‹‹ሕብረተሰቡ በቂ ወተት ሳያገኝ ለውጭ ገበያ አናቀርብም›

Date:


ወ/ሮ ሳራ ሐሰን
(የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ም/ፕሬዝዳንት)
ወ/ሮ ሳራ ሐሰን በቅርቡ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው ተመርጠዋል፡፡ ወ/ሮ ሳራ ባለፉት ዓመታት በሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስኬታማ ተግባር ማከናወን የቻሉ ብርቱ እንስት ሲኾኑ፣ አግሮ ኢንዱስትሪውን ከነበረበት ደረጃ አንስተው አሁን ወደሚገኝበትና በርካታ ኢትዮጵያውያን ትሩፋቱን ወደሚያጣጥሙበት ትልቅ ወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪነት እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ ወ/ሮ ሳራ ከዚህም ባሻገር በልዩ ልዩ ተቋማት በቦርድ አባልና አመራር በመኾን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በትጋት የሚወጡ ኢትዮጵያዊት ሲኾኑ፣ ሀገራቸው ሌሎች የደረሱበት ደርሳ ማየትን በእጅጉ ከሚናፍቁ፣ ለዚህም ያለመታከት ከሚለፉ ሀገር ወዳድ ዜጎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ በዛሬው የግዮን ቆይታችንም ከእኚህ ትንታግ ኢትዮጵያዊት ጋር በግልና በሥራ ሕይወታቸው ዙርያ ተከታዩን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ወ/ሮ ሳራ እራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?
ሳራ፡- ሳራ ሐሰን እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ምሥራቅ ሐረርጌ ደደር ከተማ ነው፡፡ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ ኬጂ እና አንደኛ ክፍል ተማርሁ፡፡ ቀጥሎ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከ2ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ቦሌ ጌቱ ኮሜርሻል አካባቢ በሚገኘሁ ‹‹አሳይ›› ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ፡፡ 9ኛ ክፍል የተማርኩት ቦሌ ትምህርት ቤት ቢኾንም፣ 10ኛ ክፍል እንደደረስኩ ግን የማማ ወተት መሥራች በኾነችው እህቴ ወ/ሮ ቡሩካ አማካኝነት ከሀገር ወጣሁ፡፡ ከፍተኛ ትምህርቴንም አሜሪካን ሀገር ከኒውዮርክ ወጣ ብላ በምትገኝ ከተማ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለ3 ዓመታት ተማርኩ፡፡ በመቀጠል ወደ ካናዳ በመሄድ በዲፕሎማ ደረጃ የዲዛይን ትምህርት ተማርኩ፡፡ ከዚህ ትምህርት በኋላም የወርቅና የአልማዝ ጌጣጌጦችን እና መሰል ነገሮችን ዲዛይን ማድረግ ጀመርኩ፡፡ መምህራኖቼ አይሁዶች ስለነበሩ አንድ ዓመት እነሱ ጋር ተምሬ ሌላ አንድ ዓመት ደግሞ በዚሁ በጠቀስኩት የዲዛይን ሥራ ላይ አሳልፌያለሁ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ መደበኛ ትምህርቴ ተመልሼ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ቀጠልሁ፡፡ በዚህ መሃል ወደ ትዳር ዓለም ገባሁ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴንም በፋርማሲ አጠናቀቅኩ፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ የሳይኮሎጂ ትምህርት አጥንቼ ስለነበር ሁለት ዲግሪ ለመያዝ ችያለሁ፡፡ በመቀጠልም እንዲሁ በዲፕሎማ መርሃግብር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ተምሬያለሁ፡፡ ጎን ለጎንም ‹‹ኢሚግራንት ውመን አሶሴሽን›› በሚባል ተቋም በሥነ ልቦና አማካሪነት መሥራት ጀመርኩ፡፡
