የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ማኅበራዊ ሚዲያ እና የጽንፈኝነት አደጋ

Date:

መግቢያ
በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣው የወጣቶች ቁጥር በፍጥነት እየተስፋፋ ካለው የዲጂታል መሠረተ-ልማት ጋር ተደምሮ ከፍተኛ አቅም ያለው፣ ነገር ግን ዕድሎች ብቻ ሳይሆን ጉዳቶችም ያሉት በሁለት በኩል የሚቆርጥ ስለት ፈጥሯል።

የዲጂታል መሠረተ-ልማቱ ተደራሽነቻቸው እንዲጨምር ዕድል የፈጠረላቸው የማኅበራዊ ትስስር ገጾች – በዋናነት ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብ –  በፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና በኢኮኖሚያዊ ስጋት ውስጥ ላደገው ትውልድ ከመገናኛ መሳሪያነት አልፈው የማንነት መገንቢያ ምህዳሮች ሆነዋል።

እነዚህ የዲጂታል አማራጮች ከ2007 እስከ 2010 የኢትዮጵያን ፖለቲካ የቀየሩ የወጣቶች ተቃውሞዎች እንዲቀናጁ አዎንታዊ ሚና የነበራቸው ቢሆንም፣ ከዚያ ወዲህ ግን ከፊሎቹ ወደ “የመረጃ ጦርነት” አውድማነት ተቀይረዋል።

ይህ አጭር ጽሁፍ በሚዲያ፣ በወጣቶች እና በግጭት መካከል ያለውን ቁርኝት ይተነትናል፤ ማኅበራዊው ሚዲያ ስሜትን በሚኮረኩሩ ‘አልጎሪዝሞች’ በመታገዝ  የብሶት ትርክቶችን በመሸጥ ወጣቶች ለግጭቶች ተጋላጭ  እንዳደረጋቸው ይከራከራል፤ ጥቂት የመፍትሔ ሀሳቦችንም ይሰጣል።


የዲጂታል አደባባይ፡ ማንነት፣ የባለቤትነት ስሜት እና የወጣቶች ሥነ-ምህዳር


በመዋቅራዊ ችግሮች (ለምሳሌ፤ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና የፖለቲካዊ ውክልና ማነስ) ምክንያት ከማኅበረ-ፖለቲካዊ ተሳትፎ የተገለሉ ወጣቶች፣ የኦንላይን መድረኮችን እንደ አማራጭ የዜግነት እና የባለቤትነት ማረጋገጫ ቦታዎች መገልገል ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ማኅበራዊ ሚዲያን እንደ ህልውና ዋስትና የሚወስዱ ግለሰቦችና ቡድኖች እየበረከቱ መጥተዋል።


የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዘይቤው እንደ መድረኮቹ ባህሪ ይለያያል። ፌስቡክ ለሰፋፊ የፖለቲካ ክርክሮች እና ለረጅም ትረካዎች እንደ “የሕዝብ አደባባይ” ያገለግላል። ቴሌግራም፣ አነስተኛ ዴታ የሚጠይቅ እና ደህንነቱ አስተማማኝ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ለመቀስቀሻነት እና ያልተጣሩ መረጃዎችን በፍጥነት ለማሰራጨት እንደ ዋና “የኦፕሬሽን ማዕከል” ያገለግላል።

ዩቲዩብ የዲያስፖራ እና የሀገር ውስጥ ልሂቃን ለግጭቶች ርዕዮተ-ዓለማዊ ቅርጽ የሚሰጡበት መድረክ ሆኗል። በቅርቡ ደግሞ፣ ቲክቶክ ውስብስብ ታሪካዊ ቅሬታዎችን ወደ 15 ሰከንድ፣ ስሜት ቀስቃሽ ቪዲዮዎች በመቀየር ለግጭት ማቀጣጠያነት እየዋለ ይገኛል።


ለኢትዮጵያ ወጣቶች እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች መረጃ የሚቀበሉባቸው ብቻ ሳይሆኑ ስሜቶቻቸውን የሚያንጸባርቁባቸው ናቸው። የመድረኮቹ አልጎሪዝም ከፍተኛ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ጉዳዮችን (ንዴት፣ ፍርሃት እና ኩራት) ያበረታታል።

በዚህም ምክንያት፣ የብዙ ወጣቶች ዲጂታል ማንነት የሚገነባው “ከሌላው” ወገን ጋር በሚደረግ ተቃርኖ ነው። የባለቤትነት ስሜትም በዜግነት ተሳትፎ ሳይሆን፣ የራስን ብሄር ወይም የራስን ሃይማኖት ከተጋረጠበት “የህልውና ስጋት” በመከላከል ይገለጻል።


