ወንድወሰን ከበደ (ጋዜጠኛና መድረክ መሪ)
ወንድወሰን ከበደ የተዋጣለት መድረክ መሪ በመሆን በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሱን አሻራ ያሳረፈ ሰው ስለመሆኑ በርካታ ባለሙያዎች ምሥክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ እርሱም ቢሆን፣ ገና ከአፍላ ወጣትነት ዕድሜው አንስቶ የተሰጠውን ይህንን ሙያ የአንድ ዘመንና ትውልድ ትውስታ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ከ25 ዓመታት በኋላ ‹‹የመድረክ ማስታወሻ›› በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ ሰንዶ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡
አሁን ላይ ኑሮውንና ተቀማጭነቱን በሃገረ አሜሪካ ያደረገው ጋዜጠኛ እና የመድረክ መሪ ወንድወሰን ከበደ፣ ከጥቂት ወራት በፊት በርካታ ከያኒያንና የጥበብ ወዳጆቹ በተገኙበት ይህንን ሳቢ በሆነ ይዘትና ቅርጽ ያዘጋጀውን መጽሐፍ አስመርቆ ለንባብ አብቅቷል፡፡ ስለመጽሐፉ፣ ስለወርቃማው የመድረክ ሕይወቱና ትውስታዎቹ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ከሀገር ከወጣህ ምን ያህል ዓመት ኾነህ?
ወንድሰን፡- ከሀገር የወጣሁት በፈረንጆቹ በ2004 ጥር ላይ ነበር፣ የሔድኩት ደግሞ ወደ አሜሪካ ነበር፡፡ ሆኖም ከ3 ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ 2007 ወደ ሀገሬ ተመልሼ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም አንድ ሦስት ጊዜ መጥቼ ነበር፡፡ በመሃል ኮቪድ ስላጋጠመ ግን ረዘም ያለ ጊዜ ሳልመጣ ቆይቼ ነበር፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ ወደ ሀገርህ ስትመጣ ምን ይዘህ ነው የመጣኽው?
ወንድሰን፡- የመጣሁት ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዝግጅቶች የመድረክ መሪና አዘጋጅ ስለነበርኩ ‹‹የመድረክ ማስታወሻ›› የሚል መጽሐፍ አዘጋጅቼ እሱን ለማስመረቅና ቤተሰቤንም ለመጠየቅ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለብዙ ዓመታት መድረክ አዘጋጅቻለሁ፡፡
በዚህ የተነሳ በእጄ ላይ የሰነድኳቸው እጅግ በርካታ የመድረክ ምስሎች ይገኛሉ፡፡ የድምፃውያን፣ የኮሜዲያን፣ የባሕልና የዘመናዊ ባንዶች በወቅቱ የነበሩ ዳንሰኞች፣ የፋሽን ትርኢትና የሰርከስ ትርኢት ተመልካቹንም ጭምር ያካተተ ከ3 ሺህ በላይ ፎቶዎች አሉኝ፡፡ እነዚህ ምስሎች በግለሰብ ደረጃ ተይዘው ከሚቀመጡ የአንድ ክፍለ ዘመን ታሪክ በመሆኑ ለሕብረተሰቡ መድረስ አለበት በሚል በመጽሐፍ ሰንጄ አቅርቤዋለሁ፡፡ መጽሐፉ እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል በታላቅ ድምቀት ተመርቋል፡፡
ግዮን፡- ፎቶዎችን ለመሰነድና በመጽሐፍ መልክ ለማዘጋጀት ምን አነሳሳህ? መጽሐፉን ለማዘጋጀትስ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?
ወንድሰን፡- ይህን ጉዳይ በይበልጥ የሠራሁት በኮቪድ ወቅት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በእጄ ላይ ያሉ ዶክመንቶች በመጽሐፍ ተሰንደው መቅረብ እንዳለባቸው አመንኩ፡፡ አሁን ላለው ትውልድ ማለትም ለጀማሪ ድምፃውያን፣ ኮሜዲያንና መሰል ሙያተኞች ስለሚጠቅም፣ በተጨማሪም የሀገር ታሪክ በመሆኑ ለሕዝብ መድረስ ስለሚገባው ይህን አድርጌያለሁ፡፡
ግዮን፡- የመጽሐፍ ምርቃቱ የተከናወነው የት ነው? የትስ ታተመ?
