ዋዜማ ሚዲያ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንዲሁም መመሪያዎችና የሙያ ስነምግባር አክብሮ ለመስራት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የስራ ፈቃድ እውቅናውን ተመላሽ ማድረጉን ባለሥልጣኑ አስታወቀ፡፡
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ በበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የእውቅና ፈቃድ አግኝቶ ሲሰራ የነበረው ዋዜማ ሚዲያ፣ “ባለሰልጣኑ ባደረገው ክትትልና ከዜጎችም በተሰጠው አስተያየትና ጥቆማ መሠረት የሚዲያው ዘገባዎች የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ፣ ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው፣ የፌዴራልና የክልል መንግስታት አስተያየትና ምላሽ ያልተካተተበት፣ ሁከት ቀስቃሽ እንዲሁም የሙያ ስነምግባርን የጣሰ የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ የተንጸባረቀበት ሆኖ መገኘቱን” ባለሥልጣኑ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
ይህንንም መሠረት በማድረግ ዋዜማ ሚዲያ ተደጋጋሚ የእርምት ግብረመልስ ሲሰጠው እንደቆየ ያመለከተው መግለጫው፤ ሆኖም የተሰጠውን አስተያያትና የማስተካከያ እርምጃ መቀበል ባለመፍቀዱ የስራ ፈቀዱን ተመላሽ እንዲያደርግ ተወስኖ ይኸው ተግባራዊ መደረጉን አስታውቋል፡፡
“ስለሆነም ዋዜማ ሚዲያ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ የጋዜጠኝነት ስነምግባርን መሰረት ያላደረጉ እንዲሁም በአዋጅና መመሪያ ያልተፈቀዱ ተደጋጋሚ ጥሰቶችን መተላለፉን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሲያከናውንለት የነበረውን ድጋፍ ከዚህ በኋላ ለማቋረጥ ተገዷል” ብሏል ባለሥልጣኑ በመግለጫው፡፡
ባለስልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ዋዜማ ሚዲያ (ሬድዮ) ለፈጸማቸው የተለያዩ ጥሰቶች ከሁለት ወር በፊት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት እንደነበር መግለጫው አስታውሷል፡፡
የዋዜማ ሬዲዮን በኢትዮጵያ መታገድ በተመለከተ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባልሥልጣን ቅዳሜ ጥር 16፣ 2018 ዓ.ም ዋዜማ ሚዲያን/ሬዲዮን በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ ተመልክተናል።
ባለሥልጣኑ ሐሙስ ዕለት ፈቃዳችንን እንድንመልስ ባዘዘን መሠረት ይህንኑ አድርገናል። መግለጫው የተሰጠው ይህንን ባደረግን በሰዓታት ውስጥ ነው።
እርምጃው በማንኛውም መመዘኛ ትክክል ነው ብለን አናምንም። አሳዝኖናልም። ዝርዝሩን በሚገባ አጢነን አስፈላጊና ጠቃሚ ከሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ እንሰጣለን፤ ሌሎች ሕጋዊ አማራጮችን እንከተላለን።
ባለሥልጣኑ ባወጣው መግለጫ፣ ዋዜማ ሚዲያን “የአገርን ጥቅም” አደጋ ላይ በመጣል እና የጋዜጠኝነት ሥነምግባርን ባለማክበር ወንጅሏል። እነዚህን ክሶች የኢትዮጵያን ሚዲያ ለሚከታተሉ ተደራሲዎች፣ ታዛቢዎች እና ባለሞያዎች የሕሊና ፍርድ እንተዋለን።
የዋዜማ ሚዲያ አመራር
ቅዳሜ ጥር 16፣ 2018
