የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሬድዮ መገናኛ አቅሙን በማሳደግ እና አዳዲስ ዘመናዊ ሬዲዮኖችን በማሟላት፤ በራስ አቅም ያበለፀጋቸውን ሦስት የፖሊስ ሲስተም ሶፍትዌሮችን በይፋ አስመርቆ ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፖሊስ ኮሙዩኒኬሽን ሲስተሙን የበለጠ ለማሳለጥ ዘመናዊ ሬዲዮኖችን በማሟላት፤ የሬድዮ መገናኛ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ በማዘመንና ተደራሽነቱን ይበልጥ በማስፋት በራስ አቅም ያበለፀጋቸውን የቅድመ ጥንቃቄ ሥርዓት ሲስተም፣ የጦር መሣሪያ አስተዳደር ሲስተም እና የኤግዚቢት አስተዳደር ሲስተም ሶፍትዌሮችን በዋናው መሥሪያ ቤት በይፋ በማስመረቅ ወደ ሥራ አስገብቷል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ኢትዮጵያ በ2030 በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችውን ከፍተኛ ጥረት እንዲሳካ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም አገልግሎቱን በየጊዜው ዲጂታላይዝ በማድረግ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሲስተም ሶፍትዌሮች በራስ አቅም እያበለፀገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ኮሚሽነሩ ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡት ቴክኖሎጂዎች አስቀድሞ ወንጀል ለመከላከል፣ ተፈፅሞ ሲገኝም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ከመያዝ ባለፈ የፖሊስን የማድረግ አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ በመሆናቸው አመራሩ ይህንን አውቆ ራሱን ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር ማላመድ እንዲችል በቀጣይ ሥልጠናዎች እንዲዘጋጁ የሥራ መመሪያ መስጠታቸው ተጠቁሟል።
ሲስተሞችን ላሻሻሉና ላበለፀጉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለወጣት ፖሊስ ባለሙያዎች ኮሚሽነር ጀነራሉ በራሳቸውና በፖሊስ ሠራዊቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በተጨማሪም ዘመናዊ የሬድዮ መገናኛዎቹ ለታለመለት ዓላማ እንዲውሉ አሳስበው ከታኅሳስ 21 ቀን ጀምሮ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ማስረከባቸው ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
