የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ሕክምና ሳይደረግ የተደፈነ የልብ ቧንቧን ለማከም የሚያገለግለው ‘ካትላቭ’ የተሰኘ መሣሪያ ከፍተኛ የጥገና ወጪ መጠየቁ ህክምናው ላይ እንቅፋት እንደፈጠረ አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብርሃኑ ሰንደቅ እንደገለጹት፣ ለጥገና የሚሆኑ ግብዓቶች ከውጭ ሀገር የሚመጡ እና ዋጋቸውም ውድ በመሆኑ ብልሽት ሲያጋጥም በወቅቱ ለማስተካከል አዳጋች ሆኗል።
በሆስፒታሉ ያሉት የ‘ካትላቭ’ መሣሪያዎች ሁለት ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ብርሃኑ፣ መሣሪያዎቹ አልፎ አልፎ ጥገና እንደሚፈልጉና ተጠግነው ወደ ሥራ የሚገቡበት አጋጣሚም እንዳለ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ ከብልሽት ጎን ለጎን በ2018 የበጀት ዓመት ‘ኸርትአታክ ኢትዮጵያ’ ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ የተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር መሣሪያዎቹ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ለ94 ሰዎች የልብ ሕክምና መስጠቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል።
ዶክተር ብርሃኑ አክለው እንደገለጹት፣ የመሣሪያ አቅርቦቱን ለማሻሻል እና የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግ ከተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እየተሠራ ነው።
ለአሐዱ ሬድዮ
