”ይህ ድርጊት ዓለም አቀፍ ህግን እና የቬንዙዌላን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሰ ነው” – ሮድሪጌዝ
ቀደም ሲል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዴልሲ ሮድሪጌዝ ወደ ሩሲያ ኮብልለዋል ተብሎ ሲነገር ነበር።
የቬንዙዌላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕገ-መንግሥት ምክር ቤት ቅዳሜ ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲረከቡ አዘዘ። ይህ እርምጃ የተወሰደው የአሜሪካ ኃይሎች ኒኮላስ ማዱሮን በትናነት ማለዳ ወታደራዊ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ነው።
በፍርድ ቤቱ የውሳኔ መግለጫ ላይ፣ ሮድሪጌዝ “የአስተዳደር ቀጣይነትን እና የሀገሪቱን አጠቃላይ መከላከያ ለማረጋገጥ ሲባል የቬንዙዌላ ቦሊቫሪያን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤትን” እንደሚረከቡ ተገልጿል።
የሕገ-መንግሥት መሠረት
በቬንዙዌላ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 233 እና 234 መሠረት፣ ፕሬዝዳንቱ በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት ከሥራቸው በሚለዩበት ወቅት ስልጣናቸው በምክትል ፕሬዝዳንቱ ይተካል።
በተመሳሳይ የፋይናንስ እና የነዳጅ ሚኒስትር ሆነው የሚያገለግሉት ሮድሪጌዝ፣ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አዲሱን ኃላፊነታቸውን በይፋ ተረክበዋል። ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ ሮድሪጌዝ የብሔራዊ መከላከያ ምክር ቤት ስብሰባን መርተዋል።
ማዱሮ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሮድሪጌዝ ጋር መነጋገራቸውን እና እሷም ከዋሽንግተን ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸው ነበር።
ሆኖም ሮድሪጌዝ በይፋዊ ንግግሮቿ ለአሜሪካ የመለሳለስ ምልክት አላሳየችም። ከአሜሪካ ጋር የመተባበር እድልን ውድቅ ያደረገች ሲሆን፣ ማዱሮ አሁንም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥታለች።
”በዚህች ሀገር አንድ ፕሬዝዳንት ብቻ አለ፣ ስሙም ኒኮላስ ማዱሮ ሞሮስ ይባላል” — ዴልሲ ሮድሪጌዝ
ዴልሲ ሮድሪጌዝ ማን ናቸው ?
ዴልሲ ኤሎይና ሮድሪጌዝ ጎሜዝ (56)፣ በቬንዙዌላ ማዕከላዊ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ በመንግሥት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ቁልፍ ሰው ሆነው ቆይተዋል። ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ በሟቹ ሁጎ ቻቬዝ የተመሰረተው እና በማዱሮ የቀጠለው የ”ቻቪስሞ” ፖለቲካ ንቅናቄ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተወካይ ናቸው።
ሮድሪጌዝ ቀደም ሲል የሚከተሉትን ዋና ዋና ኃላፊነቶች መርተዋል፦
የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር በፈረንጆቹ (2013–2014)
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (2014–2017)
የሕገ-መንግሥታዊ ጉባኤ ፕሬዝዳንት (2017)
ተንታኞች እንደሚሉት፣ ሮድሪጌዝ በስልጣን ላይ መቆየቷ ከምዕራባውያን ጋር ያለው ግንኙነት ይለሰልሳል ማለት አይደለም። ይልቁንም እርሷ በስርዓቱ ውስጥ ካሉ እጅግ ጠንካራ እና የማይንቀሳቀሱ ሰዎች አንዷ እንደሆነች ይገለጻል።
