የመንግሥት ነገር አሁንም እንቆቅልሽ ነውን?!

Date:

የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናዢ ከቀናት በፊት በቲውተር ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ማስታወሻ እንዲህ አሉ፡- “ለመኾኑ በኢትዮጵያ አወዛጋቢ ከመኾን የተረፈ ጉዳይ አለ? ብሔር፣ ሃይማኖት፣ አሁን ደግሞ አንጸባራቂው ታሪካዊ ኹነት ፤ የዓድዋ ድል፡፡ የከበረ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር አሁን ላይ ራሷን ለመከፋፈል አዳዲስ መንገዶች ፍለጋ ላይ ትመሥላለች”                 

ዝክረ ዓድዋ 127 ባሳለፍነው ሳምንት ተከብሮ አልፏል፡፡ አማናዊው የሶሎዳ ተራራ ዛሬም “ከነዓን” የኾነበት መንግሥትም ክብረ በዓሉን ከሕዝብ ጋር በመጋፋት አሳልፏል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓድዋ ድል ብሔራዊ የመከበሪያ ሥፍራን አስመልክቶ ሞቅ በረድ ያለ ክርክር ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ይኽ ክርክር “ሁለት” መልክ እና “ሁለት” ቅርጽ የነበረው ነው፡፡ አንደኛው ባለሁለት መልክ ክርክር “ዐዲስ አበባ ወይስ ዓድዋ?” በሚለው ነጥብ ላይ የሚሽከረከር ነው፡፡ የቱንም ያህል ንዑስ ቄሳራዊ መንፈሶች ባያጣም በስፋት ግን ለበዓሉ ከፍታ ከመቅናት የሚመነጭ መከራከሪያ ነው፡፡ በተለይ “ዓድዋ ላይ ይከበር” የሚለው ድምጽ ከቦታው አማናዊ እና ታሪካዊነት በመነጨ ስሜት የሚቀርብ መከራከሪያ ከመኾኑ በላይ፣ ያለፉትን አምስት እና ስድስት ዓመታት የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ድሉን በሥፍራው በመገኘት የማክበር ተከታታይ ልማዶች አባሪ ኾነው የሚጠቀሱለት ነው፡፡

በአንጻሩ በዓሉ መከበር ያለበት ዐዲስ አበባ ላይ ነው የሚለው መከራከሪያም እንዲሁ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት እና ሥርዓተ መንግሥታት (እንደ ሃምሳኛ እና መቶኛ ዓመት ካሉ ወሳኝ ኢዮቤልዮዎች ውጪ) ነገሥታት እና ፕሬዝዳንቶች ዐዲስ አበባ ምኒልክ ዐደባባይ ሲያከብሩ የመቆየታቸውን አስረጂ ያቀርባሉ፡፡ በርግጥ የዓድዋ በዓል ትንሣኤ ካገኘበት ያለፉት ጥቂት ዓመታት በፊት በዐዲስ አበባ ደረጃም ቢኾን በከንቲባ አንዳንዴም በም/ቤት አፈጉባኤ ደረጃ ወርዶ ይከበር የነበረበት የታሪክ ኹነት ክሱት ኾኖ አልፏል፡፡

ሁለተኛው የዓድዋን ማክበሪያ ሥፍራ አስመልክቶ አሁን አሁን በስፋት የሚታየው የቅርጽ ልዩነት ግን ከፍ ብለን ካነሳነው መከራከሪያ ለየት የሚል ነው፡፡ ይኽውም በዓሉ በዐዲስ አበባ ደረጃ ከመከበሩ ይልቅ “የት መከበር አለበት?” የሚለው ጥያቄ ግዘፍ የነሳበት ኾኖ ይገኛል፡፡ ምናልባትም በያዝነው ዓመት መንግሥት ዓድዋን ከሕዝብ ጋር በማክበር ሳይኾን በመጋፋት በታሪካዊው ዕለት እንግዳ ክስተት እንዲፈጠር ያደረገው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በተለይም ምኒልክ ዐደባባይ ላይ ሱታፌ ሕዝብ ባለበት እንዳይከበር እንደ ብዙዎች ዕምነት “የጥቁር ጥልያኖች”ን ሚና እስከመጫወት የደረሰበት እልህ ከዚህ የሚመነጭ ምሥጢር አለው፡፡

“የድሉ ሕጋዊ ወራሽ መከላከያ ነው” የሚለውን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን መግለጫ በውርስ ሕጉ መሠረት በደንብ እንመርምረው ብለን ብናልፈው እንኳን ከምኒልክ ዐደባባይ በኋላ “ሰፋ ባለ ትርዒት እና ሥነ ሥርዓት መስቀል ዐደባባይ ላይ” እንዲከበር መደረጉ የሚያስከፋ ባልኾነ ነበር፡፡ ኾኖም ድሉም በዓሉም የሕዝብ መኾኑን ፍጹም በዘነጋ ሁኔታ የነጻነት ድሉን በነጻነት እንዳያከብር ሞትን እስከማስከተል የደረሰ እርምጃ ሕዝብ ላይ መወሰዱ፣ ከማስደንገጥ በላይ ነገሩን በተለየ መልኩ ለመመልከት የሚያስገድድ ነው፡፡ በተለይም የምኒልክ ዐደባባይ እና የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በዓድዋ ላይ የነበራቸውን ግንኙነት ባላማከለ ሁኔታ በቤተክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ካህናት እና ምዕመናን ላይ ጭምር በድፈረት የተወረወረው ፍላጻ እንዲህ በቀላል አንድምታ የሚታለፍ ሊኾን አይችልም፡፡

ሰላም እና እፎይታ እንደ ውሃ የጠማት ሀገር፣ እንዲህ ያለ ዓይን ያፈጠጠ ነውጥን በዐደባባይ የሚጠምቅላት መንግሥት መኖሩ ደግሞ ከኾነው በላይ ሊኾን የታሰበውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ጊዜ አያሰጥም፡፡ ለመኾኑ እንቅቆልሹ ምንድነው? ይኽ ከተላላ አእምሮ የሚነቃ ጥያቄ አይደለም፡፡ ነጠብጣቡን ገጣጥሞ አንዳች ሥዕል ማግኘት ዳገት የኾነበት ባለአእምሮ ጥያቄም አይደለም፡፡ ጥያቄውን እንቆቅልሽ ያደረገው በዚህ መንገድ ሀገር ትኖራለች የሚል ዕምነት ያለው መንግሥት በሀገሩ ላይ መኖሩ ነው፡፡            

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ...

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...