በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ግሽበት መጠን እየቀነሰ ቢመጣም፣ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሸቀጦች ዋጋ በዝቅተኛ ገቢ የሚኖሩ ዜጎችን የመግዛት አቅም እያዳከመ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው አዲስ የኢኮኖሚ ሪፖርት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የዓለም ኢኮኖሚ እድገት እ.ኤ.አ. በ2026 ወደ 2.7 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት ከነበረው የ3.2 በመቶ አማካይ እድገት በታች ነው።
የተመድ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሊ ጁንሁዋ እንደገለጹት፣ የዋጋ ግሽበት ቁጥር መውረድ ብቻውን በቤተሰቦች የኑሮ ደረጃ ላይ ለውጥ አያመጣም። ለዚህም መንግሥታት መሠረታዊ ወጪዎችን መጠበቅ፣ የገበያ ውድድርን ማጠናከር እና ለተደጋጋሚ የዋጋ ንረት መንስኤ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮችን መፍታት ይኖርባቸዋል።
በተለይ የምግብ፣ የኢነርጂ እና የሎጂስቲክስ ዘርፎችን የማምረት አቅም በማሳደግ የአቅርቦት ሰንሰለትን ማጠናከር የዋጋ ጫናን ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረት እየጨመረና አገራት ወደ ራሳቸው ብቻ የሚያተኩሩ የንግድ ፖሊሲዎችን እየተከተሉ ባለበት ወቅት፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብር እየደከመ መምጣቱ ለዓለም ኢኮኖሚ ተጨማሪ ስጋት ሆኗል።
ሪፖርቱ አገራት የዋጋ ጫናን ለመቋቋም የገንዘብ፣ የፊሲካል እና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎቻቸውን አስተሳስረው መምራት እንዳለባቸው አሳስቧል።
በስፔን ሴቪያ በተካሄደው አራተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮንፈረንስ ላይ የጸደቀው የ”ሴቪያ ስምምነት” ለዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት እንደ አዲስ መመሪያ ተቀምጧል። ይህ ስምምነት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማሻሻል፣ የታዳጊ አገራትን የዕዳ ጫና ለመቀነስ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የሚውል የገንዘብ ድጋፍን ለማሳደግ ያለመ ነው።
የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር ረገድ የተገኘው ስኬት ወደ እውነተኛ የኑሮ መሻሻል እንዲቀየር፣ አገራት ከመነቃቀፍ ይልቅ በጋራና በተቀናጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ተመድ ጥሪውን አቅርቧል።