ግዮን፡ የትዳር አመሠራረት ሂደትዎ እንዴት እንደነበር ቢነግሩን?
ሳራ፡- በወቅቱ ያገባሁት የሀገራችንን ሰው ነው፡፡ አንድ ሴት ልጅ አለን፡፡ አሁን ያቺ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ጨርሳ ሥራ ጀምራለች፡፡ እሷ የ8 ዓመት ልጅ እያለች እዚያው ካናዳ ከትዳር አጋሬ ጋር ተለያየን፡፡ እኔ ወደሀገሬ መመለስ እፈልግ ነበር ፤ እሱ ደግሞ አልፈለገም፡፡ ስለዚህ እሱ በምርጫው እዚያ ሲቀር እኔም በምርጫዬ ልጄን ይዤ መጣሁ፡፡ ልጄም እዚህ በሚገኝ ‹‹አይሲኤስ›› በተባለ የአሜሪካኖች ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተማረች፡፡ በመቀጠል ወደ ካናዳ ሄዳ ሁለት ዲግሪዎችን ሠርታ መጣች፡፡ እኔ ግን ወደዚህ ሀገር ስመለስ በሙያዬ አልቀጠልኩም፡፡
ወደ ሀገሬ የመጣሁት ቤተሰቤ የጀመረው የማማ ወተት ፕሮጀክት ላይ በአጋርነት ለመሳተፍና እሱን ለማሳደግ ነው፡፡ ድርጅቱን ከእህቴ ጋር አጠናክረን ዛሬ ያለበት ደረጃ አድርሰነዋል፡፡ በእርግጥ ድርጅቱን የጀመሩት እሷና ባለቤቷ ናቸው፡፡ ባለቤቷ እንደመጣሁ አካባቢ አረፈ፡፡ እዚህ ከመጣሁ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኾኖኛል፡፡
ግዮን፡- ወደ ድርጅቱ ሲመጡ ደርጅቱ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ሳራ፡- ድርጅቱን አብረን ነው የሠራነው፡፡ ብዙ የተቀየሩ ነገሮች አሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ድርጅቱ በየጊዜው የምርት ዓይነቶቹንና መጠኑን እየጨመረ ሔዷል፡፡ በርካታ የሰው ኃይልም ጨምሯል ፤ አዳዲስ ዲፓርትመንቶችም ተከፍተዋል፡፡ ድሮ ያልነበሩ ምርቶች ተጨምረዋል፡፡ ፓኬጃችን ተቀይሯል፡፡ በርካታ የማዘመን ሥራ ሠርተናል፡፡ ድርጅቱ በሁለት እግሩ ስለቆመ እኔ ደግሞ ወጣ ብዬ ሀገር ለማገልገል እየሠራሁ ነው፡፡ እህቴ ሙሉ ጊዜዋን እዚያው ነው የምትሠራው፡፡
ሀገሬን በጣም እወዳለሁ፡፡ በሀገሬ አልደራደርም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊት ለሀገሬ ማበርከት ያለብኝን ነገር ማድረግ አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁሌ ከመንግሥት ብቻ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ የኾነ አካል መጥቶ ለውጥ እንዲያመጣ መጠበቅም ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው የየራሱን ካበረከተ ለልጆቹ የኾነ ነገር ትቶ ማለፍ ይችላል፡፡ የልጆቻችን ኢትዮጵያን በዚህ መልኩ ነው ሠርተን ማለፍ የምንችለው፡፡ ካለዚያ ግን ስንዴ የዘራ ባቄላ እንደማያጭደው ሁሉ እኛም የኾነ ነገር ሳንሠራ የተሻለ ነገር መጠበቅ አንችልም፡፡ ኢትዮጵያ የአማኞች ሀገር ነች፡፡ እያንዳንዱ የሀገር አገልጋይ ‹‹ነገ በፈጣሪ ፊት እዳኛለሁ›› የሚለውን እምነት ወለድ ሕሊና በልቡ ውስጥ ማኖር ይኖርበታል፡፡ ይኽ ሲኾን ለሀገር የሚሠራው ደስ እያለው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ግዮን፡- ብዙ ጊዜ ስለእህትዎ በየመድረኩ ያነሳሉ፡፡ እንደውም ‹‹እህቴ ሮል ሞዴሌ ነች›› ይላሉና እህትዎን ቢያስተዋውቁን?
