ግብታዊው የልዩ ኃይል ፍርሰት ለምን?

Date:

በሀገራችን ታሪክ ከአንድ እውቅና ካለው ሀገር አቀፍ የጸጥታ ተቋም ውጭ ተጨማሪ ኃይል የተቋቋመው በዘመነ ኢህአዴግ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት ይህን ያደረገው ያለ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ነው፡፡ ይህ በመኾኑ ደግሞ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ “ልዩ ኃይል” የተሰኘው የጸጥታ አደረጃጀት ተቋም በበርካቶች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትና ትችት ሲሰነዘርበት ነበር፡፡ የኾኖ ኾኖ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቀድሞ የነበረው የውግዘትና ትችት ምልከታ ተቀይሯል፡፡ ለእይታው መቀየር ደግሞ በርካታ ሰበበ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሰሞኑን የፖለቲካው አየር በሀገሪቱ ልዩ ኃይል አባላት ላይ አነጣጥሯል፡፡ ይህ የኾነው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በደረሰበት የልዩ ኃይል ይፍረስ ውሳኔና ለዚህ መሳካትም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ ነው፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎች የቡድን መሣርያዎችን ለመከላከያ እንዲያስረክቡ እና ወደ መደበኛ ፖሊስና ወደ ማረሚያ ቤት ፖሊስ እንዲቀየሩ ወስኗል። ኾኖም ግን “ይህ ውሳኔ ጊዜውን ያልጠበቀ፤ ፍፁም ኃላፊነት የጎደለው፤ በተለይም ጥቃት ያንዣበበበትን ሕዝብ ለማስመታት ያለመ አደገኛ ወሳኔ” ሲሉ በርካቶች ውሳኔውን አጣጥለውታል። አልፎም በተለይ በአማራ ክልል ውሳኔውን የሚቃወም ሰልፍ ተካሂዶበታል፡፡ አልፎም ልዩ ልዩ የአመጻ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

የብልጽግና መንግሥት ለዚህ ውሳኔ በመርህ ደረጃ ምክንያት አድርጎ ያስቀመጠው ከፍ ሲልም እንደተነሳው “ልዩ ኃይል ለአገር ደህንነት አስጊ ስለኾነ መፍረስ አለበት” የሚለውን የቆየ የምሁራንና የሕዝብ ትርክትን ነው። ብልጽግና ይህን መርህ የተከተለው ፖለቲካ ለመሥራት እንጅ መርኁን አምኖበት አለመኾኑ ግልጽ ነው፡፡ አሁን እየሄደበት ያለውም ቢኾን መርኅን ተከትሎ ነው ለማለት አያደፍርም፡፡ ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ፣ ቅድመ ሁኔታን ያላሟላ እንዲሁም የንግሥና ዙፋንን ለማጽናት ሲባል የሚደረግ ውሳኔ ነው፡፡ በእርግጥ በተለይም የአማራ ልዩ ኃይልን ማፍረስ ቀድሞውንም የነበረ እና ቀን ሲጠበቅለት የቆየ ጉዳይ እንደነበር በርካታ አመላካች ነገሮች ነበሩ፡፡ ውሳኔው በዋናነት የአማራ ሕዝብን ቀውስ አሁን ካለበት የባሰ የሚያያደርግ መኾኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ገና ከጅምሩ በርካታ ነውጦችን እየወለደ ይገኛል፡፡ እንደሀገር የሚያስከፍለው ዋጋም ቀላል እንደማይኾን ግልጽ ነው፡፡ 

