ተጨማሪ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የላኩት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከኢራን ጋር ንግግር የማድረግ እቅድ እንዳላቸው ተናገሩ። የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በበኩላቸው ሠራዊቱ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በሚያሳልፉበት ወቅት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ትራምፕ ኢራን ላይ ለማድረግ ስላቀዱት ንግግር ይዘት፣ መቼ ሊካሄድ እንደሚችል አልያም ዋሺንግተን ድርድሩን ትመራው እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
ትራምፕ ከቴህራን ጋር ሊደረግ ስለሚችል ድርድር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ “እያቀድኩበት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። “በአሁኑ ሰዓት በጣም ግዙፍ፣ በጣም ኃይለኛ የሆኑ መርከቦቻችን ወደ ኢራን እየቀዘፉ ነው። እነርሱን መጠቀም ባይኖርብን በጣም ጥሩ ይሆናል” ማለታቸውን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ትራምፕ፤ ኢራንን ማጥቃትን በተመለከተ አማራጮቻቸውን እያዩ ቢሆንም ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል። የአሜሪካ እና ኢራን ውጥረት ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ እንደገና ያገረሸው የቴህራን እስላማዊ መንግሥት በተቃዋሚዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት፤ ኢራን ተቃዋሚዎችን መግደሏን የምትቀጥል ከሆነ እርምጃ እንደሚወስዱ ሲዝቱ ቆይተዋል። በኢኮኖሚ መላሸቅ እና ፖለቲካዊ አፈና ምክንያት በመላው አገሪቱ የተነሳው ተቃውሞ ባለፉት ቀናት ረግቧል።
የእስራኤል እና የአሜሪካ ኃይሎች ሰኔ ውስጥ በዋና ዋና የኒውክሌር ተቋማቷ ላይ የአየር ጥቃት የፈጸሙባት ኢራን፤ በድጋሚ የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንደገና የምታስቀጥል ከሆነ ዋሺንግተን እርምጃ እንደምትወስድ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።
ለሰሞኑ ደግሞ ከፍተኛ የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ተሰባስቧል። የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሄግሴት የኢራን ሁኔታን በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ በትራምፕ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
የትራምፕ አስተዳደር የመከላከያ ሚኒስቴርን ስያሜ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ “የጦርነት ሚኒስቴር” ብሎ መቀየሩን ያስታወቁት ሄግሴት፤ “የኒውክሌር አቅም ሊኖራቸው አይገባም። ፕሬዝዳንቱ ከጦርነት ሚኒስቴሩ የሚጠብቁትን ማንኛውንም ነገር ለማቅረብ ዝግጁ ነን” ብለዋል።
