የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ ቀውስ ከመፍጠር እንዲቆጠቡ አሳስበው፣ ችግሮች በውይይት እና የመግባቢያ ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተናገሩ።
ፔዜሽኪያን በቴህራን በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ “በውይይቱ እና በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ከቀጠልን ችግሮቹን እንፈታለን እና መብቶቻችንን እናስጠብቃለን” ሲሉ መናገራቸውን ሜህር የዜና ኤጀንሲ ዘግቧል።
“ትራምፕ ተጨማሪ ቀውስን ባይፈጥሩ እና እስራኤል አለመረጋጋትን ባትፈጥር እና ጠብ ባትጭር ለአገሪቱ፣ ለቀጣናው እና ለዓለም ጥቅም ነው” ሲሉ አክለዋል።
ፔዜሽኪያን ኢራን ጦርነትን እንደማትደግፍ፤ ነገር ግን ለማንኛውም ጥቃት ብርቱ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
“ጦርነትን አንወድም፤ ነገር ግን ለየትኛውም ጠብ አጫሪነት በጽናት ቆመን ራሳችንን እንከላከላለን” ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም “ግዛቱን ለመከላከል ቆርጦ የተባበረ አንድ አገር እጅ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ኃይል” እንደሌለም ተናግረዋል።
ቴህራን ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እንደምትፈልግ ቢናገሩም፣ የኢራን ሕዝብ፣ ባለሥልጣናት እና የጦር አዛዦች ለዛቻ እና ጠበኝነት “በፍፁም እጅ እንደማይሰጡ” አፅንዖት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንቱ እስራኤል በሙስሊም አገሮች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ትፈልጋለች ሲሉም ከስሰዋል።
አክለውም በሙስሊም አገሮች መካከል ያለው አንድነት እንዲህ ዓይነቱን ጥረት ሊያደናቅፍ እንደሚችልም ተናግረዋል።
ፔዜሽኪያን ሕዝቡ እንዲረጋጋ እና ከመንግሥት ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበው፣ የኢራን ጠላቶች በጫና አገሪቱን እንደምትንበረከክ ማመን የለባቸውም ብለዋል።
እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ኢራን ላይ ጦርነት የጀመሩት የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን እንዲሁም ቁልፍ የአመራር እና ወታደራዊ ማዕከላትን ዒላማ በማድረግ ነበር።
ነገር ግን በጦርነት እና በድርድር ውስጥ ሳትበገር የቆየችው ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት እንዲሁም በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከባድ ተጽዕኖን ማሳደር ችላለች።
በሰኔ ወር በኢራን እና አሜሪካ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት በተኩስ አቁም ጋብ ለማድረግ ያስችላል የተባለ የመግባቢያ ስምምነት በፓኪስታን እና ኳታር አደራዳሪነት እንዲፈራረሙ ማድረግ ተችሎ ነበር።
ነገር ግን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ዘላቂ መፍትሄ ላይ ባለመደረሱ ዳግም ውጥረት አገርሽቷል።
