የትግራይ ሕዝብ ዋስትና በማን እጅ ላይ ነው?

Date:

በህወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አምስት ወራት ሊኾነው ነው፡፡ በዚህ የአምስት ወር ጊዜ ውስጥ የትግራይ ምድር ምንም እንኳን ከመሣሪያ ድምጽ የጸዳ ቢኾንም ሕዝቡ አሁንም በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይገኛል፡፡ የኢሮብ አካባቢዎች፣ ታሕታይ አድያቦ እና ሌሎች አካባቢዎች በኤርትራ ኃይሎች እንደተያዙ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ከእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትግሬዎች እስከአሁንም ወደቀያቸው አልተመለሱም። የትግራይ በጀት ባለመለቀቁ ለመንግሥት ሠራተኞች እስከ አሁን ደመወዝ አልተከፈለም። በዚህ ምክንያት ሠራተኛው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ። ሰብአዊ እርዳታ እና መድኃኒት ወደ ትግራይ እየገባ ቢኾንም ካለው ችግር አንጻር ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ በቂ ምግብና መድኃኒት እያገኘ ባለመኾኑ በረሃብና በጤና ችግር እየተሰቃየና መከራ አሳሩን እያየ ይገኛል፡፡

የመኪና ትራንስፖርት፣ የንግድና ነፃ የሰዎች ዝውውር እስካሁን በይፋ አልተጀመረም። በእርግጥ ሰሞኑን በሽሬ ከተማ ወደሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መጠነኛ የትራንስፖርት ፍሰት ቢኖርም የሕዝቡን ዕለታዊ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሂደት ያቃለለ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ሕዝብ ምን ዓይነት የሰቆቃ ጊዜ እያሳለፈ እንደሚገኝ መገመት አይከብድም፡፡ በተለይም ወጣቱ ክፍል በሀገሩም ይሁን በክልሉ ተስፋ በመቁረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ስደትን ምርጫው አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ህወሓት እስከ አሁንም ከሽብርተኝነት መዝግብ አልተፋቀም። ኾኖም በፕሪቶሪያ-ናይሮቢ ስምምነት መሠረት በትግራይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የማቋቋም ሂደትን እየመራ ይገኛል። በአጠቃላይ ከስምምነቱ ወዲህ በትግራይ በርካታ ለውጦች ቢኖሩም በቂ ነው ማለት ግን አይቻልም። የሕዝቡ ችግር አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ወድመው የነበሩ መሠረተ ልማቶች አንዳቸውም አልተጠገኑም፡፡ በክልሉ የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሥርዓት አሁንም በተሟላ መልኩ አልተጀመረም፡፡

ሕዝቡም እስካሁን በጦርነት ቆፈን ውስጥ እንደተሸበበበ ይገኛል፡፡ በቂ የኾነና ከዕለት ፍጆታ ያለፈ የንግድ እንቅስቃሴም በክልሉ እየተካሄደ አይገኝም፡፡ ቀደም ሲል የነበሩ የተለያዩ አምራች የኢንደስትሪ ተቋማትም ወደ ሥራቸው መመለስ አልቻሉም፡፡ ከዚህ አንጻር ለምሳሌ ከኢፈርት ኢንዶውመንት ክፍሎች አንዱ የኾነው ሸባ ፕላስቲክ ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ አዲስ አደረጃጀትና አዲስ ማሽን እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡ ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አመራሮችን ያቀፈ የልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል፣ በጦርነት ምክንያት የወደሙ የኢንቨስትመንት ተቋማትን በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል። ልዑኩ ከጎበኛቸው የወደሙ ተቋማት መካከል የሸባ ሌዘር ኢንዱስትሪ ተጠቃሽ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በጉብኝታቸው የተመለከቱን እንደገለጹት ከኾነ ሸባ ሌዘር ኢንዱስትሪ ሙሉ በሙሉ 100% የወደሙ ሌላ አዲስ ማሽን ካልመጣ በስተቀር አንድም ተጠግኖ ሥራ ላይ የሚውል አንድ ማሽን የለም፡፡ ተጠግኖ እንኳን ሥራ ላይ የሚውል ንብረት እንዳይቀር ተደርጎ ነው የወደመው። ቀደም ሲል ሸባ ሌዘር 1200 ሠራተኞች ነበሩት፡፡ ውድመት ከደረሰበት በኋላ ሠራተኛው ደመወዝ አጥቶ፣ ተቸግሮ ተፈናቅሏል። ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ተቋማትም የዚሁ ዓይነት እጣ እንደደረሳቸው አቶ ካሳሁን አረጋግጠዋል፡፡ ከኢንቨስቱ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና የተለያዩ የባሕል አውታሮችም የጦርነቱ ሰለባዎች በመኾናቸው እስካሁንም ማገገም ተስኗቸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በቅርቡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ዳግም ወደ አገልግሎት ለመግባት እርዳታ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባስተላለፈው የድጋፍ ጥሪ “ከትግራይ ጦርነት በፊት የአክሱም ዩንቨርስቲ ከሀገር አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከዋና ዋናዎቹ ተርታ ለመሰለፍ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ነበር። ነገር ግን፣ ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው ጦርነት በኋላ፣ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውድመት ገጥሞታል፣ ይህም ዩኒቨርሲቲው ከባዶ እንዲጀምር አድርጓል። ከዚህ ውጪ ላለፉት ሃያ (20) ወራት ደሞዝ ባለመከፈሉ ሰራተኞቻችን በሳይኮ-ማህበራዊ ቀውስ እና በኢኮኖሚ ቀውሶች እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ስለዚህ የአክሱም ዩንቨርስቲን መልሶ ማቋቋም እና ማገገሚያ ጥረቶችን የሚያግዝ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉልን የሀገር ውስጥ፣ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ከፍተኛ ተቋማት ጥሪያችንን እናቀርባለን።” በማለት ተማጽኗል፡፡