ከዚህ አንጻር በዚህ የተዛባ ውሳኔ ላይ የተሳተፈው አመራር በሙሉ በቀጣይ ለሚፈጠር አገራዊ ትርምስ እና የሕዝብ ጥቃት ተጠያቂ ሊኾን እንደሚችል ሊያምንበት ይገባል፡፡ ውሳኔው ያለጥናትና ሀገር ባልተረጋጋችበት ጊዜ የተወሰነ በመኾኑ ገና ከጅምሩ ብዙ ሽብርና መናጦች እየተስተዋሉበት ነው፡፡ ምንም እንኳን የብልጽግና መንግሥት ውሳኔው ጥናትን ተመርኩዞ የተወሰነ መኾኑን ቢያሰምርበትም የመሬቱ ሀቅ ግን ያንን አያረጋግጥም፡፡ “ልዩ ኃይሉን ለማፍረስ ሳይኾን በአዲስ መልክ ለማደራጀት ነው” የሚለው ለበጣዊ የመንግሥት ማብራሪያ ለዶሮ ገላ ማጠቢያ ውሃ እንደማሞቅ ዓይነት ማሞኛ ነው፡፡ የኾኖ ኾኖ አንድን የተደራጀና የታጠቀ ኃይል መበተን እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ዙሪያ የዓለም ተሞክሮም የሚያሳየው ሂደቱ ምን ያህል ከባድና እልቂትን አቀጣጣይ እንደኾነ ነው፡፡ በአሜሪካ በ1830 ላይ “The Native American Removal Act” በመባል የሚታቀው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ያስከተለውን ምስቅልቅስና የበርካታ ሰዎች ሞት ታሪክ የመዘገበው የዓለም መማሪያ ነው፡፡ ጃፓንም “ናንኪንግ” የተሰኘውን የቻይና ከተማ ከተቆጣጠረች በኋላ በአካባቢው ሰላም ሰፍኗል በማለት የከተማውን ነዋሪና ታጣቂ ትጥቅ በማስፈታቷ ከ20ሺህ በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሰለባ እንዲኾኑ መዳረጋቸውን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በአህጉራችን በሩዋንዳም ከዘግናኙ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በፊት የተደረገው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ፤ እና እርሱን ተከትሎ የመጣው ቀውስና ጭፍጨፋ ሀገሬው ብቻ ሳይኾን ዓለም ዛሬም ድረስ በራሱ የሚያፍርበት ዘግናኙ ታሪክ ነው፡፡

ስለዚህ ቢያንስ ይፍረስ የተባለው ልዩ ኃይል ከመፍረሱ በፊት አሁን ካለው አለመተማመን አንጻር በመጀመሪያ የመከላከያ፣ ሪፐብሊካን እና የፌደራል ፖሊስ በብሔር ስብጥር ደረጃ ኮታውን ያሟላ መኾን ይኖርበታል፡፡ እነዚህ 3 ተቋማት አብዛኛው ፐርሰንታቸው አሁን ላይ በአንድ ብሔር የበላይነት  የተያዙ ናቸው። ለዚህ ማሳያ ይኾን ዘንድ ከዓመታት በፊት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍትሕ መጽሔት አንደኛ ዓመት ቁጥር 18 መጋቢት 2011 ዓ.ም ላይ እንዳሰፈረው በወቅቱ የነበሩት የመከላከያ አራቱ ዕዞች ከሚያስፈልጋቸው 16 ዋናና ምክትል አዛዦች ውስጥ ከ6 በላይ የሚኾኑት ወንበሮች በአንድ ብሔር የተያዙ ሲኾን በሥራቸው ባሉ ስድስት ቁልፍ ቦታዎች ላይም ስድስቱም በዚሁ አንድ ብሔር ብቻ የተያዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ስብጥር ባለተመጣጠነበት ሁኔታ ልዩ ኃይልን ማፍረስ የአፓርታይድ ሥርዓት መገንባትና በመቋጫው ሀገርን ለብተና መዳረግ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ አገራዊ መግባባት (reconciliation) ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከ1972 እስከ ዛሬ በወያኔ፣ ወያኔ ባቋቋመው የኢህአዴግ መንግሥት እና በብልፅግና መንግሥት ለተፈፀሙ የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀሎች ተጠያቂነት ሳይሰፍን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ወንጀል የፈፀሙ አካላት ሳይጠየቁ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላምና መተማመን ሳይረጋገጥ ልዩ ኃይልን ማፍረስ አደጋው የከፋ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ምናልባትም ቢደረግ ምክንያታዊ እና መልካም ሊኾን የሚችለው በልዩ ኃይሉ ላይ የትጥቅ አቅም ገደብ ማበጀት ነው። ይህም ደግሞ አሁን እንደምናየው በአንድ ክልል ላይ ባነጣጠረ መልኩ ብቻ ሳይኾን በሁሉም ክልሎች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይህ ካልኾነ ግን በተለይም ሰሞኑን እንደምናየው በአማራ ልዩ ኃይል ላይ ብቻ ይህ እርምጃ የሚወሰድ ከኾነ ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የጃፓኖች ታሪክ ዓይነት ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ የሩዋንዳው ዕጣ እንደማይገጥም ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ዝም ብሎ “ሁሉም ክልሎች ልዩ ውሳኔውን ይፈጽማሉ” የሚል የታይታ መግለጫ በማውጣትና በተለይም የፈረሱ ክልሎችንና ልዩ ኃይል ያላደራጁ አዲስ ክልሎችን መግለጫ በማስወጣት ብቻ ሕዝብን ማደናገር አይቻልም፡፡

