በማዕቀቡ 60 የሩሲያ ድርጅቶችና 73 ግለሰቦች ተካትተዋል
የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፣ ዛሬ በቴሌግራም ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መረጃ፣ በሩሲያ ላይ አዲስና ጠንካራ ማእቀብ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ማእቀቡ የሩሲያን የፋይናንስ ገቢ የሚያሽመደምድ ነው›› ያሉት ዘለንስኪ፤ ከእነዚህ ውስጥ በሩሲያ መንግስት የሚንቀሳቀስ የክሪፕቶ ከረንሲ እንደሚገኝበትም ገልፀዋል፡፡
በዛሬው ማእቀብ 60 የሩሲያ ድርጅቶችና 73 ግለሰቦች መካተታቸውንም አስረድተዋል፡፡
‹‹የሩሲያን ወታደራዊ ኢንዱስትሪ አቅም በዚህ መልኩ እንዲገደብ ካደረግነው ሩሲያ ይህንን ጦርነት እንድታቆም ማስገደድ እንችላለን›› ያሉት ዘለንስኪ፤ በሚቀጥለው ሳምንት በአውሮፓ ህብረት ሊወጣ የሚችለውን የሩሲያ ማእቀብንም በዩክሬይን ውስጥ ተግባራዊ እንደሚያደርጉት አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት እስካሁን 17 ጊዜ በሩሲያ ላይ ማእቀብ መጣሉ ይታወቃል፡፡ ለ18ኛ ጊዜ በሩሲያ ላይ የሚጥለውን ማእቀብ በተመለከተ በተደረገው ምክክር ስሎቫኪያ ተቃውሞ በማሰማቷ በድጋሚ ለመምከር ለሚቀጥለው ሳምንት ሌላ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል፡፡
የስሎቫኪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በሚቀጥለው ሳምንትም 18ኛው ማእቀብ ላይ እንደማይስማማ በመግለፅ ላይ ነው፡፡
(ዘ-ሐበሻ ዜና)
