የሸኔ እና የገደብ ከተማ ነዋሪዎች ትንቅንቅ!

Date:

ሲሳይ ማሞ (ከጌዴኦ)

የጠ/ሚ ዐቢይ መንግሥት ከባዕድ ሀገር ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው ከነጠብ-መንጃ ትጥቃቸው በአንቀልባ ታዝለው እና ጉሮ ወሸባዬ እየተጨፈረላቸው ወደ ሀገራችን ገብተው በኢትዮጵያውያን ላይ ጣርና መከራ፣ ግድያና አፈና፣ እልቂትና ፍጅት፣ ስቃይና እንግልት፣ እገታና ሽብር እንዲፈጽሙ መንገድ ከሰጣቸው አሸባሪ ኃይሎች መካከል በዳቦ ሥሙ “ኦነግ ሸኔ” የሚባለው ኃይል ዋነኛው ነው፡፡ ይኽ ቡድን ላለፉት አራት ዓመታት በምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና የማስልጠኛ ካምፑን ገንብቶ በዙርያው ላሉ ከተሞችና መንደሮች የመከራ ምንጭ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩም በአንድም ኾነ በሌላ ከዚህ በፊት በወጡ የሕትመት ውጤቶችና በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገር የቆየ ቢሆንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላትም ኾኑ የክልሉ መንግሥት የሚገባውን ትኩረት ሊሰጠው ባለመቻሉ መከራው በቅርጽ በዐይነት ሊሰፋ ችሏል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት አሸባሪውን ኃይል አስመልክቶ ‹‹በጉጅ ዞን ይሄን ያህል ደመስሰን፣ ይህን ያህል የሚኾኑት እጅ ሰጡ፣ ይህን ያህል ደግሞ ተማረኩ፣ ይኽን ያህል ቁጥር ባላቸው ላይ እርምጃ ወሰደንባቸዋል›› በማለት የመግለጫ ጋጋታ ሲያሰማ እንጂ ቡድኑን ከሥሩ ለማጥፋትም ኾነ ዕለት ዕለት የመከራ ሕይወትን ለመኖር የተፈረደባቸውን በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰላም እስትንፋስ እንዲተነፍሱ ሲሰራ አይታይም፡፡

ለዚህም ይመስላል ባለፉት ዓመታት የነበረው የመከራ ጅራፍ አልበቃ ብሎ አሁንም ይኼው አሸባሪ ቡድን የጥፋት በትሩን ይዞ በዚሁ ባሳለፍነዉ ወር ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ዕለተ ረቡዕ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌደኦ ዞን ገደብ ወረዳ ፊቱን አዙሮ ሌላ ግፍ የፈጸመው፡፡ ነገሩ የኾነው እንዲህ ነው፡-

ጥር 20 የሚከበረዉን የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ “ዳራሮ” በዓል ለማከበር የጌደኦ ዞን ዋና መቀመጫ ዲላ ከተማ እጅግ አሸብርቃለች፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ በሚመጡ እንግዶችም ደምቃለች፡፡ ገደብ ከተማም በአቅሟ በዓሉን ለማክበር ከሞያሌ እስከ ገርባ ካለው መሥመር ወደዋና ከተማው በበዓሉ ላይ ለመታደም የሚመጡትን ኢትዮጵያውያን ሁለት እጆቿዋን ዘርግታ “አሻማ ባጋ ናገኢክ ዳግነን” (Ashshamma baga nageik dagineen) እያለች ስትቀበል አርፍዳ ውላለች፡፡ እነኾ እንግዳ በመቀበል የተደከመበት ቀን መሸ፡፡ ሁሉም ነዋሪ ወደየቤቱ ከተተ፡፡ ዳሩ ግን እንግዳን በፈገግታ የተቀበለው ሕዝብ የሰላም እንቅልፍ ተኝቶ እንዲያድር አልተፈቀደለትም፡፡ ልክ እኩል ሌሊት ሲደርስ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡፡ ከሰማይ የወረደ መብረቅ እስኪመስል ድረስ የጥይት ዕሩምታ በገደብ ከተማ ላይ ዘነበ ፤ ያለማቋረጥ ተርከፈከፈ፡፡ ክላሽ፣ ስናይፐር፣ ብሬን፣ ድሽቃ በየዐይነቱ ተንጣጣ፡፡ ገደብ በአንድ ጊዜ ተናወጠች፡፡ “የምን መብረቅ ነው? ምንድነዉ እየሆነ ያለዉ?” በድካም የዋለው ሕዝብ ግራ በመጋባት ጠየቀ፡፡