መድልዎን የሚያጎሉ አልጎሪዝሞች፡ ወጣቶች እና ዘውግ-ተኮር ግጭቶች


የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አወቃቀር ከኢትዮጵያ ብሄር-ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት ጋር ተዳምሮ አሉታዊ ውጤት ፈጥሯል። የተጠቃሚን ተሳትፎ ለመጨመር የተነደፉት አልጎሪዝሞች የአልጎሪዝሙ ፈጣሪዎችም ሆነ ተጠቃሚዎች ሳያውቁት የብሄር ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ ናቸው።

አንድ ወጣት የራሱን ብሄር ታሪካዊ ተበዳይነት የሚያረጋግጥ ይዘትን ሲመለከት፣ መድረኩ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን በርካታ መረጃዎች ደጋግሞ ያቀርብለታል። ይህም ወጣቱ ወደ ተዘጋ “የመረጃ ቋት” ወይም “የገደል ማሚቶ” ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። ይህም በአካባቢው ያለ ሁሉ ተመሳሳይ ብሶት እየተናገረ ያለ እንዲመስለው ያደርጋል።


በአብዛኛው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ቅሬታዎች ለውይይት አይቀርቡም፤ የልጥፎቹም ዓላማ ለችግሮች መፍትሔ መሻት አይደለም። የልጥፎቹ ዓላማ የአንባቢን ስሜት በመቀስቀስ ለጥቃት መሳሪያነት ማዘጋጀት ነው። የወጣቶች “የሳይበር ሠራዊት” በአመክኖ ለተደራጀ ውይይት ዝግጁ አይደለም።

የሳይበር ቀስቃሾች በተለምዶ ከምናውቃቸው የአዳራሽ ቀስቃሾች እጅግ የበለጠ ተጽዕኖ አላቸው።  ለምሳሌ በአንድ በአልታወቀ ቦታ የሚገኝ አንድ “ኢንፍሉዌንሰር” አንድን ክስተቶች ከትልቅ የህልውና እና የተጋድሎ ትረካ ጋር በማያያዝ በአማራ፣ በኦሮሚያ ወይም በትግራይ ክልል የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በቁጣ እንዲንቀሳቀሱ መቀስቀስ ይችላል።


በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች፣ ጥላቻን የሚያንጸባርቁ ንግግሮች በምስል እና በቀልድ መልክ ሲሰራጩ እናያለን። ይህ ደግሞ ለቃላት የነበረውን የሞራል ልጓም በማላላት ወደ አካላዊ ጥቃት መሸጋገርን ቀላል ያደርገዋል። የመረጃ ስርጭት ፍጥነትም ወሳኝ ነው፤ በፌስቡክ ወይም በቴሌግራም የሚናፈስ የብሄር ጥቃት ወሬ፣ የመንግስት አካላት ወይም እውነታ አጣሪዎች ከመድረሳቸው በፊት በሩቅ ከተማ ውስጥ የበቀል ጥቃትን ሊያስነሳ ይችላል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተነዛ ውሸት፣ ውሸት መሆኑ ከመጣራቱ በፊት የበቀል ተግባራት ተፈፃሚ ይሆናሉ። በቀል በቀልህ ይወልድና ሁኔታዎች በቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። የሚዲያው አሠራር ወጣቶች አስበውበት ብቻ ሳይሆን ሳያስቡትና ሳይፈለጉ የጥላቻ ንግግር ተቀባዮች ከዚያም አልፎ የጥላቻ ንግግር አምራቾች ያደርጋቸዋል። 


ይህ ጽሁፍ በYCDF የሰላም እና ግጭት ማስወገድ መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው። የጽሁፍ አዘጋጅ ታደሰ ብሩ (ዶ/ር)  የYCDF  የፕሮግራምና አጋርነት ክፍል ኃላፊ ናቸው። በ  info@ycdfet.org ወይም  tkersmo@yahoo.com ይገኛሉ።

በሚቀጥለዉ ከዚህ በታች በቀረቡት ርዕሰ ጉዳይ እንገኛለን ።


እምነት እና የዲጂታል ምሽጎች፡ የሃይማኖት ግጭት ተለዋዋጭ ባህሪያት

በምርጫ እና በተጽዕኖ መሃል፡ “የላይክ” ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...