የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ አንጋፋው ፖለቲከኛ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው፡፡ አቶ የሺዋስ ከሰማያዊ ፓርቲ ምሥረታ እና የፖለቲካ ትግል በኋላ ሥማቸው እየገነነ የመጣ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመንም ለዓመታት በሰላማዊ የፖለቲካ ታጋይነታቸው ለዓመታት በእሥር ያሳለፉ ሰው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የመጋቢት 2010ሩ ለውጥ ከመጣ በኋላ ሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ከነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመኾን ኢዜማ እንዲመሠረት ጉልህ ሚና ከተጫወቱ ግለሰቦች አንዱም ናቸው፡፡ ከኢዜማ ምሥረታም በኋላ የፓርቲው ሊቀመንበር በመኾን አገልግለዋል፡፡ በቅርቡ እርሳቸው እና ሌሎች ጓዶቻቸው ፓርቲያቸው የነበረው ኢዜማ የትግል መሥመሩን ስቷል በማለት በውስጠ ፓርቲ ሲያደርጉት የነበረው ትግል ፍሬ ማፍራት አለመቻሉን ገልጸው በይፋ ድርጅቱን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ የፖለቲካ ኃይል አዋልዶ ለመታገል በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ ክሽፈት፣ በአሁናዊ የኢትዮጵያ እውነታ እና ‹‹አሉ›› በሚሏቸው ተስፋዎች ዙርያ የሚከተለውን ቆይታ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የመጀመሪያ ጥያቄያችን የሚኾነው በመሰባሰብ፣ በመበተን አንዳንዴ ደግሞ በመቀናጀት፣ ብዙም ሳይቆይ ደግሞ በመፍረስ አልያም አንጃ በመፍጠር ዛሬ የደረሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች እውነታ ሲያስቡ ምን ይሰማዎታል?
የሺዋስ፡- በእኔ እምነት የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ትግል ካለፈው የቀጠለ ነው፡፡ ውጤት ሳያገኝ አይቆምም ብዬም አምናለሁ፡፡ መፍረስ መነሳት እንኳን የፖለቲካ ስብራት ባለበት ሀገር አይደለም በማንኛውም ቢዝነስ ላይ የሚጋጥም ነው፡፡ እኛ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ‹‹መሬት ለአራሹ፣ የብሔረሰቦች እኩልነት፣ የዜጎች ነፃነት፣ ሕዝባዊ መንግሥት፣…›› የሚሉ ጥያቄዎች ያነሱ እህት ወንድሞቻችን ጥያቄን ነው እያስቀጠልን ያለነው፡፡ የዛ ትግል ውጤት ገና አልተመለሠም ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የጠቀስከው ችገር የሚያጋጥምበት ምክንያት አለ ማለት ነው፡፡ ትግሉም፣ ሕዝቡና ሀገሩም ባለበት እንዳለ ነው፡፡ በመኾኑም ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ድርጅት አልያም ስብስብ ማለት ቢሮና ማኅተም ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ትግል ነው ብለን እናምናለን፡፡ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በአጠቃላይ ዜጎቻችን ለአገዛዝ የማይመቹ፣ አምባገነን አገዛዝ ትከሻቸው ላይ ተጭኖ እንዲኖር የማይቀበሉ ኾነዋል፡፡ ይህ የኾነው በእኛ ብቻ ሳይኾን ከእኛ በፊት በነበሩ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በነበረው የትግል ውጤት ነው፡፡ እናም የትግል ምክንያቱ እስካለ ድረስ ትግሉ አሁንም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እረፍት እስከሚያገኝ ድረስም ይቀጥላል፡፡ በእኔ እምነት እኔ የዚህ የቀጠለው ትግል አካል ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡
ግዮን፡- እዚህ ጋር ታዲያ ተመሳሳይ ጥያቄና አጀንዳን ይዘው ሲታገሉ የነበሩ ሰዎች አብረው መታገል አቅቷቸው በተለያየ መንገድ የሚበታተኑት ለምንድነው ማለት ይቻላል?