ወንድሰን፡- መጽሐፉ የታተመው ኢትዮጵያ ውስጥ ሴንትራል ማተሚያ ቤት ነው፡፡ የመጀመሪያው ምርቃት አዲስ አበባ እንዲሆን ያሰብኩበት ምክንያት የመጽሐፉ ማጠንጠኛ አዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል በመሆኑ ነው፡፡ የመጽሐፉ ባለጉዳዮችም በአብዛኛው አዲስ አበባ በመሆናቸው ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ በምኖርበት በአሜሪካን ሀገር ለማስመረቅ እየሠራሁ ነው፡፡
ግዮን፡- የአሜሪካው ምርቃት የመጽሐፉ ሕትመትም ጭምር እዚያው ነው?
ወንድሰን፡- ሕትመቱ አሜሪካን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ለማሳተም አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ቮልዩሙ ትልቅ ስለሆነ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሜሪካ ደግሞ ሕትመቱ እጅግ ውድ ነው፡፡ ስለዚህ በልዩ ጥራት በቻይና ታትሞ ወደ አሜሪካን ሀገር በጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚያም እዚህ አሜሪካም ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ ባለሙሉ ቀለም (ፉል ከለር) ነው፡፡ ቮልዩሙም ትልቅ ነው፡፡
ግዮን፡- በአዲስ አበባ የነበረው የምርቃት ፕሮግራም ምን ይመስል ነበር?
ወንድሰን፡- የምርቃት ፕሮግራሙ በሂልተን ሆቴል ነው የተከናወነው፡፡ ቦታው ታሪካዊ ቦታ በመሆኑ ነው የመረጥኩት፡፡ ሙሉ ዝግጅቱን በማዘጋጀት ትልቁን ድርሻ የተወጣው ወንድሜ ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ ነው፡፡ ፈጣሪ ረጅም እድሜና ጤናውን ይስጠው፡፡ ኮሚቴ አዋቅሮ ቀን ከሌሊት ደክሞ ሊያዘጋጀው ችሏል፡፡
ግዮን፡- ፕሮግራሙን እንዴት አገኘኽው?
ወንድሰን፡- በፕሮግራሙ በቃላት ከምገልፀው በላይ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ በሀገራችን አሉ የተባሉ ጋዜጠኞች እና የመድረክ ሙያተኞች ተገኝተው በዚያ ዘመን በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል እኔ ያሳለፍኩትን የመድረክ ሂደት በመጽሐፉ ከተመለከቱ በኋላ እጅግ በመደሰት መርኃ ግብሩን ተካፍለዋል፡፡
በዚህም እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ መጽሐፉ ላይ ስለኤግዚብሽን ማዕከል ሰው ከሚያውቀው ነገር በላይ ሰፍሮበታል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው የሚያውቀው በኤግዚብሽን ማዕከል የንግድ ባዛር እንደሚከናወንበት ብቻ ነው፡፡ በመጽሐፉ ግን የኤግዚብሽን ማዕከል ምሥረታ ምን ይመስል እንደነበር ሳይቀር ሠፍሯል፡፡
የዚህን ሙሉ መረጃ ያካፈለኝ ነዋሪነቱ በኮሎምበስ ኦሀዮ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ንጉሴ አየለ ተካ ነው ፤ ባለበት ምሥጋናዬ ይድረሰው፡፡ እሱም በመጽሐፉ የምረቃት ፕሮግራሙ ላይ ተገኝቶ ምሥክርነቱን ሰጥቷል፡፡ የእሱ በዚያ ቦታ ላይ መገኘት ለእኔ በጣም ትልቅ ክብር ነበር፡፡
ግዮን፡- የመጽሐፉ ምርቃት ፕሮግራም በኢቢኤስ ቲቪ እንዲተላለፍ የተደረገበት ሁኔታ ከምን የመነጨ ነው?
