የ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በቅድመ-ምርጫ ወቅት መከናወን ያለባቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።
ሆኖም በጋምቤላ ክልል ለሚካሄደው ምርጫ የጸጥታው ሁኔታ እክል እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚፈልግ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታውቋል።
የክልሉ የጋራ ምክር ቤት አባል እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአቅም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሳይመን ቱት ምርጫው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤
በክልሉ ምክር ቤት ስር አምስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚገኙና አራቱ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቀዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹም በተናጠል እያከናወኑዋቸው ያሉ ተግባራት እንዳሉ ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን ፓርቲዎቹ ለምርጫው ዝግጅት ለማድረግ ጥረት ላይ ቢሆኑም፣ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው አቶ ሳይመን ቱት ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ቢያደርግም፣ በጸጥታ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ክልሎች ጊዜው እንዲራዘም ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
