የእስራኤልና የሀማስ የተኩስ አቁም የመጀመሪያ ምዕራፍ ስምምነት መደረሱን ተከትሎ፤ ዶናልድ ትራምፕ “እለቱ ለአለማችን ታላቅ ነው አሉ!”
ሀማስና እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በደስታና በኩራት ዕገልፃለሁ!
ይህ ስምምነት ማለት እስራኤል ወታደሮቿን ከጋዛ የምታስወጣበት እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ የሚደረግበት ይሆናል ሲሉ ትራምፕ ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል።
አክለውም ሁለቱም ሀይሎች በፍትሀዊ መንገድ መስተናገዳቸውንና እለቱም ለአረብና ለሙስሊሙ አለም፣ ለእስራኤል፣ ለአሜሪካ በአደራዳሪነት ሲሳተፉ ለነበሩት ግብፅ ፣ካታርና ቱርክ በአጠቃላይ ለመላው አለም ታላቅ ቀን ነው ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው እለቱን “ለእስራኤል ታላቅ እለት” ሲሉ ጠርተውታል!
ስምምነቱን ለማፅደቅ የመንግስት አካላቶችን የምንሰበስብ ይሆናል፤ ውድ ታጋቾቻችን ወደ ቤት የምናስመልስበት ይሆናል፤
በዚህ ረገድ መስዋትነት የከፈሉ የአይ ዲ ኤፍ ወታደሮችንና ሁሉም የደህንነት ባለሞያዎች ለከፈላችሁት ተጋድሎ ምስጋና ይገባችኋል፤
በዚሁ አጋጣሚ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላበረከቱት አስተዋፅኦ በጥቅሉ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ ኔታንያሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ስምምነቱን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ” በዶናልድ ትራምፕ በቀረበው የተኩስ አቁም ዕቅድ ስምምነት ላይ መደረሱ ደስታ እንደፈጠረባቸው አስታውቀዋል።”
አሜሪካ ፣ ኳታር ፣ ግብፅና ቱርክ ላሳዩት ዲፕሎማሲያዊ ርብርብ በማመስገን ስምምነቱ በአፉጣኝ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ስምምነቱ በአፉጣኝ እንዲፈፀም ፣ ታጋቾችና እስረኞች ሙሉ ለሙሉ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ ልውውጥ እንዲደረግ ፣ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግና ጦርነቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ አሳስበዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በስተመጨረሻም ለስምምነቱ ተግባራዊነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከጎን እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ሀማስ በበኩሉ የግብፅ፣ የኳታር የአሜሪካና የቱርክ ወንድሞቻችንን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብሏል።
ዘገባው የሮይተርስ ነው።
በ-የአብስራ ሚሊዮን