ኳታር የኢኳዶር ተጨዋቾችን ለመደለል ሞክራለች በሚል በሬ ወለደ ወሬ ተጀምሮ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲናን የክብር ካባ በማልበስ የተጠናቀቀው የ 2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከበስተጀርባው ግን ብዙ ፖለቲካዊ ሰበዞች እና የሴራ ትንተናን የያዘ ነበር። በእርግጥ ለኳታራዊያኑ እና ለመላው የመካከለኛ ምስራቅ ህዝብ የዓለም ዋንጫው ከውድቀት ይልቅ ስኬትን ያላበሳቸው እንደሆነ ሊያስቡ ቢችሉም ምዕራባዊያኑ ግን ከነጭ ጋቢ ጥቁር ነጥብን ከመፈለግ አልቦዘኑም።
ኳታር አስቀድማ ውድድሩን ከተረከበችበት ጊዜ ጀምሮ ስሟን የሚያጎድፍ ባታጣም የውድድሩ ጅማሮ ሰሞን ላይ የነበረው ከበድ ያለ የትችት ናዳ ግን ሊቋቋሙት የሚከብድ ናላን የሚያዞር ይመስል ነበር። ኳታር እና የዓለም አቀፉ እግርኳስ ማህበራት የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ግን ያንን ሁሉ ቅጥ ያጣ የትችት ናዳ በተረጋጋ መንፈስ
የሚያስተናግዱበት የደነደነ ልብ ነበራቸው።
ፊፋ በፕሬዝዳንቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በኩል አርፋቹ እግርኳሱ ላይ አተኩሩ እያለ ለተወዳዳሪ ሀገራት ማስጠንቀቂያ ሲልክ ኳታር በበኩሏ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰነዘርብኝ ክስ ሁሉ በሬ ወለደ ነው። የውድድሩ ጅማሮ እውነታውን ይገልጥላቹሃል በማለት ጫናውን በጋራ ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውለዋል።
የሁሉ መጀመሪያ የነበረው ግን አምጃድ ጠሃ የተባለው ግለሰብ በይፋዊ የቲውተር ገፁ ላይ ኳታር የመክፈቻ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንዲረዳት ስምንት ለሚደርሱ የኢኳዶር ተጨዋቾች 7.4 ሚሊየን ዶላር በጉቦ መልክ ሰጥታለች ማለቱ ነበር። ግለሰቡ አራት መቶ ሺ የሚደርሱ ተከታዮች ያሉት ሲሆን ዜናውን ተዓማኒ የተባሉ የመገናኛ ብዙሃን በየቋንቋቸው ለህዝባቸው ሲያደርሱ መታዘብ ችሏል። የሆላንዱ ደ ቴሌግራፍ የህንዶቹ ኢንዲያ ኢኮኖሚክ ታይምስ እና ሂንዱስታን ታይምስ ተጠቃሾች ነበሩ።
በቲክቶክ የዩኤስ የዘገባ ምንጭ የሆነው ባርስቱል ስፖርት ይህኑን ዘገባ ሲያገባ 1.3 ሚሊየን ጊዜ መታየት ችሏል። ጉዳዩን በቲውተር እና በቲክቶክ ለማስተጋባት የሞከሩት ሁለት ግለሰቦች ስለማንነታቸው ዘ አትሌቲክ በተባለው ግዙፍ ሚዲያ በተጠየቁ ጊዜ ስለ መካከለኛ ምስራቅ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራ የብሪታኒያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ውስጥ እንደሚሰሩ ነበር ይፋ ያደረጉት። ነገር ግን በተደረገው ማጣራት እንዲህ ያለ ተቋም በመላው ብሪታኒያ ሊገኝ አልቻለም። ይህ አስቀድሞም ቢሆን የዚህ ውድድር ለኳታር መሰጠትን ላለመቀበል የትችት ተኩሳቸውን የከፈቱ አካላት የውድድሩን መክፈቻ እና የሀገሪቱን ላቅ ያለ ዝግጅት ለማጣጣል የተጓዙበትን ርቀት ማሳያ ሆኖ አልፏል።
እንዲህ ያሉ ጉዳዮች እውነታ ላይ የተከፈቱ ጦርነቶች ከመሆን አልፈው የተቺዎቹ ማንነት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጋቸው አይቀርም። ለምሳሌ እንኳን አምጃድ ጠሃን ብንወስድ እንኳን The Deception Arab Spring በሚለው ፅሁፉ በአረቡ አለም ተነስተው የነበሩ ህዝባዊ አመፆችን አላስፈላጊነት የጠቀሰ ነው ይሄም የግለሰቡን ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ለራሱ ጥቅም እና ፍላጎት መቆምን አመላካች ነው በሚል ከፍተኛ ትችት ደርሶበታል። በማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው ብዙ ተከታይ ስለያዙ አሊያም ከገፃቸው ጎን ሰማያዊ ጭረትን ስላገኙ ብቻ ተዓማኒ አርጎ መቀበልም የተከታዩ ስህተት እንደሆነ ጠቋሚ ነው።
አምጃድ ጠሃ ዘ አትሌቲክ የተሰኘው ግዙፍ የሚዲያ ተቋም በሱ የተሳሳተ መረጃ ላይ ሰፊ ሀተታ በተነገረው ጊዜ በይፋዊ የቲውተር ገፁ ላይ ያጋራውን መረጃ ወዲያው አጥፍቶታል። የተሳሳቱ መረጃዎች አንዴ ካፈተለኩ የተደራሽነታቸውን መጠን መገመት ከባድ አይሆንም። ለዛም ነው በዓለም ዋንጫው ኳታርን በአሠልጣኝነት የመሩት ፌሊክስ ሳንቼዝ በይነ-መረብ ጥቅሙ ላይ ያለ እንደሆነ ሁሉ ጉዳቱም በዛው ልክ ነው ብለው የገለፁት።
ከህዝብ ግንኙነት ስራ ጋር በተያያዘ ኳታር አስቀድሞም ቢሆን በእግርኳሱ እዚህ ግባ የማይባል ስምን መያዟ እና በሰበአዊ መብት አያያዟ ላይ ጥያቄ ሲነሳባት በመክረሙ ምክንያት ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራ አስገድዷታል። ፈረንጆቹ Sports Washing ብለው ያስቀምጡታል የጎደፈን ስም በስፖርታዊ ክንውኖች ለማጥራት የሚደረግ ጥረት ነው። የውድድሩ ጅማሮ ሲቃረብ ዳቪድ ቤካምን አስቀድማ ደሞ እንደ ዚነዲን ዚዳን ፣ ፔፕ ጓርዲዮላ ፣ ጋብሬል ባቲስቱታ ፣ ሮጀር ሚላ እና ቲም ካሂልን ለማስታወቂያ ስራ መጠቀሟ ከምዕራባዊያኑ የመገናኛ አውታሮች የተሰነዘረባትን የበዛ ፍላፃ ለመቋቋም እንዳስቸግራት ቁልጭ አድርጎ ያስያል።
ለምሳሌ የቀድሞ የባርሴሎና አማካይ ዣቪ ሄርናንዴዝ በኳታር አል-ሳድን በሚያሰለጥነበት ወቅት ስለ ዓለም ዋንጫው በጎ በጎ ነገሮችን ብቻ እንዲያወራ ለሶስት አመት የሚቆይ ስምምነት ነበራቸው። በስምምነቱ መሰረት ዣቪ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቀርቦ ስለ ውድድሩ ካላወራ ከክፍያው የሚቆረጥበትን አንቀፅ የያዘ ነበር። የቀድሞውን የኤቨርተን የፊት መስመር ተሠላፊ ቲም ካሂልንም ብንወስድ በአውስትራሊያ እግርኳስ ፌደሬሽን በኩል በኳታር ውክልና ቢሰጠውም ጎን ለጎን ግን የውድድሩ አምባሳደር ነበር። ታዲያ የአውስትራሊያ ብሄራዊ ቡድን እና የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ውዝግብ ውስጥ በገቡ ጊዜ ካሂል ዝምታን ለመምረጥ ተገዷል። ኳታር በህዝብ ግንኙነት ስራዋ ላይ ስኬታማ ነበረች እንድንል የሚያደርገንም ስመጥር የሆኑ የእግርኳሱ ዓለም ሰዎችን ወደራሷ የሳበችበት መንገድ አስደናቂ በመሆኑም ጭምር ነው።
እንደዛም ቢሆን ኳታር ቀጥተኛም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ ዴኒማርክ እና ጀርመን ካሉ ሀገራት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብታ ነበር። በእርግጥ ጀርመን ‹‹ዓይኔን ግንባር ያድርገው›› በሚመስል መልኩ ሰብዓዊ መብት ጥሳለች ብላ ስትከሳት ከከረመችው ኳታር ጋር የሊኪውድ ጋዝ አቅርቦት ለማግኘት ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ ውል ማሰሯ በርካቶችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል፡፡ ዴኒማርክ እና ጀርመን ግን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ባሰሙበት ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አቋም ሳያሳዩ ከምድባቸው በጊዜ በመውደቅ ነበር ዶሃን የተሰናበቱት። ከዚህም ባለፈ ኢራናዊያን መንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲያሳዩ ሞሮኮ በበኩሏ ለፍልስጤማዊያን የድጋፍ ድምፃቸውን አሰምተዋል። የኳታሩ ውድድር ክብረ-ወሰን የሆነ ወጪ የወጣበት ብቻ ሳይሆን ፊፋም ሪከርድ የሆነ ገቢ ያጋበሰበት ሆኖ አልፏል። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላም ቢሆን ስደተኛ ሰራተኞች በቂ የካሳ ክፍያ አላገኙም በሚል ንትርኩ ማቆሚያ ባይገኝለትም በመካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር የተካሄደው የዓለም ዋንጫ ግን እግርኳሳዊ በሆኑ መመዘኛዎች እንከን የማይወጣለት ፣ ብዙዎችን ባስማማ መልኩ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲናን ያነገሰ ፣ የተመልካች ድርቅ ያልመታው ፣ ትልልቆቹ ቡድኖች ካልጠበቁት ቅዠት ጋር የተላተሙበት አስደናቂ ውድድር መሆን ችሏል።