የሺዋስ፡- አዎ፣ እዚህ መመለስ የሚገባን ጥያቄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት የሚጨናገፈው በማን ነው? የሚለው ነው፡፡ በሕዝብ ነው? በገዢው ፓርቲ ነው? በራሳቸው በፖለቲካ ድርጅቶች አማካኝነት ነው? በእኔ ዕምነት በማሕበረሰቡ የዕምነትና የባሕል ተቋማት ችግር ነው፡፡ በተጨማሪም ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በመሰል ሕጋዊ ተቋማት ጭምር ነው፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን እስካሁን ሲደረግ የነበረው ትግል ውጤት አላመጣም፡፡ ቢያንስ ለነፃነታቸው ያገዝናቸው የኬኒያ፣ የጋና፣ የናይጄሪያ እና የደቡብ አፍሪካን ያህል እንኳ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አልዘረጋንም፡፡ አንድም አስተዳደር በሕዝብ ማምጣት አልቻልንም፡፡ በንጉሡም፣ በደርግም፣ በኢሕአዴግም፣ አሁንም ባለው መንግሥትም በምርጫ ውጤት አላመጣንም፡፡ የኾነውም በአንድ እጅ ጠመንጃ በሌላው ምርጫ በማድረግ ሥልጣንን ማስቀጠል ነው፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ግን አሁን የሚደረገው ትግል እንደቀደሙት ዐይነት ትግል አይደለም ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንድ ደረጃ ከፍ ያለ በምንም ተዓምር አገዛዞች ተረጋግተው የማይቀመጡበት፣ የሕዝብን ፖለቲካዊ ጥያቄ ‹‹የልማት›› ጥያቄ አድርገው የማያልፉበት ሁኔታ እንዲያደርጉት የሚያስችል ትግል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከንጉሡ መውደቅ በኋላ ያሉ ጥያቄዎች አልተፈቱም፡፡ የእኛም ዓላማ እዚህ ላይ የሚደረገው ትግል እንዲቀጥል ነው፡፡ ይሄ ትግል በሰርተፍኬት፣ በጽሕፈት ቤት እና መሠል አካሄዶች የሚመለስ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ አገዛዝን ‹‹አሜን›› ብሎ ተቀብሎ የሚኖር አይኖርም፡፡ ለውጥን ግድ የሚል ትውልድ ነው አሁን ያለው፡፡ ይኼን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ በቀጣይ የምትጀምሩትን ፖለቲካዊ ትግል አስመልክቶ ሲናገሩ ‹‹አዲስ የፖለቲካ ባሕል ግንባታ›› የሚል ኃይለቃል ተጠቅመዋል፡፡ እስከዛሬ ድረስ የመጣንበትን ፖለቲካዊ ባሕል አስመልክቶ የወሰዳችሁት ምን ትምህርት ቢኖር ነው?
የሺዋስ፡- አዲስ የፖለቲካ አተያይ ብለን ጀምናል ፤ እውነት ነው፡፡ ጉዳዩንም የጀመርነው ከውይይት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጥቂቶች ተሰብስበው በመፈራረም አንድ ነገር መሥርተው ሌሎች እንዲገቡ መሳብ ነበር የነበረው ልማድ፡፡ አሁን ግን ቢያንስ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ተነጋግረን የሃሳብ አንድነት መፈጠር አለበት፡፡ ለምሳሌ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በሂደቱ የነበሩ ስሕተቶችና ደካማ ጎኖች ምን ነበሩ? የሚለው ላይ በመስማማት መጀመር ይገባናል፡፡ በአሕአፓም፣ በመኢሶንም፣ በኢሰፓም፣ በሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የነበሩና ልምድ ያላቸው ሰዎች አብረውን አሉ፡፡ የወቅቱን ድክመትና ጥንካሬ የሚያሳዩ መጻሕፍትም አሉ፡፡ ከእነዚህ አካላት መማር የውይይቱ አንዱ ነጥብ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዋነኞቹ ተቃርኖዎች የሚባሉት የብሔር ፖለቲካና የአንድነት ፖለቲካ ምንድናቸው? በምን ይፈቱ? የማይታረቁስ ናቸው ወይ? የሚለውን ተነጋግሮ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው እስካሁን በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በኮታ ልዩነቶች የሚደረግ የፖለቲካ ትግል የትም አላደረሰንም፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎችችን ምንድናቸው የሚለውን በቅጡ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ለምሣሌ ሕገ መንግሥት ይባላል፤ ሕዝባዊ መንግሥት ይባላል፤ የተቋም ግንባታ ይባላል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመሬት ሥሪት፣ የፌደራል አወቃቀር፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ የመሳሰሉት ላይ ግልፅ ያለ አቋም ይዞ መነሳት ያስፈልጋል በሚል በጋራ እየተወያየን ነው፡፡፡
ለምሳሌ ኢትዮጵያ የጠንካራ ግለሰቦች ሀገር ናት ቢባል በአመራር ደረጃ ስሕተት ላይኾን ይችላል፡፡ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ አሁን እስካሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድረስ ሰዎችን መቅጣት ይችላሉ እንጂ እነርሱን መቅጣትና መግራት የሚችል ተቋም የለንም፡፡ ስለዚህ በተቋም ግንባታ ደረጃ የለንበትም ማለት ነው፡፡ በእኛ እምነት ይህን መሥራት የሚያስፈለገው አሁን ስለኾነ በውይይት ላይ ያለንበትን ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ እዚህ ሀገር መንግሥት አለው ወይ? መንግሥትስ ምን ማለት ነው? የመንግሥት አካላትስ ምንድ ናቸው? የሚለው ነው፡፡ በእኛ እምነት የመንግሥት አካል የሚባሉት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ፣ ሕግ ተርጓሚ እንዲሁም ሚዲያና ተቃዋሚ ኃይሎች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መኖር አለባቸው፡፡ ስለዚህ በእኛ አስተሳሰብ ተቃዋሚ ኃይል ስለሌለ ነው ሚዲያው በትክክል የማይሰራው፡፡ ሕግ አውጪውም፣ አስፈፃሚውም፣ ተርጓሚውም ሥራውን በትክክል የማይሠራው ለዚህ ነው ባይ ነን፡፡ ስለዚህ ይህን ክፍተት መሙላት በሚችል ደረጃ ለመደራጀት ነው እየተነጋገርን ያለው፡፡ አዲስ የኾነው የፖለቲካ አተያይ ከፍ ሲል የተነሱት ነጥቦች ላይ የነጠረ እውቀት ኖሮት እና ተረድቶ ወደ ፊት መሄድ ያስችላል ብለን እናምናለን፡፡ በነገራችን ላይ በአዲሱ ፓርቲ ውስጥ የምንኖረው ከኢዜማ የወጣን ሰዎች ብቻ አይደለንም፡፡ ከሌሎችም ፓርቲዎች የወጡ፣ ምንም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ያልነበሩ፣ አዲስ ፓርቲ ለመመሥረት የተሰበሰቡና እኛን አይተው ያዘገዩ እና መሠል አካላት ያሉበት ትልቅ ስብስብ ነው፡፡
ግዮን፡- ብዙ ጊዜ በአንድነት ፖለቲካው ጎራ የተሰለፈው የፖለቲካ ኃይል መሬት ላይ ካለው እውነታ ይልቅ ምኞቱን ማመን ይፈልጋል የሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡ እናንተ ዛሬ ላይ የሃይማኖት ተቋትን እስከማመስ የደረሰውን ሥር የሰደደ የዘውግ ብሔርተኝነት ጉዳይ ገምግማችሁታል ማለት ይቻላል?
