የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ማክሰኞ ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ ስብሰባ ምክር ቤቱ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ሹመቶችን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከስብሰባው ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሹመት አንዱ ሲሆን ምክር ቤቱ የቀረበለትን እጩ መርምሮ ውሳኔ ያሳልፋል።
በተጨማሪም የፍትህ ስርአቱን ለማጠናከር የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞች ሹመትን መርምሮ ማጽደቅ ሌላኛው ታላቅ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል።
ከሹመቶቹ ባሻገር ምክር ቤቱ በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ የተከናወኑ ተግባራትንና የነበሩ ውይይቶችን የያዘውን ቃለ ጉባኤ መርምሮ እንደሚያጸድቅ ከምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን፣ አስተምህሮና ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ የወጣው መረጃ ያመለክታል።
ይህ ስብሰባ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታና በፍትህ ስርአቱ ላይ ወሳኝ ለውጦችን ያመጣል ተብሎ ይታመናል።