ወንድሰን፡- ከኢቢኤስ ውጭ ሌሎች ሚዲያዎችም ፕሮግራሙን ለማስተላለፍ ፈልገው ነበር፡፡ ኢቢኤሶች ግን አስቀድመው የመጽሐፉን ይዘት በማየታቸውና ከኪነ ጥበብ ጋር የተቆራኘ የዓመታት ልምድ ስላላቸው ሙሉ ሥራውን ከመቅረጽና ከማስተላለፍ ጀምሮ፣ ፍላጎት ስላደረባቸው ልንመርጣቸው ችለናል፡፡ ለነበረው ነገር ኢቢኤሶችን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ግዮን፡- በመድረክ ላይ እነ ድምፃዊ ፀጋዬ እሸቱ እና ሕብስት ጥሩነህ ሙዚቃ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን ትላለህ?
ወንድሰን፡- እነሱ ብቻ ሳይሆኑ መሳፍንት አወቀ፣ ሞገስ መብራቱ፣ ግዛቸው ተሾመ፡ አሰግድ ሙሉጌታና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ በነገራችን ላይ እኔና ፀጋዬ የ30 ዓመት ወዳጅነት አለን፡፡ ቤተሰባዊ ቁርኝታችንም ከፍ ያለ ነው፡፡ በዕለቱ የእናቶች ቀን ስለሚከበር እናቴ ተገኝታ ነበር፡፡ እኔም እናቴን ለማክበር ሰርፕራይዝ አደረግናት፡፡
ካባ አልብሰን ጉልበት በመሳም ከእናቴ ምርቃት አግኝቻለሁ፡፡ እናታችን ብቻዋን ያለ አባት አሳድጋናለች፡፡ ለቤቱ እኔ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ሦስት ወንድና ሦስት ሴቶች ነን፡፡ እናታችን እጅግ ጠንካራ እናት ነች፡፡ ቀደም ሲል አራት ኪሎ ዲያና የውበት ማሰልጠኛ ተቋም ባለቤትና ሥራ አስኪያጅም ነበረች ፤ የቴዲ አፍሮ ባለቤት አምለሰት ሙጬን ጨምሮ በርካታ ሞዴሊስቶችን ያፈራች እናት ነች ያለችኝ፡፡
ስለሆነም የምረቃ በዓሉ ከእናቶች ቀን ጋር በመግጠሙ ፀጋዬም አጥብቆ ለእናቱ ፍቅር ስላለው ከእናቶች ዘፈን ተወዳጅ የሆነውን ሙዚቃ ሊጫወት ችሏል፡፡ ሕብስት ጥሩነህም ‹‹አደራ አደራ›› ስትል ተጫውታለች፡፡ ሞገስ መብራቱም የድሮውን ነገር ለማስታወስ ‹‹እሲቲ የነበረ ያውራ›› የሚለውን ተጫውቷል፡፡ እነአሰግድ ግዛቸውና ሌሎችም ጥሩ ተጫውተዋል፡፡
ግዮን፡- በመጽሐፉ ውስጥ ማስታወቂያዎች ያልተጠቀማችሁት ለምንድነው?
ወንድሰን፡- ማስታወቂያ ያልተጠቀምነው ጊዜ ስላልነበረ ነው፡፡ በሌላ በኩል መጽሐፉ ትኩረትና ይዘቱ እንደመጽሔት ሳይሆን መጽሐፍ በመሆኑ ብዙ ማስታወቂያ አልተካተተበትም፡፡ መጽሐፉ በታተመበት ዋጋ ነው የተሸጠው፡፡ ትርፍ ያልተጠየቀበት መጽሐፉ የሕብረተሰቡ ንብረት በመሆኑ ነው፡፡
ግዮን፡- መጽሐፉ በዲጂታል ሚዲያዎች የመለቀቅ እድል አለው?
ወንድወሰን፡- መጽሐፉን ወደ ዲጂታል የመቀየር ፍላጎት አለን፡፡ በመጽሐፉ ላይ የተጠቀሱት እንደ ቴዲ አፍሮ፣ ሸዋንዳኝ ኃይሉ፣ ትዕግስት በቀለ፣ ማናልሞሽ ዲቦ፣ በላይ መልሴ፣ ትዕግስት ወይሶ፣ ጆኒ ራጋ እና እጅግ በርካታ ድምፃዊያን አልበም ከማውጣታቸው በፊት የመጀመሪያ መድረካቸው ነው፡፡
በሌላ በኩል የመጀመሪያ አልበማቸውን አውጥተው ወደ ማዕከሉ የመጡ ታደለ ሮባና ብርሃኑ ተዘራ /ላፎንቴኖች/፣ ጌራወርቅ ነቃጥበብ፣ ፍቅር አዲስ ነቃጥበብ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ትዕግስት በላቸውና በርካቶችም በቪዲዮ ሥራዎቻቸው ተሰንዷል፡፡ ይህን የሚያሳይ ራሱን የቻለ የዩቲዩብ ቻናል ይኖራል፡፡ በዚያ መንገድ ለሕብረተሰቡ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ የኮሜዲያን ሥራንም ያካተተ ይኖራል፡፡
ግዮን፡- ‹‹የእኛና እኛ ኢትዮጵያ›› የሙዚቃ ፕሮግራም ስታዘጋጅ ነበር ፤ ስለፕሮግራሙ ሁኔታ ብትገልጽልን?
