Home ዕይታ ፕሬዚደንትኢሳይያስቂማቸውንእንዴትተወጡት?

ፕሬዚደንትኢሳይያስቂማቸውንእንዴትተወጡት?

ፕሬዚደንትኢሳይያስቂማቸውንእንዴትተወጡት?

ጌታቸው መላኩ

አብይና ጌታቸው (እንደ መግቢያ)

“የህወሓት ሰዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ኮይሻ ኬላ ላይ ተገናኝተው ተነጋገሩ” የሚለውን ዜና ዛሬ በትኩረት ተከታተልኩት፡፡ ሰሞኑን ካለው የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ውጪ ትኩረቴን የሳበው ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ዜናውን ስሰማ ቀድሞ ወደ አእምሮ የመጣው የአንድ ወዳጄ ትንቢት መሳይ ንግግር ነው፡፡ ወዳጄ “ጌታቸው ረዳ ህወሓትን ወክሎ መግለጫ ለመስጠት በወጣ ቁጥር ነጥብ ጥሎ ይወርድ ነበር” ብሎ ያምን ነበር፡፡ “ይህም ለፌደራል መንግሥቱ ጥሩ የፖለቲካ ድል ግብዓት ሆኖ ያገለግላል” እያለ በትኩረት ሲያስረዳኝ ልክ ዛሬ የሆነ ያህል ትዝ ይለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ወዳጄ “ጌታቸው ከዐቢይ ጋር እየሰራ መሆኑን ያሳያል” ብሎ እንዲደመድም አድርጎት ነበር፡፡ ወዳጄ ይህንን ነገር ለበርካታ ጊዜያት እንደነገረኝ እገምታለሁ፡፡ ዛሬ ያየሁት ይህ ትንቢት መሳይ ነገር በእውነት ተፈጸመ እያልኩ ነበር፡፡

በዜናው ላይ ጌታቸው ረዳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጎን ተቀምጦ ማብራሪያ ሲሰጥና ሲያዳምጥ ተመለከትኩት፡፡ በመቀጠልም በኢቢሲ ላይ ለቃለ መጠይቅ ተጋብዞ ሐሳቡን ሲያካፍል ተመለከትኩት፡፡ ወይ ጊዜ ደጉ! ጠባቂዎቹ በድንገት በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት ሲያልቁ “በተአምር ተረፍኩ” ያለን ሰውዬ ዛሬ ከሀገሪቱ ቁንጮ ባለሥልጣን ጋር ቁጭ ብሎ ሲወያይ አየሁት፡፡

ጌታቸው በቀጥታ ዐቢይ አሕመድ ላይ ከተናገራቸው ነገሮች ሁሉ በአስቂኝ መልኩ የማስታውሳቸው “ዐቢይ የሕዳሴውን ግድብ ሽጦታል … ዐቢይን ፑቲን አያድነው፣ ኤርዶጋን አያድነው፣ ሳዳም አያድነው… ዐቢይ አሳምነው ጽጌን አስገድሎታል … ዐቢይ ቀጣፊ ነው… ዐቢይ….” ወዘተ…

ጦርነቱ እንደ መንገድ

እነሆ አሁን ጊዜ አለፈ፣ ጦርነቱም አለቀ፣ ወታደሩ ዘለቀ፣ ንጉሶች ግን ታረቁ፡፡ ለነዋሪ ያልፋል የሞተ ተጎዳ አይደል አባባሉስ የሚለው፡፡ ባለፈው አንድ ስሙን የማላስታውሰው በጦርነቱ በነበረው ተሳትፎና ባበረከት አስተዋጽኦ ምክንያት በመከላከያ የከፍተኛ ጀብዱ ሜዳይ ተሸላሚ የነበረ የመቶ አለቃ ወታደር አሳዛኝ ሁኔታን ተመልክቼ ነበር፡፡ ቆፍጣናው ወታደር ቁስሉን ይዞ ሰሜን ሸዋ አካባቢ አንዲት ቤት ተከራይቶ በዚያ ቅዝቃዜ እየተሰቃየ፣ ደረቱ ላይ ካለችው ሚዳሊያና ልቡ ውስጥ ካለችው የሀገሩ ፍቅር ውጪ ምንም ነገር እንደሌለው ሲናገርም ሰማሁት፡፡ ልቤ እጅግ አዘነ፡፡ ወታደር የመሆን የልጅነት ፍላጎቴ በደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ ውስጥ ተመልምዬ ከነበረኝ የቀናት ቆይታ በላይ አልዘለቀም፡፡ ይህ ወታደር ከጠላት ጋር ያደረገው ትንቅንቅ ግን በዐይነ ሕሊናዬ ውስጥ ተስሎ ይገኛል፡፡

ለማንኛውም ጦርነቱ ተጠናቀቀ፡፡ የቀድሞ ኮሎኔል ቢኒያም አመነ እንደተባለው ህወሓት በጦር ሜዳ ብልጫ ተወስዶበት እጁን ተጠምዝዞ የሰላም ስምምነቱን ፈረመ፡፡ በገባው ስምምነት መሠረትም ከጥቂት አፈንጋጮች ውጪ ቀላልና ከባድ መሣሪዎችን አስረከበ፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱን አፍንጫ ይዘን በጉልበት ፍላጎታችንን እናሳካለን የሚለው የደብረጽዮን ፉከራ አሁን የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ ነገር ተነነ በነነ፡፡ ህወሓት ያደረገው የ2012 ምርጫ ትክክል አይደለም ብሎ አምኖ እሰርዛለሁ አለ፡፡ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች ጋር የሽግግር አስተዳደር በትግራይ ለማቋቋም ተስማማ፡፡ የተለመደው ሁሉም የኔ ብቻ ይሁን የሚለው ባህርዩ በቀላሉ ባይለቀውም ቅሉ በሽግግር አስተዳደሩ ውስጥ አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ለመቆየት እየሞከረ ነው፡፡ በውስጡ የአጋጅ ታጋጅ ድራማንም እያተናገደ ነው የሚሉ መረጃዎች አልፈው አግድመው ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን በርካቶች የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር ከዚህ ስምምነት ህወሓት አንድ የተረፈው ትልቅ ነገር በሕይወት መቆየት ነው፡፡ በእኔ ግምት ደግሞ በታሪክ ሂደት እንደታየው ቀዳማይ፣ ካልአይ እያለ እንደመጣው የሳልሳይ ወያኔ ጊዜው ያለፈ ስለሚመስልኝ የራብአይ (አራተኛ) ወያኔን መምጣት አስባለው፡፡

የፕሬዚደንት ኢሳይያስ በቀል

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በዚህ ጦርነት ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሳል የፖለቲካ ልምድና እውቀታቸውን ተጠቅመው፤ ልምድና እውቀት የሚያንሰውን ዐቢይን ፈረስ አድርገው ህወሓቶችን ተበቀሏቸው፡፡ አንድ ወዳጄ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሲናገር የሰማሁት ዜና እውነት ከሆነ ይህ ድርጊት የወያኔ ሰዎችን መበቀል መዳረሻው ይምሰል እንጂ ሌላ አንድምታ ያለው ይመስለኛል፡፡ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ ጉምቱ የሚባሉትን የህወሓት አመራሮችን ሳይቀር እንደውሻ በረሀ ለበረሀ አባረው ግምባር ግንባራቸውን ብለው በሞራልም በሥጋም ገደሏቸው፡፡ ሥዩም መስፍን፣ ዓባይ ፀሐዬ፣… ሌሎችም አሉበት ይባላል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ መንገዶች ሲዘዋወር የነበረው የሥዩም መስፍን አገዳደልን የሚያሳየው ፎቶ እንኳን ለወዳጅ ለማያውቅ ግለሰብም ያሳዝናል፡፡ ሥዩም መስፍን ባይሆን፣ የጦርነት ጊዜ ባይሆን፣ በአንድ በሰባዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ አዛውንት በዚህ መልኩ ሞቶ መታየት በወዳጅም በባዳም ዘንድ ምን ዐይነት ስሜት ይፈጥር ይሆን? ልክ ነው ጦርነት መጀመሪያው እንጂ ማለቂያው አይታወቅም፡፡ ስለዚህ የሰሜን ዕዝን ህወሓት ስለመታ ተጀመረ የተባለው ጦርነት፣ በርካታ የትግራይን፣ የአማራንና የአፋርን ክልል አውድሞ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጎ፣ በርካታ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ምስቅልቅል ፈጥሮ በረደ ተባለ፡፡

