በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ በተደጋጋሚ ይስተዋል የነበረውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ 600 ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በአቢጃታ ሐይቅ ላይ ተከናወነ፡፡
ይህ ለአገልግሎቱ የቴክኒክ ባለሙያዎች ፈታኝ የሆነው የውሀ ላይ መስመር ዝርጋታ የተከናወነው ከባቱ በ25 ኪ.ሜ ርቀት እንዲሁም ከቡልቡላ ከተማ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ከአቢጃታ ሃይቅ ሶዳ አሽ እያወጣ ለብርጭቆ፣ ለጠርሙስ፣ ለጨርቃጨርቅ እንዲሁም ለንፅህና መጠበቂያ አምራች ድርጅቶች ለሚያቀርበውና በሀገራችን ብቸኛ ለሆነው ለአቢጃታ ሻላ አክሲዮን ማህበር ነው፡፡
የአቢጃታ ሻላ አክሲዮን ማህበር ከ350 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል በመፍጠር በቀን ለ24 ሰዓት የሶዳ አሽ እያመረተ ለገበያ የሚያቀርብ አምራች ድርጅት ነው፡፡
ይሁንና አምራች ኢንዱስትሪው በአቢጃታ ሐይቅ ከመጠን ያለፈ የውሀ ሙሌት ምክንያት የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ወድቀው፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ጣቢያውም በውሃ ተጥለቅልቆ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር፡፡
ይህ ክስተት ከአካባቢው ከባድ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምሰሶ ሲቆም በንፋስ ሲወድቅና በመሬቱ ጨዋማነት ወዲያው ሲበላ፣ ተቋማችንም ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ ጥገና ሲያከናውን በርካታ ጊዜያት አልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለዚህ ችግር በዘላቂነት እልባታ ለመስጠት የመጨረሻው አማራጭ ተጠቅሞ ምሰሶውን ከመሬት ይልቅ በውሃ ውስጥ በመትከል ኢንዱስትሪው ያልተቆራረጠ ኃይል እንዲያገኝና የምርት ስራውን እንዲያከናውን ፈታኝ የሆነ ሙያዊ ጥበብን በመጠቀም በአንድ ወር ውስጥ ችግሩን መቅረፍ ተችሏል፡፡
በዚህም 7 ከብረት የተሰሩ ምሰሶዎች በውሃ ውስጥ፣ 8 ተጨማሪ የእንጨት ምሰሶዎችን በመሬት ውስጥ በድምሩ የ15 ምሰሶዎች ተከላ በማከናወን 600 ሜትር ርዝመት ያለው መስመር በአቢጃታ ሻላ ሀይቅ ላይ መዘርጋት ተችሏል፡፡
በዚህም አምራች ኢንዱስትሪው የማይጠፋና የማይዋዥቅ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ ተደርጎ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከማድረግ ባሻገር በአካባቢው ለሚገኙ 150 አባወራዎች ብርሀን እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡
ይህ ፈታኝ የሆነ የኃይል መስመር ዝርጋታ ቢያንስ ለ15 ዓመት የሚያገለግል የብረት ምሰሶ ተከላ የተከናወነበት በመሆኑ ኢንዱስትሪውን ቀጣይነት ያለው የኃይል አቅርቦት ያረጋግጣል፤ አገልግሎቱም ተደጋጋሚ ከሆነ የጥገና ስራ ያሳርፋል ተብሎ ይታመናል፡፡
(የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት)
