“እንኳን በዚያ ዘመን ያልኖርኩ”
መላኩ ብርሃኑ
ሰሞኑን ቀልቤን ከሳቡት ድራማዎች አንዱ “ግራ ቀኝ” የተባለው በኢቲቪ የሚተላለፍ ‘መቼቱን’ በደርግ ዘመን የፍርድ ቤት ውሎ ላይ ያደረገ ተከታታይ የቴሌቪዠን ድራማ ሆኗል። በርግጥ ክፍል ሶስት እስኪደርስና መዓዛ ወርቁ ሪከመንዴሽኗን እስክትጽፍለት ድረስ ከነመተላለፉም አላውቀውም ነበር። የመዓዛን ‘ተመልክቱት’ ግብዣ አይቼ ወደኢቲቪ ዩቲዩብ ጎራ በማለት ያመለጠኝን ሁሉ ወደኋላ ተመልሼ አየሁ።
እንደኔ ላለ… ባለበትና ወደፊት በሚኖርበት የሃገሩ ዘመን ተስፋ አጥቶ ላለፈችው ኢትዮጵያና ታሪኳ ‘እጅ ለነሳ’ ሰው እንደግራ-ቀኝ ያሉ ታሪኮች በጥሩም በመጥፎ ጎናቸውም ስሜት ይሰጡታል፣ ብዙም ያስተምሩታል። ስትፈልጉ በ ኢህአዲግኛ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” በሉኝ -ከነርግማኑም ከነበረከቱም ከዛሬ ይልቅ የድሮ ኢትዮጵያ ትሻለኛለች የምል ግጥም ያልኩ ‘ናፋቂ’ ነኝ።ይመስለኛል ፈረንጆች ‘በትዝታ ኗሪ’ (nostalgic) የሚሉት አይነት ሰው ሳልሆንም አልቀርም። ልጅነቴን ጨምሮ የድሮ የሆኑ ነገሮች በሙሉ ለኔ ዋጋ አላቸው።
ከሆኑ አመታት በፊት ቢልልኝ ሃብታሙ የተባለ አንድ ‘መራታ’ ፌስቡከር አንድ ልጥፌ ስር ገብቶ ‘ባልቴት ነገር ትመስለኛለህ’ ብሎ የኮመተውን ሳስብ አሁን ድረስ ሳቅ ያፍነኛል። … ቂቂቂቂቂ
ወደጉዳዬ ልመለስና …ግራ ቀኝን ምጥጥ አድርጌ አየሁት። ሎኬሽኑም ይሁን ቀረጻው፣ ኮስቲዩሙም ይሁን ሁሉ ነገሩ የተዋጣለት አይነት ዝግጅት ነው። በጥሩ ሁኔታ ኤዲት የተደረገ ፣ የተመልካቹን ቀልብ የሚስብ ነው። የሁሉንም ቱባ ተዋንያን ችሎታ አድንቄያለሁ። የማከብራቸው የጥበብ ሰዎች ናቸው -ዋናዎቹ ተዋንያን ።
ነገር ግን ምንም እንኳን የድራማው መነሻ የሃማ ቱማ (እያሱ) “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ” መጽሃፍ ቢሆንም ታሪኩ ከጽሁፍ ወደድራማ ሲመጣ ግን ግነቱ ገዝፎብኝ ቅር ብሎኛል።
ሁሉንም ክፍሎች ሳያቸው ታድያ ናኒዬም አብራኝ አይታለች። በመጨረሻ ግን ምን ብላ አስደነገጠችኝ? …”ሆሆ…እንኳን በዚያ ዘመን ያልኖርኩ”
ደርግን ያልኖሩበትና የማያውቁት የ27+3 ዓመት ትውልዶች ይህንን ድራማ ሲያዩ በትክክል የሚሰማቸው ናኒ የተሰማት አይነት ዘግናኝ ፍርሃት እንደሆነ አምናለሁ። እኔ እንደማስበው ግን የደርግ ዘመን “እንኳን በዚያ ዘመን አልኖርኩ” የሚባልልት አይነት አልነበረም።
ድራማው ከሚፈለገው በላይ፣ የጥበብ ነጻነቱ ከሚፈቅድለት በላይ የዚያን ዘመን የፍትህ ስርዓት ክፋትና ጭካኔ አጋኖታል ባይ ነኝ።
ምናልባት ግራ ቀኝ የሚያሳየን ችሎት ‘ወታደራዊ ትሪቢዩን ነው’ ከተባለም እንዲህ ያሉ አነስተኛ የፕሮፓጋንዳ ነክ ጉዳዮችን የሚያይ ትሪቢዩን በደርግ ዘመን ስለመቋቋሙ አንብቤም ሰምቼም አላውቅም። የጦርና ከፍተኛ የሃገር ክህደት ወንጀሎች፣ በተለይ ለከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና ባለስልጣናት ብቻ ይመስለኛል እንዲህ ያለ ችሎት የሚቋቋመውም፣ ጉዳዮቹን የሚያስችሉ ችሎቶች ይሰየሙ የነበረውም።