የብልጽግና መንግሥት ይህን አደገኛ ውሳኔውን የወሰነው ዓይኑን ያልሸፈነ ሁሉ እንደሚያውቀው በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ታጣቂዎች መሣርያ ሳያወርዱ፤ ይልቁንም እንደ ትህነግ ያሉት የጥፋት ኃይሎች ተጨማሪ ሠራዊት እያሰለጠኑ እና በየአካባቢው ጥቃት እየፈፀሙ ባሉበት ወቅት ነው፡፡ ከዚሀ አኳያ በዚህ ውሳኔ ውስጥ የታለመው ሴራ ሕዝብን ያለ ፀጥታ ኃይል ከለላ የጥቃት ሰለባ ለማድረግ ከመቋመጥ የመነጨ መኾኑን ያረጋግጣል። ለአገር ሕልውናና ዘላቂ ሰላም ቢታሰብ ኖሮ ከማንም በፊት ትጥቅ መፍታት የሚገባቸው በአገርና በሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት የፈፀሙትና እየፈፀሙ ያሉት የህወሓትና ኦነግ ሸኔ መሳሪያ አንጋቢ ኃይላት ነበሩ፡፡ እየኾነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ሀገር አደጋ ላይ ወድቃ በነበረ ጊዜ ዋጋ ከፍሎ የመንግሥቱን ሥልጣን ያራዘመ ሀገርን ከፍርሰት ያዳነ በዋናነት የአማራ፣ ሲቀጥል የአፋርና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ማፍረስ ነው፡፡

ወያኔ መከላከያን መትቶ ሀገር ሲወር የመከተን የአማራና የአፋር ልዩ ኃይልን፤ አልሸባብ ሶማሌ ክልልን ሲወርር የመከተን የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ይፍረስ ማለት ጸባቸው ከአማራ ወይም ከአፋር ጋር ብቻ ሳይኾን ከኢትዮጵያ ጋር እንደኾነ መረዳት መልካም ነው፡፡ በተለይም አሁን ላይ  የህወሓት ኃይል ለጦርነት እየተዘጋጀ መኾኑ እየታወቀ የአማራና አፋር ልዩ ኃይል ይፍረስ ማለት ለእርድ ተመቻች ማለት መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰሞኑን እነ ጌታቸው ረዳ በአዲስ አበባ በነበራቸው ጫጉላ አንድ ስብሰባ ላይ “ታጣቂያችሁን ትጥቅ አላስፈታችሁም” ሲባሉ “ከእኛ አቅምና ፍላጎት ውጭ ኾኖ ለጦርነት እየተዘጋጀ ያለ ኃይል እንጂ የእኛ አይደለም። ከእኛ በተቃራኒ የቆሙና ጦርነት የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው ይህን እያደረጉ ያሉት” ማለታቸው እየታወቀ ፖለቲካ ያጎራበጣቸው ክልሎችን እርስ በእርስ ለማገዛገዝ ካልኾነ በቀር በዚህ ወቅት ልዩ ኃይል ፈረሳው ምክንያታዊ ሊኾን አይችልም፡፡ በዋናነት ደግሞ የትግራይና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ሳይፈርሱ እንዲሁም መከላከያው በድፍን ኢትዮጵያውያን ተዐማኒነትን ሳያገኝ ፍረሱ ማለት ከላይ እንደተጠቀሰው በብዙ ምክንያት ዋጋ ያስከፍላል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...