Home ብዝሃ ሃይማኖት የትንሳኤው ትርጉም ትንሳኤ ለሚያስፈልጋት ሀገር

የትንሳኤው ትርጉም ትንሳኤ ለሚያስፈልጋት ሀገር

የትንሳኤው ትርጉም ትንሳኤ ለሚያስፈልጋት ሀገር

በጸሐፌ ትእዛዝ ታዴዎስ ግርማ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች፡፡

ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ፤ ታመመ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን የጌታችንና የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡ በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳም እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺህ አምስት መቶ የመከራ፣ የፍዳና የኩነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡ እንደዚሁም ይህ ሳምንት ቅዱስ ሳምንት ይባላል” ከሌሎች ሳምንቶች ሁሉ የተለየ የከበረ ነውና፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹም ፍቅር የተከፈለ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ ተሠራበት፣ የሰው ልጆች ደኅንነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኀኔዓለም ስለ እኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለ ካሠልን “ቅዱስ ሳምንት” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የመጨረሻ ሳምንት ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት ምንድነው ስንል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፣ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፣ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ሰሞነ ህማማት የታመመች ሀገር ፈውስ የምታገኝበት ወቅት ነበር ምን ዋጋ አለው ሀኪሙም ታማሚውም በዚህ ዘመን ሁሉም ታሟል:: ታማሚዋ ሀገር በዘረኝነት በሽታ አልጋ ከያዘች ከራረመች ማን ይፈውሳት? የእምነት ተቋማት? መንግስት? ሁሉም ታመዋል፡፡ ሰው ሲታመም ወደ ጤና ባለ ሙያ ይሄዳል ከባለ ሙያውም ምክር መድሃኒት ይታዘዝለታል:: ትእዛዙን ጠብቆ ተጠንቅቆ መድሃኒቱን ከወሰደ ይድናል:: እኛ የታመመች ሀገራችንን የትኛው ዶክተር ጋ ሄደን ምን መድሀኒት በጥብጠን አጠጥተን እንደምናድናት ግራ የገባ ጊዜ፡፡ሁሉም ይህችን ሀገር ለማዳን ዶክተሯ እኔነኝ አውቅላታለሁ እፈውሳታለሁ ባዩ በዛባት ዶክተር ሲበዛ በሽተኛ የሞታል ሆነና ነገሩ የሀገሬ ህመሟ ጸና፡፡ የታመመች ሀገር በሰሞነ ህማማት ካልተፈወሰች መቼቼቼቼ

የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች

  1. አለመሳሳም፡ በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንስቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡
  2. ሕፅበተ እግር፡ ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡
  3. አክፍሎት፡ በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
  4. ጉልባን እና ቄጠማ፡ ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡
  5. ጥብጠባ፡በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡
  6. ቄጠማ(ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ ‘’ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ሰሞነ ህማማቱ ሲፈጸም ትልቁን በአል ትንሳኤውን እናከብራለን ትንሳኤ ማለት ተንሥአ ካለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም መነሣት አነሣሥ ማለት ነው።”ትንሳኤ ማለት መነሳት፡መቆም፡ማለት ነዉ፡፡ እስራኤል ዘስጋ ያከብሩት የነበረው በዓለ ፋሲካ ከባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር ። የሐዲስ ኪዳን በዓለ ትንሣኤ ግን እሥራኤል ዘነፍስ ወደ ከኃጢአት ጽድቅ የተመለስንበት ከሐሳር ወደ ክብር ከአሮጌው ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነጻነትበዓል ነው ።ፋሲካ በዐረብኛ ፓስኻ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ማዕዶት መሸጋገሪያ ማለትነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በቀደምት ነቢያት የተነገሩና የተጻፉ አንቀጾች ብዙ ናቸው፡፡ የሞቱና የትንሣኤ ምሥጢር በቅዱሳን መጻሕፍት ሰፊ ቦታ ያለው ነው፡፡ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚነገረው ሞትና ትንሣኤ ከቅርቡ /ከመስቀሉ አካባቢ/ በመነሣት እሱ ራሱ መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥርዓተ ቊርባንን በሠራበት ምሽት የሞቱንና ትንሣኤውን ነገር አንሥቶ ለደቀ መዛሙርቱ በሰፊው ገልጿል፡፡ “በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛለችሁ መጽሐፍ እረኛው ይመታል የመንጋው በጎች ይበተናሉ ያለው ይፈጸማል” ብሎ ነግሮአቸዋል፡፡