ሳራ፡- እህቴ የዛሬው ማንነቴ ምክንያት ናት ፤ ጥንካሬ፣ ታማኝነትና ሀገር መውደድ በርካታ ነገሮችን ከእሷ ተምሬያለሁ፡፡ እህቴ የካሜራም የሚዲያም ሰው አይደለችም፡፡ የሽልማቱ ቀንም ያልተገኘችው ለዚያ ነው፡፡ ሁሌም ሰበታ አግሮን ወክሎ የሚሠሩ ሥራዎች በቃለ ምልልስም ቢኾን እኔው ነኝ ኃላፊነቱን ወስጄ የማደርገው፡፡ እሷ ከልጅነቴ ጀምሮ ያሳደገችኝ እህቴ ብቻ ሳትኾን እናቴም ጭምር ናት፡፡ ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ያሳደገችኝ እሷ ነች፡፡ ጥንካሬዋ ደግሞ ማንነቴን የገነባው ነው፡፡
ግዮን፡- ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ሌላ ትዳር መሥርተው ነበር?
ሳራ፡- ሌላ ትዳር አልመሠረትኩም፡፡ ልጄን የእንጀራ አባት ማሳየት አልፈለግኩም ፤ ነገር ግን በርካታ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ልጆች የአብራኬ ክፋይ ባይኾኑም አሳድጌያለሁ፡፡ አሁን ትልልቅ ኾነው ራሳቸውን ችለዋል፡፡ ፈጣሪ ምናልባትም ለእኔ አንድ ልጅ ብቻ የሰጠኝ ለሌሎቹም ልጆች እናት እንድኾን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጄ አንድ በመኾኗም ተጸጽቼ አላውቅም፡፡ የፈጣሪን ውሳኔ በፀጋ እቀበላለሁ፡፡ ስለዚህ በጣም ደስተኛ ነች፡፡
ግዮን፡- ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ከመቋቋሙ በፊት ሥሙ ማን ነበር? ካፒታሉስ ምን ያህል ነው?
ሳራ፡- ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ሲቋቋም የመጀመሪያ ስሙ ‹‹ሰበታ ፋርም›› የሚባል ነበር፡፡ በወቅቱ ትንሽ ሱፐር ማርኬትና የእንስሳት ማድለቢያ ነበረን፡፡ ከ28 ዓመት በፊት በዚች በትንሽዬ ሱፐር ማርኬት ከማድለቢያ እየወሰድን እንስሳቱን እንሸጥ ነበር፡፡ ከሰበታ ፋርም ወደ ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ የተቀየረው ማሽን ተገዝቶ ወደ ወተት ማቀነባበሪያነት ሲያድግ ነው፡፡ በወቅቱ ሌሎች የወተት ማቀነባበሪያ ተቋማት ቢኖሩም በመኖ የተነሳ ግን፣ የንግድ ፋርሞች ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበሩም፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ዕዳዋን ለማዋቀር ስታደርግ የነበረዉ ድርድር ያለ ስምምነት ተቋረጠ

የኢትዮጵያ መንግሥት በ2024 ዓ.ም. ዋናው ዕዳ የሚከፈልበት የአንድ ቢሊዮን...

የትግራይ ኃይል አባላት ሰልፍ ዛሬም በሌላ አቅጣጫ ቀጥለዋል

በመቐለና ዙሪያዋ የሚገኙ የትግራይ ኃይል አባላይ ትናንት ሰኞ ጥቅምት...

የምርመራ ኬዝ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል

ተማሪ ሊዛ ደሳለ የተባለች ወጣት ሰሞኑን በደሴ ከተማ “...

ስቲሊ አር.ኤም.አይ ላለፉት አራት ዓመታት የፕላቲኒየም ሸልማት ተሸላሚው

የ2017 በጀት ዓመት 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና...