
የወንዝ ዳርቻ ልማት በኬንያ ናይሮቢም ተጀመረ
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የናይሮቢ የወንዝ ልማት ፕሮጀክትን በይፋ ማስጀመራቸው ተዘግቧል – የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ዓይነት ይመስላል፡፡ በዚህም የተነሳ ይመስላል አንዳንዶች ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ አይተው ነው ፕሮጀክቱን የጀመሩት ለማለት ሰበብ የሆናቸው፡፡ ለዚህ ግን በቂ ማረጋገጫ ያለ አይመስልም፡፡ ቢያንስ ለጊዜው፡፡ ለነገሩ ከእኛም አይተው ወይም ቀድተው ቢሆን እሰየው ነው፡፡ ለአርአያነት በመብቃታችን ልንኮራ ነው የሚገባው፡፡
ወደ ዘገባው ስንመለስ፣ ግዙፉ የናይሮቢ የወንዝ ልማት ፕሮጀክት የ60 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ መስመር ዝርጋታና የ50 ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ያካትታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሩቶ በትላንትናው ዕለት የናይሮቢ ወንዞች ልማት የኢንጂነሪንግ ሥራን ያስጀመሩ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በእጅጉ የተበከሉትን የናይሮቢ ወንዞች ለማጽዳትና የከተማዋን ከባቢያዊ ሁኔታ ለማደስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በናይሮቢ ወንዝ ዳርቻዎች በ388 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የማህበራዊ መኖሪያ ቤቶች እንደሚከናወንም ተጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በትላንትናው ዕለት ሰኞ በካሙኩንጂ የምርጫ ክልል ለነዋሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ “ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም በናይሮቢ ወንዝ ማደስ ፕሮግራም ሥር ትልቅ ፕሮጀክት እየጀመርን ነው፡፡ የናይሮቢን ወንዝ ጽዱ ለማድረግ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር እንገነባለን” ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የከተማዋን ጽዳትና ንጽህና ብቻ አይደለም የሚያሻሻሽለው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይልቁንም ከ30ሺ ለማያንሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡
“ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የናይሮቢን ወንዝ ወደ መዝናኛ ስፍራ እንደምንቀይር ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።” ብለዋል፤ ሩቶ በንግግራቸው፡፡
ፕሮጀክቱ የማህበረሰብ ፓርኮችን፣ የህዝብ አዳራሾችንና የመጸዳጃ ቤቶችን ልማት እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ግንኙነት ለማስተሳሰርና ለማቀላጠፍ 44 የእግረኛና የተሽከርካሪ ድልድዮች ይገነባሉ ተብሏል፡፡
የናይሮቢ ወንዝ እድሳት ፕሮግራም፤ የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል፣ ኢኮኖሚያዊ እድሎችን ለማጎልበትና የናይሮቢን ተፈጥሯዊ ከባቢ ለመመለስ ያለመ የመንግሥት ሰፊ የከተማ እድሳት ስትራቴጂ አካል መሆኑ ታውቋል፡፡
@አዲስ አድማስ