ከዚህም ቀደም ብሎ በጉባኤው ይሰበሰብ ለነበረው ሕዝብ ዮናስ በከርሠ አንበሪ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት እንደኖረ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ያድራል፡፡ ነገር ግን ወደገሊላ እቀድማችኋለሁ እያለ ይነግራቸው፥ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ማቴ ፲፪፥፵፣ ፳፯፥፴፩ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሱ በተጻፈው መሠረት የመስቀልን ፀዋትወ መከራ ተቀብሎ በመስቀል ላይ ሞቶ፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሙታንን በሞቱ ሕያዋን ያደርጋቸው ዘንድ ሞተ፡፡ በዕለተ ዓርብ የፈጠረውን አዳም በፈጸመው በደል ከተፈረደበት የሞት ፍርድ ነፃ ይሆን ዘንድ፥ በባሕርዩ ሞት የሌለበት አምላክ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ዋለ፡፡ ወዳጆቹ የአርማትያሱ ዮሴፍና፥ አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ የሄደው ኒቆዲሞስ በመስቀል ላይ የዋለውን ሥጋውን አውርደው፥ ለመቅበር፤ ከገዥው ከጲላጦስ ለምነው እንዲቀብሩ ተፈቅደላቸው፡፡ ከምሽትም ከመስቀሉ አወረዱት እንደቤተ አይሁድ የአቀባበር ሥርዓትና ልማድ የደቀቀና መዓዛው የጣፈጠ ሽቱ አዘጋጅተው፥ ከጥሩ ሐር በተሠራ በፍታ ገንዘው ዮሴፍ ለራሱ አስወቅሮ ባሳነፀው አዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ታላቅ ድንጋይም አገላብጠው ገጠሙት ማቴ 27፥57‐58፣ ዮሐ19፥38‐42 ይህ ሁሉ ለአይሁድ ሊቃናትና ሕዝብ ደስ የሚያሰኝ አልበረም፡፡

ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደረገው ጥንቃቄና የሚሰጠው ክብር ሁሉ፥ በነሱ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ “ያ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ብሏልና ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት ሰርቀው፥ ወስደው ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብለው ሕዝቡን እንዳያስቱ መቃብሩ ይጠበቅ” በማለት ወስነው ነበር፡፡ በእያንዳንዱ አራት አባል የሚገኝበት በሦስት ፈረቃ የሚጠብቅ የጭፍራ ቡድን ተመድቦ መቃብሩን በንቃትና በጥንቃቄ እንዲጠብቅ ተደርጓል፡፡ ባለሥልጣኖችም ጭፍራው ባለበት መቃብሩን አስቆልፈው በየቀለበታቸው (ማኅተማቸው) አትመውት ነበር፡፡ ማቴ 27፥62-66 ይህ ሁሉ በሚፈጸምበት ዕለትና ጊዜ እነማርያም መግደላዊት፣ ማርያም ባወፍልያና እና ሰሎሜ ከእግረ መስቀሉ ሳይለዩ ከመቃብሩ ፊት ለፊት ቆመው በኀዘን፣ በተሰበረ መንፈስ የነገሩን ፍጻሜ የሚመለከቱ የዓይን ምስክሮች ነበሩ፡፡ ማቴ 27፥61 ይሁን እንጂ ሰውን ለመዳን በፈቃዱ ባደረገው የቸርነት ሥራ፥ በሥጋ ቢሞትም በባሕርዩ ሞት የሌለበትን ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው ሊያስቀሩት የማይቻላቸው በመሆኑ፤ ኃጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን ደምስሶ፥ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ሳይል በሦስተኛው ቀን በሌሊተ እሑድ ከሞት ተነሥቷል፡፡

በመቃብሩ ላይ ተገጥሞ የነበረው ታላቅ ድንጋይ ተገለባብጦ የተጠቀለለበት የከፈን ጨርቅ በአፈ መቃብሩ ተቀምጦ ተገኝቷል፡፡ የአይሁድ ጎመድ ሁሉ አልነበረም፡፡ ለጥበቃ ተመርጠው ልዩ መመሪያና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸው የነበሩ ጭፍሮችም ራሳቸውን እንኳ መጠበቅ ተስኗአቸው በያሉበት ወድቀው እንደ በድን ሆነው ነበር፡፡ ትንሣኤውን ለማየት ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ያነጉት ቅዱሳት አንስት ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ለማየት ቀዳሚ ዕድል ነበራቸው፡፡ አስቀድማ ለማየት የበቃችው ማርያም መግደላዊት መሆኗን ቅዱስ ወንጌል አስቀምጦታል፡፡ ከሷ በማስከተል፥ ሁሉም ሴቶች አይተዋል፡፡ ጌታችን በተነሣ ጊዜ፥ መልአኩ እንደ ፀሐይ በሚያበራልብስ እንደ በረዶ በነጣ ግርማ ርእየቱ በሚያሰፈራ ሁኔታ ተገልጦ ነበር፡፡ ሴቶቹንም“አይዞአችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ ዐውቃለሁ፤ እሱ ከዚህ የለም እንሣለሁ እንዳለ ተነሥቷል፡፡ ነገር ግን ኑ የተቀበረበትን ቦታ እዩ ካያችሁም በኋላ ፈጥናችሁ ሄዳችሁ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው በገሊላ ይቀድማችኋል (መታየትን ይጀምርላችኋል) በገሊላ ታዩታላችሁ” ብሎአቸው፥ ወደመቃብሩ እየመራ ወሰዳቸው፡፡ ሴቶችም ፍርሃትና ድንጋጤ በተቀላቀለበት የደስታ መንፈስ ተውጠው ወደ መቃብሩ ሄዱ፡፡ ፍርሃት የእግዚአብሔርን መልአክ ማየታቸው፤ ደስታው ደግሞ፥ ትንሣኤውን መስማታቸው ነው፡፡

በደስታ ተሞልተው ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ነግረው፥ እየተቻኮሉ ሲሄዱ ጌታችንን በመንገድ ተገለጠላቸው፡፡ “እንዴት ሰነበታችሁ! አስታረቅኋችሁ” አላቸው፡፡ ቀርበውም ሰገዱለት፤ እሱም አይዞአችሁ  አትፍሩ፤ ሂዱ፤ ለወንድሞቻችሁ ገሊላ ይሂዱ ዘንድ ንገሩአቸው በዚያ ያዩኛል” አላቸው፡፡ ዐሥራ አንዱ ሐዋርያትም ዜናውን ሰምተው ወደተባሉበት ቦታ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡ በዚያም ጌታችንን ከሙታን ተነሥቶ አዩት፤ ሰገዱለትም፡፡ ማቴ ፳፰፣ ማር ፲፮፡፩‐፲፪፣ ሉቃ ፳፥፲፪ ለፍቅሩ ይሳሱ፥ ይናደዱ የነበሩ ጴጥሮስና ዮሐንሰም በጊዜው ወደ መቃብሩ ሄደው መነሣቱን አረጋገጡ፡፡ ዮሐ፳፥፩‐፲፩፣ ፲፰ የክርስቶስ ትንሣኤ በስሙ ላመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስ ለሙታን ሁሉ በኲር ሆኖ ተነሥቶአል፡፡ የሙታንን ሁሉ መነሣት የሚያረጋግጥልን የጌታ ትንሣኤ ነው፡፡ የክርስቶስም ትንሣኤ መርገመ ሥጋ፥ መርገመ ነፍስ፤ ሞተ ሥጋ፥ ሞተ ነፍስ የተሻረበት ርደተ ገሃነም ጠፍቶ፥ በአዳም የተፈረደው ፍርድ ሁሉ ተደምስሶ፤ ፍጹም ነፃነት፣ የማይለወጥ ደስታ፣ የተገኝበት ስለሆነ ፋሲካ ይባላል፡፡ ፋሲካ ደስታ ነው እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነፃ የወጡበትን ቀን ፋሲካ ብለውታል፡፡ የእርቅ፣ የሰላም፣ የድኅነት ቀን ነው ከሞት ከመነሣት ከመቃብር ጨለማ ከመውጣት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከመላቀቅ፥ ከሲኦል እስራት ከመፈታት የሚበልጥ ምን ደስታ ሊኖር ይችላል? የክርስቶስ ትንሣኤ እግዚአብሔር እኛን ምን ያህል እንደ ወደደን የምናስተውልበት፣ የፍቅሩን ጥልቀት፤ የቸርነቱን ስፋት የምናደንቅበት፤ የነፍሳችን የዕረፍት ቀን ነው፡፡

