የአዲስ አበባ ጉዳይ “ቅርቃር” እንደገባ ተደርጎ ለአሸማጋይ ቡድን ቀርቧል

Date:

በቅርቡ በኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው የምክክር ጉባዔ በታዛቢነት ያሰማራቸው አባላቱ በተለይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ሁለተኛ ሰነድ ያቀረበውን የክልል ምክር ቤት ጉባዔ እና ሌሎች “ጠንከንር ያሉ ውይይቶችን” ለመታዘብ የሚያስችላቸው ሁኔታ እንዳላገኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ) ገለጸ።

ህብረቱ ጉባዔውን የተመለከተ የመጀመሪያ ሪፖርት በራድሰን ብሉ ሆቴል ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ በሰጡት ገለጻ፣ “እኛ ያሰማራናቸው 10 ታዛቢዎች የተወሰኑ ውይይቶችን ገብተው ለመከታተል ያልቻሉባቸው ሁኔታዎች አሉ። በተለይ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የክልል ምክር ቤት ጉባዔን፣ አንዳንድ ጠንከር ያሉ ውይይቶች በሚደረጉበት ጊዜ Regular ባልሆነ መንገድ ያልገቡባቸውና ያልታዘቧቸው አሉ” ብለዋል።

“ይህንን እንደ አንድ ክፍተት አይተናል” ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ዘርግቶት በነበረው መመሪያ መሰረት ምክረ ሀሳቦች ላይ የድምፅ አሰጣጥ አሰራር እንደሚኖር ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ግን ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል።

ይህ በእንዲህ እያለ በድምፅ አሰጣጥ መመሪያው መሰረት ሳይታይ ካለፈ በኋላ የአዲስ አበባ ጉዳይ “ቅርቃር” እንደገባ ተደርጎ ለአሸማጋይ ቡድን ቀርቧል። ጉዳዩ መጀመሪያ የድምፅ አሰጣጥ ሂደትን ማለፍ ቢኖርበትን ይህ ሳይሆን በመጨረሻው ሰዓት የክልል ምክር ቤት ጉባዔ (አሸማጋይ ቡድን) መቅረቡም ቅሬታ አስነስቶ ተነስተውሏል።

ይህንኑ በተመለከተ የተቋማቸው ግምገማ ምን እንደሆነ አቶ መሱድ ዛሬ ተጠይቀዋል።

በምላሻቸውም፣ “ይህ ዝርዝር ሪፖርታችንን ስናወጣ የምናሳየው ነው። በጥሩ መልክ ያነሳነው ግን ኮሚሽኑ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን የሚያሳይ መመሪያ አዘጋጅቶ በመመሪያው መሰረት ሂደቱን ለመምራት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሆኖም ግን እስከ መጨረሻው ጊዜ ድረስ መመሪያው ላይ የተቀመጡት ነገሮች ተግባራዊ አልተደረጉም” ብለዋል።

“የክልል ምክር ቤት ጉባዔ ወደ 336 አካባቢ የክልል ተወካዮች (ከፌዴራል ተቋማት፣ ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና ከሁሉም ክልሎች) የተመረጡ ነበሩ። መመሪያው መሰረት የዚህ ኮሚቴ አስፈላጊነት በጉዳዮች ላይ መግግባት ሳይቻል ቢቀርና ወደ ቅርቃር የሚገባ ቢሆን፣ አንድን ጉዳይ ከ75% በላይ ድምፅ ካልደገፈው፣ ከሁለት በላይ ክልሎች ጉዳዩ ህልውናችንን አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ምክንያት ካላቸው፣ በምክር ቤቱ እንደገና ታይቶ 70% ድምፅ ካገኘ ሀሳቡ የሚያልፍበት ነው። እዚህ የደረሰ ነገር ግን የለም። ስምምነት ከተደረሰ ደግሞ ድምፅ መስጠት አስፈላጊ ላይሆን ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።

ምንም እንኳ ከ400 ምክረ ሀሳቦች አብዛኞቹ ቢያስማሙም ዋና የሚባሉት የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የመንግስት አደረጃጀት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሰንደቅ አላማ ጉዳዮች በልዩነት መያዛቸውን አስረድተው፣ ይህ የሆነው “የምክክር ኮሚሽኑ የዘረጋውን ስርዓት እስከ መጨረሻው ባለመከተሉ ክፍተት ነው የሚል እይታ አለኝ” ብለዋል።