ታዲያ ከዚህ የጦርነት ገበያ ዋና አትራፊ ሆኖ ማን ወጣ? ቢባል የዚህ ጽሑፍ መልስ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በግልም በሀገርም ተጠቅመዋል እላለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ህወሓቶችን የተበቀሉበት መንገድ እጅግ ደስተኛ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል፡፡ የኢሳይያስ በቀል በቀሩት የህወሓት አመራሮችም ላይ ታቅዶ እንደነበር የሚወራው ወሬ ደግሞ ሲሰማ ደብረጽዮን “ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ ለሰላም ስምምነቱ ያደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለሆነ አመሰግናቸዋለሁ” የምትለዋ ንግግር አንደምታዋ ብዙ ነው፡፡

ኢሳይያስ እንዴት አጋጣሚውን ተጠቀሙበት?

እውቀት፣ ልምድ እና መረጃ ለፖለቲካ ስኬት ቁልፍ ይመስሉኛል፡፡ ኢሳይያስ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ መቆየታቸው ቢያንስ ከእድሜ የሚገኝ ልምድን ያስገኝላቸዋል፡፡ በመቀጠል በሥልጣንና በተጽእኖ ፈጣሪነት በቆዩበት ጊዜ ያገኙት መረጃ ቀላል የሚባል አይመስለንም፡፡ የስለላና ደህንነት ሥራ የሚያስገኘው አበርክቶ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሚደርጋቸው እሙን ነው፡፡ የሁለቱ ድምር ደግሞ በክልሉም ይሁን በአህጉሩ ያላቸውን የፖለቲካ እውቀት ሊጨምር እንደሚችል ለመናገር አዋቂ መሆን አይጠይቅም፡፡ በመሆኑም ኢሳይያስ እነዚን ልዩ ግብአቶችን በመጠቀም ህወሓትን ተበቀሉ፡፡ በተለይም በእርሳቸው እድሜ ክልል የሚገኙ ጠበኞቻቸውን ፊት ለፊት አግኝተው መሆኑ የሚገርም አጋጣሚ ይሆንብኛል፡፡

ነገር ግን ለዚህ አጋጣሚ መሳካት ከኢሳይያስ እውቀት፣ ልምድና መረጃ ባልተናነሰ የዐቢይ አሕመድ የነዚህ ነገሮች በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ለኢሳይያስ እድል ከፍቶላቸው እንደሆነ መከራከር አመክንዮአዊ ይመስለኛል፡፡ ልምድ፣ እውቀትና መረጃ ይዞ የሚወለድ ማንም የለም፡፡ ነገር ግን በቅርበት የሚገኙ አጋጣሚዎችን በመጠቀም፣ በኩነቶችና ክንውኖች አካባቢ መኖር የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ለማግኘት እንደሚጠቅም እሙን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የአጋጣሚ ክስተት ያህል የሚታዩ ናቸው፡፡ ፖለቲካ በተአምር፣ በትንቢትና በእምነት ይሆናል ብዬ የማምን ሰው ስላልሆንኩ፣ ዐቢይ እናቴ ስለተነበየችልኝ ስዘጋጅ ቆይቻለው የሚለውን ተረክ የምገዛው አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም በቅርበቴ ያህል እውቀት ልምድና መረጃ አዳብሬአለሁ ቢሉኝ የምቀበለው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን በመነሻዬ ላይ እንዳስቀመጥኩት ከኢሳይያስ ልምድ፣ እውቀትና መረጃ ጋር ለውድድር መቅረቡ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የሆነ ሆኖ በእኔ እይታ ኢሳይያስ ይህንን ልምዳቸውን ተጠቅመው ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ የቆውን በህወሓት ላይ ያላቸውን በቀል ተወጡ፡፡