የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች በካፒታል ገበያ ላይ በቀላሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችለውን “ንዋይ” የተሰኘ የመጀመሪያውን የድረ-ገጽና የሞባይል ግብይት መተግበሪያ በይፋ ማስጀመሩን አስታወቀ።
ዛሬ ይፋ የተደረገው ይህ መተግበሪያ፣ ገበያው ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ አቅራቢ “ኢንፎቴክ ፕራይቬት ሊሚትድ” ጋር በመተባበር ያበለጸገው እንደሆነ ተጠቁሟል።
መተግበሪያው ደንበኞችን በቀላሉ ለመመዝገብ፣ የሽያጭና ግዢ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ እንዲሁም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን በየሰዓቱ ለመከታተል የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮችን አካትቷል።
የገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን እስማኤል ካሰሁን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ “ንዋይ” መተግበሪያ የሀብት ተደራሽነትን ዲሞክራሲያዊ በማድረግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባሉበት ቦታ ሆኖ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ዕድል ይፈጥራል።
መተግበሪያው ጠንካራ የደህንነት ሥርዓት (KYC) ያለው በመሆኑ፣ የኢንቨስተሮችን ጥበቃ የሚያረጋግጥና በገበያው ላይ ያለውን እምነት የሚያሳድግ መሆኑ ተገልጿል። ይህም በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
