የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በሕጋዊ የንግድ ስምምነት “ያለ ገደብ” በባሕር በርነት ልትጠቀማቸው የምትችላቸው በርካታ የጎረቤት አገራት ወደቦች አሉላት አሉ።
ኢትዮጵያ፣ “አላስፈላጊ” እና “በቀጠናዊ መረጋጋት” እና “በጤናማ ትብብር” ላይ የከፋ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ግጭት በመቀስቀስ ፋንታ፣ “ቀጠናዊ” እና “ዓለማቀፍ” ትብብሮችን ለመፍጠር ልትጠቀመው የምትችለው “ብዙ ሃብት” አላት በማለት የማነ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ችግሩ ግን የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ በቀጠናው “ኃያል” መኾኑን ለማሳየት የሚጣጣረው፣ “የጎረቤት አገራትን ሃብት የመንጠቅ” ሃሳብ ስላለው ነው በማለት የማነ ወቅሠዋል።
ኾኖም ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን በሕጋዊ የንግድ ስምምነት እንድትጠቀም መንግሥታቸው ይፈቅድ እንደኾነ የማነ አልጠቆሙም። የማነ፣ የቀይ ባሕር ጸጥታ ጉዳይ “አዋሳኝ” አገራትን ብቻ የሚመለከትና “ከሕግ አንጻር የተዘጋ” መኾኑን ጭምር በአጽንዖት ገልጸዋል።
[ዋዜማ]
