በኔፓል ኑዋኮት ወረዳ በሚገኘው ትሪቡቫን ትሪሹሊ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት ራጄንድራ ዳዋዲ፣ አሰቃቂው ጎርፍ ትምህርት ቤቱን ከመደምሰሱ ከ10 ደቂቃ በፊት ባደረጉት ፈጣን ውሳኔ የ900 ተማሪዎችን ህይወት ታድገዋል።
በዕለቱ ከጧቱ 3፡10 ላይ ጎርፍ እየመጣ መሆኑን የሚገልጹ ጥሪዎች እንደደረሷቸው፣ ሰከንድ ሳይወላውሉ ተማሪዎቹ በፍጥነት ወደ ተራራ እንዲሸሹና ወደ ትምህርት ቤት እየመጡ ያሉ ባሶች እንዲመለሱ አዘዋል። መምህሩ “ውሳኔያችን በ10 ደቂቃ ቢዘገይ ኖሮ፣ ተማሪዎቼን ጨምሮ ሁላችንንም ዛሬ በሕይወት አታዩንም ነበር” ሲሉ አስደናቂውን አጋጣሚ ተናግረዋል።
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የ16 ዓመቷ ተማሪ ዩኒሻ አማትያ እና ጓደኞቿ አደጋው ከመድረሱ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት አምልጠዋል። ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ ጀርባ ባለው ጠባብ መወጣጫ በኩል ወደ ተራራው ሲወጡ፣ ከኋላቸው የነበረው ገበያ በደቂቃዎች ውስጥ በጎርፍ ተጠራርጎ ሲወሰድ በዓይናቸው ተመልክተዋል።
በተራራው ላይ ከፍ ብለው በመሸሸጋቸው ምክንያት ለሁለት ቀናት ያህል ከውጭው ዓለም ተቆራርጠው የቆዩ ቢሆንም፣ የልጅቷ አባት በስልክ ሲያገኛት በደስታ አልቅሷል። በኋላም በሄሊኮፕተር ተነስተው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከ2,400 በላይ ሰዎችን ደብዛ ባጠፋው በዚህ አሰቃቂ የጎርፍ አደጋ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ በጭቃና በፍርስራሽ ተሸፍኗል። ተማሪዋ ዩኒሻ በሕይወት በመተርፏ ብትደሰትም የትምህርቷ ነገርና የጓደኞቿ መለያየት አሳስቧታል። ርዕሰ መምህር ዳዋዲ በበኩላቸው፣ ያንን አጣዳፊ እርምጃ ባይወስዱ ኖሮ የትምህርት ቤቱ ደወል ብቻውን እንደሚቀርና ትልቅ እልቂት ይከሰት እንደነበር ገልጸዋል።