በጥቅሉ ክልሉ ያለበት የቀውስ ደረጃ ይህን ሲመስል በአንጻሩ ህወሓት እና የፌደራል መንግሥት ደግሞ የሕዝቡን ችግር ከመፍታት ይልቅ በሥልጣን ኮታ መሞዳሞድ ላይ ተጥደው ሰንብተዋ፡፡ ከዚያ ባለፈም ህወሓት በፌደራል መንግሥት በኩል ተንጠራርቶ አራተኛ ዙር ጦርነት በአማራ ክልል ላይ ለመክፈት የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ ይህን የሚያስረግጠው ደግሞ የሰሞነኛው የህወሃት መግለጫ ነው፡፡ ህወሓት በዚህ መግለጫው ፌደራል መንግሥቱ የአማራ ክልል ታጣቂዎችን ከክልሉ ግዛቶች ያስወጣ ሲል ጠይቋል። የክልሉ መንግሥት በዚሁ መግለጫው፣ ፌደራል መንግሥቱ በምዕራብ፣ ደቡባዊና ሰሜን ምዕራብ የትግራይ ግዛቶች የአማራ ክልል ታጣቂዎች ይፈጽሙታል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የማስቆም ኃላፊነት እንዳለበት አውስቷል። መግለጫው፣ በአማራ ክልል ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ባለችው አላማጣ ከተማ የአማራ ክልልን በመደገፍ የተካሄደው ሰልፍ፣ ከአማራ ክልል ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ሰዎችን ወደ ከተማዋ በማጓጓዝ የተደረገ “ተቀባይነት የሌለው” ሰልፍ ነው ብሏል።

በሌላ ወገን የራያ እና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ መልስ እንዲሰጠው የአላማጣ ከተማና በዙሪያው የሚገኙ የራያ ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል፡፡ በሰላማዊ ሰልፉ ንግግር ያደረጉት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ የራያ ሕዝብ ተፈጥሯዊ ማንነቱ የተነጠቀው በ1984 ዓ.ም ጀምሮ ነው ያሉ ሲኾን ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በርካታ ግፎች ደርሰውበታል፣ ጥያቄያችን እውነታዊ መሠረት ያለው በመኾኑ ፍትሐዊ የማንነት ጥያቄያችን መልስ ሊሰጠን ይገባል በማለት አሳስበዋል። በጉልበት በትግራይ ክልል ሥር በነበርንበት ወቅት በርካታ ግፎች ደርሰውብናል ያሉት ከንቲባው የትግራይ ሕዝብም እየደረሰበት ካለው ሰቆቃ መላቀቅ የሚችለው የራያና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ሲመለስ ብቻ መኾኑን ተረድቶ ተላላኪዎችን ሊቃም ይገባል ብለዋል። “አማራነታችን በተፈጥሮ ያገኘነው ማንነታችን በመኾኑ በሁለቱ ሕዝቦች እየተደረገ ያለውን የሸፍጥ ፖለቲካ አካሄድ በመቃወም በኢትዮጵያ ጥላ ስር ልንኾን ይገባል” ሲሉ ከንቲባው ጨምረው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ህወሓት ያለባበሰው የጦር ወንጀል የአሜሪካ የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ቢሮ በጦርነቱ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመድብ ገልጧል። አልፎም አሜሪካ ሰሞኑ ባወጣችው መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች “የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን ብትገልጽም፣ ይፋ ባደረገችው ዝርዝር ሰነድ ግን ህወሓትን በሰብዓዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ነጻ አድርጋ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ኃይሎችን ብቻ ተጠያቂ አድርጋለች፡፡ ይኽ አካሔድ አሁንም የትግራይን ፖለቲካ ይበልጥ እንዳያወሳስበው የሚሰጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በአንድ ወገን ላይ ብቻ ያነጣጠረው እንዲህ ያለው ፍረጃ ቢያንስ ሰላምን እንደ ውሃ ጠምቶት የኖረውን የትግራይ ሕዝብ ወደሌላ አዙሪት መልሶ እንዳያስገባው ጥበብ የተሞላበትን መልስ ይሻል፡፡    

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...