የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በትግራይ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውንና ሁኔታውም ጥልቅ ስጋት እንደፈጠረባቸው አስታወቁ።
ሊቀመንበሩ ባወጡት መግለጫ፤ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መካከል ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት (COHA) የተገኘው ድል ተጠብቆ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመካከላቸው ያለውን መተማመን ሊሸረሽሩ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ማንኛቸውም ያልተቋጩ ጉዳዮች ካሉ በሰላም ስምምነቱ መንፈስ እና ግዴታዎች መሠረት ገንቢ በሆነ ውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
አፍሪካ ህብረት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲተገበር ያለውን ጽኑ አቋም በድጋሚ ገልጿል።
ህብረቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ለሚካሄደው የሰላም ግንባታ እና የዕርቅ ሂደት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም መግለጫው አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተቋቋመው የህብረቱ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ውይይት፣ ትብብር እና መተማመንን የማሳደግ ሥራ ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት አካል መሆኑ ተጠቁሟል።
