ሕብረት ባንክ ከአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (አፍሬክሲም ባንክ) ጋር ያለውን ስምምነት በማደስ የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የንግድ ፋይናንስ ዋስትና ማግኘቱን አስታወቀ።
የተገኘው የዋስትና ስምምነት በአፍሬክሲም ባንክ የትሬድ ፋሲሊቴሽን (AFTRAF) ፕሮግራም ስር የሚፈጸም ሲሆን፣ ሕብረት ባንክ ለሚከፍታቸው የሌተር ኦፍ ክሬዲት እና በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ለተመሠረቱ የፋይናንስ ሰነዶች ዋስትና የመስጠት አቅም ይሰጠዋል።
በዚህ ስምምነት አማካይነት ሕብረት ባንክ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር በበለጠ ቅልጥፍና ለመስራት እንደሚያስችልም ተገልጿል።
በደንበኞችና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዘንድ ያለውን ተዓማኒነት እንደሚያጎለብተው ባንኩ ገልጿል። በተጨማሪም ይህ ስምምነት የባንኩን የንግድ ፋይናንስ አቅም በእጅጉ የሚያሳድግ እንደሆነ ታውቋል።