በሰው ዘንድ በቃል ሲነገር በተግባር ሲፈጸም የሚታየው ፍቅር ዘመድ ወዳጅ የሚለይበት ሰው ከሰው የሚዳላበት፤ ባለ ካባ ከባለ ካባ፣ ባለዳባ ከበለዳባ የሚበልጥበት፤ የሚወደውን የሚወዱበት፤ የሚጠላውን የሚጠሉበት ነው፡፡ ለሚጠሉት ይቅርና ለሚወዱት ተላልፎ የሚሞቱበት ፍጹም ፍቅር በዓለማችን አይታይም፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ እኛን የወደደበት ሕይወቱን እስከመስጠት ደርሶ ቤዛ የሆነበትን ምሥጢር የሰው ሕሊና መርምሮ ሊደርስበት የሚችል አይደለም፡፡ ተነጻጻሪ ተወዳዳሪ አቻ ምስያ የሌለው ልዩ ነው፡፡ ከቀደምት አበው እነ አብርሃም ልጆቻቸውን በቁርጥ ሕሊና ለመሥዋዕት አቅርበዋል፡፡ እነ ሙሴ እነ ዳዊት ይመሩት ይጠብቁት ለነበረው ሕዝብ ተላልፈን እንሙት እንቀጣ የሕዝቡን ቅጣት እንቀበል ብለው እንደነበረ ተጽፎአል፡፡