አሸባሪው ኃይል ግን ይህን የጥይት እሩምታ ከማዝነቡ ቀደም ብሎ የኔትዎርክ መስመሩን በመበጣጠስ እና መብራት በመቁረጥ የፀጥታ አካላት እንዳይናበቡ አድርጎ ስለነበር ነገሩ ሁሉ የእውር ድንብር ሩጫ ኾነ፡፡ ለ2 ሰዓት ተኩል ያህል ማለትም ከሌሊቱ 6፡00-8፡30 የቆየው የኔትወርክና መብራት መቆራረጥም ለቡድኑ ምቹ ዕድል ፈጥሮለት ያሻውን ለማድረግ ሞከረ፡፡ በዚህ 2 ሰዓት ተኩል ቆይታው 6 ባንኮችን ከመሰባበር ጀምሮ፣ 1 ፖሊስ ጣቢያ፣ 1 ጤና ጽ/ቤት፣ 1 አምቡላሰንስ፣ 1 የዕርሻና ተፈጥሮ ላንድኩሩዘር፣ 6 ሞተር ሳይክል አቃጥሏል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ 9 ክላሽ በመዝረፍ በከተማዋ የሚገኙ ሞባይል ሱቆችን በመስባበር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሞባይል ስልኮችን በመዝረፍ እና 4 ንጽሃን ዜጎችንና 1 ፖሊስ በመግደል በብዙኃንም ላይ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ አቅዶ የመጣበትን የመግደል፣ የመዝረፍ እና ንብረት የማውደም ግብ አሳካ፡፡

ይህን ሁሉ የሰው ሕይወት ለመቅጠፍና ሃብት ንብረት ለማውደም ወደ ገደብ ከተማ የገባው አሸባሪ ቡድን ግን ዓላማው ይኽ ብቻ አልነበረም፡፡ የኔትዎርክ መስመር ከመቆራረጥና መብራት ከማጥፋት ባሻገር የገደብ ከተማ ከንቲባ አጠቃላይ የከተማ ካብኔ አባላትን፣ የ6 ባንኮች ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ፣ ዳሽን፣ ንብ፣ ኦሮሚያ ሕብረት ሥራ፣ አቢሲኒያ ካሻሮቻቸውን እንዲሁም በዐጼ ኃይለሥላሴ፣ በደርግም ሆነ በኢሕ.አ.ዴ.ግ በጦር ሜዳ ቆይተዉ የመጡ ጀግኖች አርበኞች አባቶችን መኖርያ ቤት ድረስ በመሄድ ስናይፐር በመደቀን ሕይወታቸውን ለመቅጠፍ እና ሚስቶቻቸዉንና ልጆቻቸዉን ለመድፈር፤ ሃብት ንብረታቸዉን ለመዝረፍ ጭምር ነበር፡፡ ዳሩ ግን አቅደውና አልመው እንደሄዱት አልተሳካላቸውም፡፡ ሕዝብን የሚያገለግሉ ቅን አመራሮች እና የሕዝቡን ምሥኪንነት ተመልክቶ አምላክ ከባሰ መከራ ታደጋቸው፡፡

በሰላሙ ጊዜ አራሽ በችግሩ ጊዜ ተኳሽ የሆነዉ የገደብ ሕዝብም፣ በከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ከስድስቱ ባንኮች ጥበቃዎች ጋር በጥንቱ ኢትዮጵያዊ ወኔ እና ከዚህም ከዛም በአንድነት ጩኸት በማስተጋባት፣ ሁሉም በቤቱ ያለውን ሕጋዊ የጦር መሳርያ ይዞ በመውጣት እና ወደ ሁሉም አቅጣጫ በመተኮስ ከተማዋን ምድራዊ ገሃነም ለማደረግ የመጡትን የሸኔ አሸባሪ አባላት በአጭር ሰዓታት ውስጥ፣ “ቦንቱ” የምትባለዋን ታጠቂ ግንባሯን፣ ሌሎቹንም አካላቸውን አጉድለው፣ ከተማዋን አመድ ለማድረግ የመጣውን ቡድን እግሬ አውጪኝ ብሎ እንዲጠፋ አድርገውታል፡፡ ክብር ለገደብ ከተማ ሕዝብ!