ወንድሰን፡- ቀደም ባለው ጊዜ ጀምሮ በርካታ መድረኮችን መርቻለሁ፡፡ በርካታ ፌስቲቫሎችንም አዘጋጅቻለሁ፡፡ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም ‹‹ሐኪም ሁለት ሺህ›› የሚል ትልልቅ የሀገር ባለውለታዎች የተሸለሙበት ዝግጅት አዘጋጅቻለሁ፡፡ ‹‹እኛና እኛ ኢትዮጵያ›› የሙዚቃ ፌስቲቫልን እኔና አልማዝ ደምሴ በጋራ የምናዘጋጀው መድረክ ነበር፡፡
አልማዝ የምወዳት እህቴ ነች፡፡ በመጽሐፉ ምርቃት ዕለትም አመስግኜ ሠርተፍኬት ሰጥቻታለሁ፡፡ የእኛና እኛ ኢትዮጵያ ፕሮግራም በጣም የሚወደድ መድረክ ነበር፡፡ እኛና እኛ ኢትዮጵያ ፕሮግራምን ሙዚቀኞችም ሆነ ተመልካቹ በትልቅ ጉጉት ነበር የሚጠብቁት፡፡ በወቅቱ በሬዲዮ በቴሌቭዥንና በብሮሸሮች፣ በትላልቅ ባነሮችና በስፒከሮች ቅስቀሳ በደንብ ይተዋወቅ ነበር፡፡ በእኛና እኛ ኢትዮጵያ ላይ ያልተሸለመ የስፖርት ጋዜጠኛ የለም፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና እነ ጎርፍነህ ይመር፣ ደምሴ ዳምጤ፣ ከበደ በየነ፣ ኢብራሂም ሀጂ አሊ፣ እግርኳስ ተጫዋቾችን፣ ከየክለቡ አሠልጣኞችን ሸልመናል፡፡
ለምሳሌ የጃኖ ባንዱ ኃይሉ አመርጋ በወቅቱ ከተመልካች መሀል እየመጣ ነበር ዜማዎችን የሚያቀርበው፡፡ የአንጋፋ ድምጻውያን የእነ ይርጋ ዱባለን ነበር የሚጫወተው፡፡ የእኛን እኛ ኢትዮጵያ ፌስቲቫል ላይ ሲጫወት ቴዲ አፍሮ እራሱ አልበም አላወጣም ነበር፡፡ የእኛና እኛ ኢትዮጵያ ለሀገራችን ሙዚቃ ፌስቲቫል እና ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበከረተ ዝግጅት ነበር፡፡
ግዮን፡- ዝግጅቱ አንተ ከሀገር ስትወጣ ቆመ?
ወንድወሰን፡- አዎ፡፡ የዝግጅቱ ባለቤት እኔና አልማዝ ደምሴ ነበርን፡፡ እኔ ከሄድኩ በኋላ ሊሠራ የሚችል ሰው ስለሌለ ሥራው ቆሟል፡፡
“ግዮን” መጽሔት ቅዳሜ ህዳር 13 2018 ዓ.ም የወጣ ዕትም ነዉ
ግዮን፡- ከአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር የበጎ አድራጎት ሥራ ትሠሩ ነበር ፤ ለምን ያህል ጊዜ ሠራችሁ? የነበረው ሂደትስ ምን ይመስላል? አንተ ከሄድክ በኋላስ ቆመ?
የጋዜጠኛና መድረክ መሪ ወንድወሰን ከበደን ክፍል ሁለት ቃለ ምልልስ በሚቀጥሉት ቀናት ጠብቁን !!!