ነገሩ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ‘ግራ ቀኝ’ ታዲያ ምንድነው? …የምን ችሎት ነበር? …መደበኛ ፍርድ ቤት ነበር ?…
እንደሱ ከሆነ ግን ‘ዝንጀሮ ኋላዋን ዘወር ብላ ሳታይ በሰው ምንትስ ትስቃለች’ እንዲሉ ሊሆን ነው ተረቱ።ግራ ቀኝ ግጥም ያለ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው ብዬ ልወርፈው ነው።
ይህ ድራማ በዘመነ ኢህአዴግ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ “ደርግ ደርግ” እያለ ተወልዶ “ደርግ ደርግ” እያለ ለሞተው የኢህአዴግ መንግስት ‘እልል በቅምጤ’ በሆነለት ነበር።በጭብጡ ከመርካቱ የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ድራማ በሚተላለፍበት ቀን ስራ ትቶ ቁጭ ብሎ እንዲመለከተው ጭምር ትዕዛዝ ያወርድ ነበር። የደርግ ጥላቻው ራሱን ከደርግ የመረረ አድርጎ ለሰራው ለዚያ መንግስት ይህ ድራማ ጥሩ ግጣሙ ነው።
ሃሳቤን ሳጠቃልል ግን…
በኢህአዲጉ ‘የካንጋሮ ፍርድ ቤቶት’ ችሎቶችም ሆነ በአሁኑ የለውጥ ዘመን ‘ፍትህ በኢትዮጵያ ከደርግ ዘመን የተሻለ ነጻነት አግኝታለች’ ብዬ አላምንም። በርግጥ ልዩነቱ የደርጉ ዘመን ፍትህ ፖለቲካ ላይ ሲሆንበት እንደዛሬው ዙሪያ ጥምጥም ሳይሄድ … ግልጽ ያለ፣ ያለድብቅብቅና ያለማስመሰል ፊትለፊት የሚገጭ ጎምዛዛ ምች ነው።
ከዚህ ሲዘል ግን ሌሎች ወንጀሎች ላይ በጊዜው ያን ያህል የጎላ የፍትህና ርትዕ መጓደል ነበረ ብዬ አላምንም ።በተለይ እንደዛሬው ዘመን ሙስና የሚቀስጠው ፍትህ ፣ ጉቦ የሚያጨማልቀው ፍርድ ቤት፣ ባለስልጣናት በአንድ ስልክ የሚዘውሩት ችሎት በደርግ ዘመን የሃገሪቱ ችግር ነበር ብዬ አላምንም። ህዝቡም ፍርድ ቤቶች ቢያንስ ፍትህ እና ርትዕ አገኝባቸዋለሁ ብሎ እምነት የሚጥልባቸው ተቋማት ነበሩ።
የምታውቁትና የኖራችሁበት እንግዲህ ያኔን ከዛሬ እያነጻጸራችሁ ትመሰክራላችሁ። እንደኔ እንደኔ ግን …የግራ ቀኝ “ጭብጡን” ብቻ ነጥዬ ስመዝነው ውሉ ያልለየለት …አላማና ግብ የሌለው…እንደው በወደቀ ዛፍ ምሳር የሚያበዛ ‘የጠሉትን ጠልተን እናጥላላ’ አይነት ስራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ዝም ብሎ የሆነ ‘ስፖንሰርድ’ ጭብጥ።
“የወረደ የሃገር መሪ፣ የወረደ ፍርድ ቤት፣ የወረደ ዳኝነትና የዘቀጠ ጥብቅና የነገሱብን ህዝቦች ነበርን …አሁን ግን ጌታ ይመስገን ከዚህ ችግር ነጻ ወጣን” እንደሚሉ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ አይነት ምስክር ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ከዚህ በተረፈ ግን የሚኪ ልዩ ትወና፣ የአበበ ድምጽና አይኖች፣ የግሩም ግራ የተጋባ ፊትስለሚያስቀኝ ብቻ ለመዝናናት ስል አየዋለሁ።
ለማንኛውም !…በ27+3 የተወለዳችሁ ልጆች እስካሁን በኖራችሁበት እድሜ እንደናኒ “‘እንኳን ያኔ አልነበርን” የምትሉበት የዛሬ ዘመናችሁ ማንጸሪያ ማግኘት ባለመቻላችሁ በርግጥ ‘አም ሶሪ’ እላችኋለሁ።
መፍቻ!
“ግራ! ቀኝ!” የወታደራዊ ሰልፍ ትዕዛዝ
“ግራ -ቀኝ” – የፍርድ ችሎት ክርክር
“ይኸው ነው!