ግን በቅርብ ለነበረ፣እንዲያስተዳድሩ ለተሾሙለት ለተወሰነ ሕዝብና ለወገናቸው ብቻ ነበር፡፡ ሁሉን የሚያጠቃልል ሁሉን የሚያድን አልነበረም፡፡ መድኃኒታችንን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ መከራ ተቀብሎ የሞተው፥ ለመላው የሰው ዘር ለአዳም ልጆች ሁሉ ነው፡፡ ቤተሰብና ዘመድ ወዳጅና ጠላት ወንዝና አካባቢ የሚለው አልነበረም፡፡ ከሰው አስተሳሰብ ሚዛንና ግምት የራቀ የጠለቀ ነው፡፡ የወደደን መከራ የተቀበለው እኛ ስለወደድነው አልነበረም፡፡ እሱ ስለ ወደደን ብቻ ነው፡፡ ስንኳንስ ቀድሞ ዛሬም ያደረገልንንና ያደለንን አስበን፥ ፍቅሩን ተገንዝበን፥ ለሰው በጎ ማድረግ፤ በፍቅሩ መመላለስ እጅግ ያዳግተናል፡፡ ከሁሉም የሚረቀውና የሚደንቀው ያጠፋን የበደልን፣ በጥፋታችን ሞትን በራሳችን ላይ ያመጣን እኛ ስንሆን፥ እሱ ስለኛ በደል ተላልፎ በእኛ የተፈረደውን የሞት ፍርድ ተቀብሎ መሞቱ ይደነቃል፡፡ ለዚህም አንክሮ ይገባል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ርእዩ መጠነ ዘአፍቀረነ እግዚአብ ሔር … ወሶበ እንዘ ፀሩ ንሕነተሣሃለነ በሞተ ወልዱ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደወደደን አስተውሉ ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር አለን ” ብሎ እንዳስተማረው ስንኳን ተላልፎ እስከመሞት የሚያደርስ ፍቅርና ከፍርድ የሚያድን ምንም መልካም ሥራ ሳይኖረን፤ በሱ ፍቅር የተደረገልንን ቸርነት የምናስብበት የነፃነት የምስጋና ዕለት ነው፡፡ ሮሜ 5፥6‐ 10 በልጁ ሞት ስለካሰልን ይቅርታን አገኝን፤ በአንድ አዳም በደል ምክንያት ኃጢኣት ወደ ዓለም እንደ መጣች፤ በዚችም ኃጢኣት ምክንያት፥ በሰው ሁሉ ሞት እንደተፈረደበት፤ ሰውን ሁሉ በደለኛ፣ ኃጢአተኛ፣ አሰኝቸው፡፡ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የመጣ ሞት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበሩትን የበደሉትንና ያልበደሉትን ሁሉ ገዛቸው፡፡ ታላቁ ሙሴ እንኳን ሌላውን ሲያድን ራሳቸውንም ከሞት ማዳን ስላልተቻላቸው ለሞት ተገዝተዋል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋው ስጦታ በኃጢአታችን ልክ የተደረገብን አይደለም፡፡ ራሱን ቤዛ አድርጎ ካሰልን፤ ከዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ በጥምቀት፣ በሃብት፣ በልጅነት ለሰው ሁሉ ሕይወት በዛለት፡፡ ሮሜ5፥16‐18 የተነሣውን ክርስቶስን ሐዋርያት አይተውታል ገጽ በገጽ ዓይን በዓይን ፊት ለፊት ተያይተዋል፡፡ ሰግደውለታል፤ አመስግነውታል፤ ደስታቸው ፍጹም ሆኖላቸዋል፡፡

መላ የኢትጵያ ህዝብ ትንሳኤውነ ስናከብር በሚበላና በሚጠጣ ብቻ ሳይሆን የትንሳኤውን ትርጉም በመረዳት ሊሆን ይገባል፡፡ ትንሳኤ መነሳት ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ከወደቅንበት እንነሳ ከእራስ ወዳድነት፣ ከግለኝነት፣ ከዘረኝነት፣ ከጎጠኝነት እንነሳ፡፡ የትንሳኤው ትርጉም ትንሳኤ ለሚያስፈልጋት ሀገር ወሳኝ ነው፡፡ ሀገር በመቃብር ውስጥ እንደአላዛር በጨለማ ውስጥ ተውጣለች ከመቃብር የሚያስወጣትን የጥሪ ድምጽ እንደአላዛር እየጠበቀች ነው፡፡ የሀይማኖት አባቶች በፓላሳቸው በተዘጋ መቃብር ውስጥ ላይናገሩ አፋቸው ተዘግቷል አፋቸውን የዘጋው ሰይጣን ይሁን  ወይ መንግስት ይሁን አይታወቅም፡፡ ብቻ ሀገራችን ትንሳኤ ያስፈልጋታል፡፡ ወገኔ ተነስ ከመለያየት ሀሳብ፣ ከዘረኝነት፣ ከቋንቋ አምላኪነት፣ ከተራራና ወንዝ ቆጣሪነት፣ ተነስ ተነስ ገጀራህን ጥለህ፣ ተነስ መሳሪያህን ጥለህ፣ ተነስ የጥሉን መቃብር ደርምሰው፣ መገዳደል ይብቃ የትንሳኤውን መብራት እናብራ የፍቅር ብርሀን፣ የአንድነት ብርሀን ይብራ፡፡  ጨለማው እርሀብ ይወገድ፣ ጨለማው ወንድሙ ወንድሙን መግደል ይቁም፡፡ ስለዚህ ተነስ ተነስ ተነስ…. የትንሳኤው ትርጉም ትንሳኤ ለሚያስፈልጋት ሀገር ለኢትዮጵያያያያያያያያያያያ   

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን አደረሳችሁ አሜን፡፡