Home ዜና የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉ ታወቀ

የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉ ታወቀ

የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉ ታወቀ

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
መጋቢት 19/2017 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በዛይሴ ወዘቃ፣ ፃናኦ ቀበሌ በግለሰብ ቤት ላይ በተፈፀመ የቤት ማቃጠል ጥቃት ቤት ንብረት መውደሙ እና የሁለት ህፃናት ህይወት ማለፉን ለማወቅ ችለናል፡፡


በዚህ አሰቃቂ ሕገወጥ ድርጊት ድርጅታችን ኢዜማ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ የክልሉ መንግስት ድርጊቱን የፈፀሙትን አካላት ሕጋዊውን መንገድ ተከትሎ እንዲያጣራ እና በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን፡፡ከዚህ አሳፋሪ እና አስነዋሪ ተግባር ጀርባ ያለ የትኛውም አካል ቢሆን በጋራ ሊወገዝ የሚገባው መሆኑንም ኢዜማ በፅኑ ያምናል።


ይህን በጭካኔ የተሞላ አስነዋሪ ድርጊት ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች እና የመንግስት አካላት የድርጅታችንን ስም አላግባብ እያነሱ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡ ይህን መሰል ስም ማጥፋት በቸልታ የማናየው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ኢዜማ በእንደዚህ አይነት ሕገወጥ ተግባር ውስጥ የማይገኝ ብሎም ከቆመለት የሰላማዊ ትግል መርሆ ውጪ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡


ሳናነሳ የማናልፈው ጉዳይ ቢኖር ወንጀል የፈፀሙ አካላትን ለፍርድ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ከዚህ በፊት የተስተዋሉ አይነት የፖለቲካ ልዩነትን መሰረት ያደረጉ ንፁሐንን ከአጥፊዎች ያለየ የጅምላ እስርና ህገወጥ አፈና እንዳይኖር የህግ አስከባሪ አካላትም ሕግና ሕግን ብቻ መሰረት አድርገው እንዲሰሩ በአፅንኦት ለማሳሰብ እንወዳለን ፡፡
ስለሆነም ይህን አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ አካላት በአስቸኳይ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ የፀጥታ አካላትም የደረሱበትን ግኝት ደረጃ በደረጃ ለሕብረተሰቡ እንዲያሳውቁ እየጠየቅን ኢዜማም ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እንደሚከታተል ለማሳወቅ እንወዳለን።


በተፈፀመው ሕገወጥ እና በጭካኔ ለተሞላ አስነዋሪ ተግባር ቤት ንብረታቸውን እና ህፃናት ልጆቻቸውን ላጡ ቤተሰብ፣ ወዳጅ እና ዘመድ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
መጋቢት 22/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