በእርግጥ ሸኔነት ገዳይነት፣ ሕጻናት አራጅነት፣ ሴቶችን ደፋሪነት፣ ንብረት አውዳሚነት፣ ፀረ ኢትዮጵያዊነት እና አሸባሪነት ማለት እንደኾነ፣ አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደርኩ ነኝ ከሚለው መንግሥት ከሰማን ውለን አድረናል፡፡ መንግሥትም ኾነ ይኽንን አሸባሪ ኃይል በጉያው ያቀፈው የኦሮሚያ ክልል ግን ለችግሩ መፍትሔ መሥጠት አልፈለገም፡፡ ከገደብ ከተማ 20 ኪ.ሜ ርቀት የምትገኘው በም/ጉ/ዞን ቡሌ-ሆራ ወረዳ ሥራ ያለችው ገርባ ከተማም በ2013 ዓ/ም ላይ የአሸባሪው ሸኔ በትር ከቀመሱት ከተሞች አንዷ ነበረች፡፡ በዚህች በገርባ ቀበሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገርባ አኖ ቅርጫፍ በሸኔ ዲሽቃና ስናይፐር ወድሞ ከተዘረፈም ድፍን 3 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

በዚህ ባንክ ዘረፋና ውድመት ሳቢያም ዳግም የባንክ አገልግሎት ባለመጀመሩ በገርባ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ቡሌ-ሆራ 20 ኪ.ሜ አልያም ወደ ገርባ 20 ኪ.ሜ በመጓዝ ነበር ላለፉት 3 ዓመታት አገልግሎት ሲያገኙ የከረሙት፡፡ ለትራንስፖርት ቀላል የማይባል ወጪ እየከፈሉ የባንክ አገልግሎት የማግኘት ችግራቸው እስከዛሬ መፍትሔ ባለማግኘቱም እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በዚህ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡

ሃይ ባይ የሌላቸውና ትጥቅና ስንቅ አቀባይ ያላቸው እነኚህ ቡድኖች በኃይላቸውና በሥልጣናቸው መሠረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶችን አውድመው ሦስት ያህል ዓመታት እንዳንከራተቱት የገርባ ሕዝብ ለማድረግ፣ እንኾ ጌደኦ ዞን ገደብ ከተማ ገብተው ስድስት ባንኮችን ሰባብረው አዘግተዋል፡፡ በገደብ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ልክ እንደ ገርባ ወንድሞቻቸው ወደ ይርጋጨፌ ወረዳ 40 ኪ.ሜ፣ ወደ ጉጂ ዞን ቡሌ-ሆራ ወረዳ 40 ኪ.ሜ እየተጓዙ ለመጠቀም ተገድደዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈፀም አሸባሪ ብሎ የፈረጀው የፈደራሉ መንግሥት ከዝምታ ባለፈ ምንም እርምጃ ሲወስድ አይታይም፡፡ ይህን ያህል የሰው ሕይወት ጠፍቶ፣ ይኼን የሚያህሉ ባንኮች ተሰብረው እና ፖሊስ ጣቢያዎች ተቃጥለው ብሎም እሥረኞች ተበትነው ባለባት ከተማ መንግሥት መከላከያን አለማስገባቱና፤ ከጠላት ቀጠናነት ነፃ ወጥቶ አካባቢው የሰላም እስትንፋስ እንዲተነፈስ አለመስራቱ ለዜጎች ያለውን ዝቅተኛ ግምት የሚያሳይና የጥፋት ኃይሉ እንዲጠፋ የማይፈልግ መኾኑንም አረጋግጧል፡፡

አሁንም ቢኾን አካባቢው የሥጋት ቀጠና እንደመሆኑ መጠን መከላከያ ገብቶ ሳይቀደም ቀድሞ ኦፕሬሽን በመሥራትና ሥጋቱን በጥልቀት በመመርመር የሕግ የበላይነት በማስከበር ለሕዝብ ሰላም ዘብ መቆምና ዜጎችን ከአሸባሪው ኃይል መታደግ አለበት፡፡ መከላከያ አካባቢውን እንዲቆጣጠር፤ ባንኮች እንዲከፈቱ፤ የዜጎች እንግልትና ሥቃይ እንዲያበቃ፤ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የሕዝቦች ደህንነት እንዲጠበቅም ማኅበረሰቡ አስቸኳይ ጥሪውን ማቅረብ ይወዳል፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...