የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ማዕቀብ ምክንያት የአቪዬሽን ችግር ለገጠማት ሩሲያ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በኪራይ ለማቅረብ ውይይት እያደረገ ነው።
ባለፈው ወር በኢትዮጵያ እና በሩሲያ ባለስልጣናት መካከል በተደረገ ስብሰባ ላይ፣ የሁለቱ ሀገራት የአቪዬሽን ትብብር እንዲስፋፋ ፍላጎት መኖሩ ተገልጿል። ከውይይቱ ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ለሩሲያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖችን በ”ዌት ሊዝ” (wet-lease) ስምምነት ማከራየት አንዱ ነበር።
ይህ የኪራይ ስምምነት፣ ኢትዮጵያ አውሮፕላኑን፣ የበረራ ሰራተኞችን፣ ጥገና እና ኢንሹራንስን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለሩሲያ የምታቀርብበት ሲሆን፣ ሩሲያ ደግሞ ለነዳጅ እና ለሌሎች ወጪዎች ብቻ ኃላፊነት የምትወስድበት ነው።
ሩሲያ ይህንን አማራጭ የምትፈልገው በምዕራባውያን ማዕቀቦች ምክንያት አዲስ አውሮፕላኖችን ወይም ለመለዋወጫ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ማግኘት ስለተቸገረች ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ120 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ ይህም የሩሲያን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያስችል የሲምፕል ፍላይት መረጃ ያሳያል።
ምንም እንኳን የውሉ ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ ባይሆኑም፣ የሩሲያ መንግስት አየር መንገዶቹ ከውጭ ሀገራት አውሮፕላኖችን በኪራይ እንዲጠቀሙ መፍቀዱ ለዚህ ውይይት አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጠው ይችላል ተብሎ ይታሰባል።
ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል