔ እዚያ ደረጃ ላይ ከደረሰ መስዋዕትነት የሚከፍለው የመንግሥት መከላከያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ይኾናል አሁን እንደ ጧፍና ሻማ እየቀለጠ ለኢትዮጵያ ብርሃን የኾነው የአፋር ሕዝብ ነገ ተስፋ ከቆረጠ ሻማነቱ ይጠፋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ግዮን፡- ለጠቅላይ ሚኒስትሩስ ምን የምትለው ነገር አለህ?

ገአስ፡- እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያ መንግሥት በአጠቃላይ ብዙ ችግር አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡ የውጭው አለም ላይ የሚደረገውን የ “no more” ሰላማዊ ሰልፍ አስተባብረናል፤ ታግለናል፡፡ ያን ትግል ያደረግነው ኢትዮጵያ እንደሀገር መቀጠል አለበት ብለን ስለምናምን ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ገሀነም ድረስ እንሄዳለን ባሉበት ሰዓት እኛ ደግሞ አታፈርሱም የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ በዚያን ጊዜ ጭምር መንግሥት መረጃዎችን ለሕዝብ አለመስጠት እና የመዘግየት ባሕሪ ይታይበት ነበር፡፡ ወያኔ ደብረሲና እስኪደርስ ድረስ በማይገባን መልኩ ጩኸታችን አልተሰማም ነበር፡፡ እኔ የማነሳው ጥያቄም መንግሥት ከዚህ መማር አልቻለም ወይ የሚል ጥያቄ ነው፤ ምክንያቱም አድበስብሶ ማለፍ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ስለዚህ ከትንትን መማር ካልቻሉ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአፋር አንድ አባባል አለ “በግ ሰማይን የምታየው ልትታረድ ስትል በመጨረሻ ሰዓት ነው”፡፡ የመንግሥት ነገር እንደዚያ እንዳይኾን እሰጋለሁ፡፡

ግዮን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥህ?

ገአስ፡- ማስተላለፍ የምፈልገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መንግሥትን የመጠየቅ ኃላፊነት የአፋር ብቻ መኾን የለበትም፡፡ የአፋር ሕዝብ ትናንትና የታገለውና ዋጋ የከፈለው ለመቶ 10 ሚሊዮን ሕዝብ መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ምክንያቱም መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ጎሮሮን የሚይዙ ነገሮች ሲሠሩ ነበር፡፡ ያንን በቆራጥነት ታግሎ እዚህ አድርሷል፡፡ ዛሬ የአፋር ሕዝብን ድምጽ ለመኾን የግድ አፋር መኾን አይጠበቅባቸውም፡፡ ስለኾነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ አፋር ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር በሰላማዊ ሰልፍም ጭምር መንግሥትን የማሳሰብ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በሁሉም ክልሎች የአፋርን ጥያቄ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከ300 ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከጎንህ ነን የሚለውን ነገር ማንፀባረቅ አለባቸው፡፡

በመንግሥት ተስፋ የቆረጠው ሕዝብ በሕዝቡ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ ለሕዝብ ያለው ግንኙነት ተስፋ ተቆረጠ ማለት አብሮ የመኖሩ እሴት ተሸረሸረ ማለት ነው፡፡ ሕዝቡ የአፋር ተፈናቃዮችን የመርዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ ለምሳሌ እኛ መቶ ብር ለአፋር ወገን በሚል በአፋር ልማት ማኅበር አካውንት ውስጥ የሚገባ ገንዘብ በፌስቡክ ሰብስበናል፡፡ አፋር ኢንፎርሜሽን ሴንተር በሚል ፌስቡክ ገፃችን ላይም ለጥፈናል፡፡ ከመቶ አስር ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ሚሊዮን እንኳ ቢረዳ መቶ ሚሊዮን ይኾናል፡፡ ሁለት መቶ ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ቢሰበሰብ ለተፈናቀሉ ወገኖች ቀላል ድጋፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይኼ ወገን “ዛሬ መንግሥት ቢረሳኝም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እየረዱኝ ነው” የሚል ስሜት ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ ይኸን አይነት ርብርብ ሊደረግለት ይገባል፡፡ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ በአፋር ሕዝብ ላይ የሚደረገውን ግድያና የጁንታው ወረራ የመቃወም ኃላፊነት አለበት፡፡ ምክንያቱም ዛሬ አፋር ብቻውን ከኾነ የሚጮኸው ነገ ደግሞ አማራ ወይም ሌላው ብቻውን ይጮሃል፡፡ ያ እንዳይፈጠር በጋራ መቆም መቻል አለብን ነው የምለው፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ትዕዛዝ የሚሰጠው ከመንግሥት ነው፡፡ ያን ያህል የምላቸው ነገር የለኝም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ትዕዛዝ ቢሰጣቸው ኖሮ እነርሱ ትዕዛዝ ተቀብለው ይገቡ ነበር፡፡ መንግሥት ግን አሁንም አረፈደበትም፡፡ ስለዚህ በቁጭት መልክ የአየር ድብደባ አድርገናል ወዘተ ከማለት መላቀቅ ያስፈልገዋል፡፡ ለውጥ የሌለው አንድ የአየር ድብደባ ተደርጎ መቶ ቃላት መደርደር ትርጉም የለውም፡፡ ትርጉም ያለው ሥራ ተሠርቶ ቢኾን ኖሮ ህወሓት 5 ወረዳዎችን አይቆጣጠርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ትላንት እኔ ኢሳት ቀርቤ ከተናገርኩ በኋላ አንድ የመከላከያ ሰው ቀርበው የድሮን ጥቃት ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የድሮን ጥቃት ሦስት ወይም አራት ተደርጎ ሊኾን ይችላል፡፡ ነገር ግን አምስት ወረዳ እስከመቆጣጠር የደረሰ ኃይል በዚህ ብቻ ሊመታ አይችልም፡፡ አሁንም አምስት ወረዳ ተቆጣጥሮ ምሽግ እየቆፈረ ባለበት ሁኔታ ላይ ጊዜ የሚሰጠው ከኾነ ብዙ መስዋዕትነት የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ ግዮን፡- ሥለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሰግናለን፡፡