“በአዲስ አበባ ጉዳይ መጨረሻ ላይ ከተነሳው ጉዳይ ላይ ኮሚሽኑ የክልል ምክር ቤት ጉባዔ ጠርቶ ምን እንድናደርግ ምክር ትሰጡናላችሁ? ነው እንጅ ያለው፤ ስልጣን ያለው አይደለም። የአሸማጋዮች ጉባዔም ምክረ ሀሳብ ነው የሰጠው፤ ማንዴት ስላለው ስለሌለው ሳይሆን ኮሚሽኑ ይህን ቢያደርግ የተሻለ ነው የሚል ምክረ ሀሳብ ነው የሰጠው” ሲሉም አስረድተዋል።

“በአጀንዳው ላይ የነበሩ ተመካካሪዎች ያመጣቸው ምክረ ሀሳቦችም፣ ይሄ ጉባዔም የሰጠው ምክረ ሀሳብ ተነቧል። ኮሚሽኑ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን ምክረ ሀሳብ ምን ያክል ታሳቢ ያደርገዋል? የሚለውን ሁላችንን ወደፊት የምናቸው ነው የሚሆነው” ብለዋል።

“ኮሚሽኑ ይህን ማድረጉን በመጥፎ የማየው አይደለም” ብለው፣ ይልቁንም ለውሳኔ አሰጣጥ እንዲመቸው የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

እንዲሁም፥ “ከተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ ‘የእኔ ጉዳይ በገለጽኩት አግባብ አልተነሳልኝም’ በሚል በፅሑፍ መልክ በተለይ በኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓት ላይ ኮሚሽኑ ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ፓርቲዎች ነበሩ” ያሉት አቶ መሱድ፣ “ወዲያው ጉዳዩ ተፈትቶላቸው መሆን አለመሆኑን ሂደቱ እየተደረገ ባለበት ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

“መጨረሻም መዝጊያው ላይ ቅሬታችሁን ያቀረባችሁ ባለድርሻ አካላት ካላችሁ ጉዳያችሁ እየታዬ እንደሚቀጥል የሚል ነበር” ብለው፣ “ወዲያው ወዲያው መፍትሄ እንዲያገኙ እንጠብቅ ነበር” በማለትም ግምገማቸውን ገልጸዋል።

ወቅቱን በጠበቀ መልኩ የቅሬታ አፈታት ስርዓቶች አለመኖራቸውን፣ የመረጃ መስጫ ደስኮች በየቦታው ቢቀመጡም ባለሙያዎች ይገኙባቸው እንዳልነበር አንስተው፣ “ይሄ ቶሎ ቶሎ ቅሬታ፣ አቤቱታ ለማቅረብና በኮሚሺኑ በኩል ቶሎ መልስ ለማግኘት የተወሰኑ ክፍተቶችን አይተናል” ብለዋል።

በምክክሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉባዔው ወቅት በተለይ የባለሙያዎች፣ የአመካካሪዎች ጣልቃ ገብነት እንዳለ ሲያነሱ ነበር፣ ቅሬታዎቹ ትክክለኛ ስለመሆናቸው በሪፖርታቸው ዳሰው እንደሆንም ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ተጠይቀዋል።

እሳቸውም፣ “ለምሳሌ አመካካሪዎች ጫና ያደረጉባቸው ሁኔታዎች በጣት የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ ግን በተወሰነ ደረጃ እንደዛ አይነት ነገሮች እንዳሉ፤ የባለሙያዎች ቡድንም አንዳንድ ጉዳዮች ሲያብራሩ የራሳቸውን ፖዜሽን በሚመስል መልኩ ሲያቀርቡ የነበሩ እንዳሉ ዶክሜንት አድርገናል” ሲሉ መልሰዋል።

“የአቤቱታቸውን ኮፒ የሰጡን ፓርቲዎችም አሉ” ያሉት አቶ መሱድ፣ ታዛቢዎቻቸውም ያስተዋሏቸው ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸው፣ “የአሁኑ ላይ ግኝታችን በደንብ አላሳየነውም። በቅርብ ሌላ ራሱን የቻለ ሪፖርት የምናወጣው አለን” ሲሉ ጠቁመዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት ገለጸች

ኢራን የአሜሪካን የጦር መርከቦች ዒላማ የማድረግ አቅም እንዳላት የአገሪቱ...

ከትግራይ ዩኒቨርሲቲ ታጣቂዎች ካልወጡ ተማሪ አንመድብም

ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የሚገኙ መቐለ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና...

ኢራን አሜሪካ የጣለችባት ዕገዳ የበለጠ የሚጎዳው ዋሽንግተንን ነው አለች

አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ እና የባሕር እንቅስቃሴ እገዳ...

ግብጻዊቷ የቴሌቪዥን አዘጋጅ በዕፅ ዝውውር ወንጀል የሞት ፍርድ ተወሰነባት

የካይሮ የወንጀል ችሎት፤ ዕውቋን የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ሳራ ካሊፋን...