:
- በ5 ዓመት ውስጥ 500 ሺ ቢዋይዲ መኪኖችን ለማስገባት ታቅዷል
- የሚዲያ ባለሙያዎች የመኪና ባለቤት የሚሆኑበት ዕድል ተመቻችቷል
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ከቻይናው ቢዋይዲ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያ ጋር በመተባበር ለመኪና ፈላጊዎች 1 ነጥብ 14 ቢሊዮን ብር ብድር ማመቻቸቱን የገለፀ ሲሆን፤ በቅርቡም በአራተኛ ዙር 350 ቢዋይዲ መኪኖችን ለገዢዎች ለማስረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ዛሬ ረፋድ ላይ በስካይላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት ከዚህ ቀደም በሦስት ዙር፣ 258 መኪኖችን ለገዢዎች ማስረከቡም ተብራርቷል።
ፊንቴክ ኢንቨስትመንት፣ ቢዋይዲ መኪኖችን በቅድመ ክፍያ 950 ሺ ብር በመክፈል፣ ቀሪውን 950 ሺህ ብር ከወለድ ነፃ በሆነ ክፍያ በአምስት ዓመት ከፍሎ ማጠናቀቅ ይቻላል ብሏል።
ፊንቴክ በቅርቡ ከ20 ሺ በላይ መኪኖችን ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ የተገለጸ ሲሆን፤ ኩባንያው እስከ ፈረንጆቹ 2030 ዓ.ም ድረስ 500 ሺህ ቢዋይዲ መኪኖችን ለማስገባት ማቀዱም ተነግሯል።
ፊንቴክ በቅርቡ ምናልባትም በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ያደርገዋል ተብሎ የሚጠበቀው ቢዋይዲ መኪኖች እዚሁ የሚገጣጠሙበት ፋብሪካ ገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ በመቀሌ፣ ሐዋሳና አዳማ የሽያጭ ቢሮዎችን ለመክፈት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፊንቴክ ከዘመኑ ጋር የተጣጣሙ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በስፋት በማስገባት ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት፣ ከካርበን ልቀት ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የአየር ብክለት መከላከልና አረንጓዴ ኢትዮጵያን በታዳሽ ኃይል ማስቀጠል የሚሉ ዋና ዋና አላማዎችን ሰንቋል፤ ብለዋል ኃላፊዎቹ።
ተሽከርካሪዎቹ ሰባት አይነት ሲሆኑ፤ ለሁሉም ብራንድ አምባሳደር እንደተሾመላቸው ተነግሯል። ከዚህ ቀደም የብራንድ አምባሳደር ሆና የመረጠችው ተዋናይት ዕፀሕይወት አበበ ለምን ብራንድ አምባሳደርነቷን እንደተወች ከአዲስ አድማስ ለቀረበው ጥያቄ፤ አርቲስቷ በራሷ ፈቃድ ብራንድ አምባሳደርነቷን መልቀቋን ተናግረዋል።
በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣የቀድሞው የሔሎ ታክሲ መስራች ዳንኤል ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ አርቲስቶች፣ የንግድ ባንክና የአዋሽ ባንክ ተወካዮች፣ እንዲሁም የመኪኖቹ ብራንድ አምባሳደሮች ተገኝተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ ፊንቴክ በተለይ ለሚዲያ ባለሙያዎች ግማሹን የመኪናውን ዋጋ (950 ሺህ ብሩን) በሙያቸው ድርጅቱን ፕሮሞት በማድረግ፣ ቀሪውን 950 ሺህ ብር ደግሞ በአምስት ዓመት ውስጥ ያለወለድ እየከፈሉ የመኪና ባለቤት የሚሆኑበትን እድል ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡ በምን መልኩ ተግባራዊ ይሆናል በሚለው ዙሪያም ከባለሙያዎች ጋር የሚመክር ቡድን እንደሚዋቀር ነው የተገለጸው።
Addis Admass