የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የቅድሚያ ትኩረቱን እንዲፈትሽና በሰው ልጅ ጤና ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪም አቅረበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በጄኔቫ በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ለጦርነትና ለወታደራዊ ዝግጅት የሚወጣው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በአንጻሩ ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሊታደጉ ለሚችሉ የጤና አገልግሎቶች የሚመደበው በጀት እየቀነሰ መሆኑን በማንሳት፣ ይህ አዝማሚያ አሳሳቢና የዓለምን የወደፊት ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደገለጹት፣ ዓለማችን በየስምንት ሰዓቱ ለጦርነት የምታወጣው ወጪ (2.1 ቢሊዮን ዶላር ገደማ)፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ መደበኛ በጀት ጋር እኩል ነው።
“አገራት እርስ በርስ ለመጠፋፋትና የሰውን ልጅ ለመግደል በሚረዱ መሣሪያዎች ላይ ቢሊዮኖችን ሲያፈስሱ፣ በሽታን ለመከላከልና ሕይወትን ለመታደግ በሚረዱ የጤና ዘርፎች ላይ ግን በጀታቸውን እየቀነሱ ነው” ብለዋል።
የወታደራዊ ወጪዎች መጨመርና የጤና በጀት መሳሳት፣ ዓለም እንደ ኮቪድ-19 ያሉ የወደፊት ወረርሽኞችን ለመቋቋም ያላትን ዝግጁነት በእጅጉ እንደሚቀንሰው ተገልጿል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አክለውም፣ ጤና እንደ ወጪ ሳይሆን እንደ መሠረታዊ የልማትና የሰላም ኢንቨስትመንት መታየት እንዳለበት አሳስበዋል።
“ጦርነት መፍትሔ አይደለም፤ መፍትሔው ሰላም፣ ዲፕሎማሲና በሰው ልጅ ደኅንነት ላይ ማተኮር ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ የዶ/ር ቴዎድሮስ ማሳሰቢያ የመጣው፣ በርካታ አገራት በመከላከያ በጀታቸው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እያደረጉ ባለበትና በሌላ በኩል ደግሞ ለዓለማቀፍ የጤና ዕርዳታ የሚመድቡት የገንዘብ መጠን እየቀነሰ በመጣበት ወቅት ነው።
