የየመን ሁቲዎች ከእስራኤል ወደቦች ጋር ስምምነት ያለው የትኛውም መርከብ እንደሚመታ አስጠነቀቁ።
”የየትኛውም ኩባንያ መርከብ በየትኛውም አገር ሰንደቅ ዓላማ ስም ይንቀሳቀስ ዒላማ ይሆናል” በሚል ዝተዋል።
ሁቲዎች ወደ 4ኛው ምዕራፍ የእስራኤል የባህር እንቅስቃሴን መዝጋት እርምጃ እንደሚገቡ በወታደራዊ ቃል አቀባያቸው ያህያ ሳሬ በኩል ይፋ አድርገዋል።
የሁቲ ሀይል የጦር መሳሪያ መድረስ በሚችልበት ቦታ ሁሉ መርከቦቹ ይመታሉ ነው ጥቅል ሀሳቡ።
እሁድ አመሻሹን መግለጫ የሰጠው ሁቲ አሁንም ለፍልስጤማውያን ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚገፋበት ግልጽ አድርጓል።
ከቴል አቪቭ ጋር ስምምነት ያለው መርከብ ሁሉ ዒላማ እንደሚደረግ አንስራላሆች አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በቀይ ባህር እና ህንድ ውቅያኖስ በኩል በተለይም በበብ-ኤል መንደብ ሰርጥ መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ አድርገው መሰንበታቸውም አይዘነጋም።
በዓመት ከ1 ትሪሊዬን ዶላር በላይ ምርት ይተላለፍበታል በሚባለው ቀጠና ላይ ከባድ ጫና ሲያሳድሩም ቆይተዋል።
የመርከቦችን ጉዞም በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ደቡባዊ አፍሪካ ጫፍ እንዲሆን በማስገደድ የቀይ ባህርን የንግድ ታሪክ 155 ዓመታት ወደ ኋላ መልሰውታል።
