በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያሳረፉትና ለግማሽ ክፍለ ዘመን ሀገራቸውን በታማኝነት ያገለገሉት አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ-ጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አምባሳደሯ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ከመመሥረቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ወደ ዲፕሎማሲው ዓለም የተቀላቀሉ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ጥቂት ሴት ዲፕሎማቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ታሪካዊ ሰው ነበሩ።
አምባሳደር ቆንጂት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ ኃላፊነት የደረሱ ሲሆን፣ በካይሮ፣ ኦታዋ፣ ቴል አቪቭ እና ቪየና በሚገኙ ሚሲዮኖች በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ሀገራቸውን ወክለዋል።
እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት እና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን በብቃት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር በመሆን ታሪክ ሰርተዋል።
ከሀገራዊ አገልግሎታቸው ባሻገር፣ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ውስጥ በልዩ አማካሪነት በመሳተፍ ለቀጠናው ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ላበረከቱት የላቀ የዲፕሎማሲ አገልግሎት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና እና ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ ህልፈታቸው ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ትልቅ የዲፕሎማሲ ባለሙያ ማጣት መሆኑ ተገልጿል።
ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።