የሺዋስ፡- ባለፈው የፖለቲካ ሥርዓት ከዘውግ ፖለቲካና ከአንድነት ፖለቲከ የትኛው በትክልል ሥር የሰደደ ነው የሚለው በትክክል የሚታቅ ነገር የለም፡፡ እኛ ግን ማሳያዎች አሉን፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን ወረራ ወይም ወረርሽኝ ሲገጥመን፣ ጦርነት ሲገጥመን፣ በሩጫ ወይም በኳስ ስናሸንፍ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዴት ቅርብ እንደኾነ እንድናይ ያስችለናል፡፡ አሁን የመጡትን ዶ/ር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ማናቸውም ‹‹ኢትዮጵያ›› ስላሉ ነው ማዕከላዊ ሥልጣኑን መቆጣጠር የቻሉት፡፡ በእኛ እምነት አንዳንዶች እንደሚሉት ኢትዮጵያዊነት የተዳፈነ ሳይኾነ የተገለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገለጠ እውነት ነው፡፡ ይህን አቋም ይዘን ነው የምንታገለው፡፡ ሕዝብ ብሔርተኝነቱን አይቶ አይቶ ተፀይፎታል፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ ኢትዮጵያን ‹‹የብሔረሰብ እስር ቤት›› ነበር የሚላት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በትክክልም ይህ እውነታ ተረጋግጧል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ያለ ተቋም እየታገልን ኢትዮጵያን ማስቀጠል የቻልነው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለምሳሌ በ1997 ሚያዚያ 30 ይመስለኛል የቅንጅት ሰልፍ ጊዜ አቶ መለስ ነፍሳቸውን ይማርና በጣም ደንግጠው ‹‹የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጠፍቷል ብለን አስበን ነበር ፤ አከርካሪውን ሰብረነዋል ብለን ነበር፤ ለካ አለ›› ብለው ነበር፡፡ ይህን ሁሉም ብሔርተኛ ኃይሎች ደግመውታል፡፡ አሁንም የኦሮሞ ብሔርተኛ ነን የሚሉ ኃይሎችም፣ የትኛውም ብሔርተኛ ይህን የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ እምነት ኢትዮጵያን የሚያድነው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተሞላው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን ለማጥፋትና ለመገንጠል ከሚሄዱት የብሔር አስተሳሰቦች በስተቀር ከ60ዎቹ ጀምሮ የቆየው የብሔረሰብ እኩልነት ጥያቄ የሚካድ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ከተለያየ የብሔር ፖለቲካ ትግል የመጡ ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ በትክክል የወጡበት ማኅበረሰብ የልማት፣ የባሕልና የፖለቲካ እኩልነት አላገኘም ብለው የሚያምኑ ናቸው እነዚህ ግለሰቦች፡፡ በመኾኑም እንዲህ ዐይነት ለልማት ተደራሽነታቸው አብረን በመሥራት በኢትዮጵያ አንድነት የሚምኑትን ኃይሎች እናቅፋለን፡፡ ‹‹ተገፍተናል›› ብለው የሚስቡትን አካላት ጨምረን አካታች የኾነ ትግል እናደርጋለን፡፡ ያ ካልኾነም መፍትሔ ማምጣት አይቻልም፡፡ ለሁሉም የኢትዮጵያዊነት ሐሳብና መንፈስ መዳኛ ነው ብለን ስለምናምን በትኩረት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
ግዮን፡- የዘውግ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ የጋረጠውን አደጋ በዚህ መጠን ብቻ ነው የምትገመግሙት?
የሺዋስ፡- እኛ የሁሉ ነገር ስብራት መነሻ የፖለቲካው ስብራት ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ትግል ማለት ደግሞ የሌለ ነገርን ወደ ነባራዊ እውነት ማምጣት ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ብርሃን ማሳየት መቻል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ብሔርተኝነት ያልነበረን አስተሳሰብ አምጥቶ ነው ለዚህ ያበቃው፡፡ በ1960ዎቹ አሜሪካ እና አውሮፓ ሄደው የሚማሩት ተማሪዎች ብሔረሰባቸውን የሚጠሩት ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ብለው ነበር፡፡ አሁን ግን ተገልብጦ ሌሎች የተውትን ብሔርተኝነት እኛ ይዘነዋል፡፡ ግን ደግሞ ኢትጵያዊነት የለም አልቆልናል በሚል አይደለም ማኅበረሰብን ወደ ትንሣኤው መውሰድ የሚቻለው፡፡ ችግሩ አለ፡፡ ስላልተስተካለም ኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ ሁሉም ነገራችን እንቅፋት ገጥሞታል፡፡ ማኅበራዊ ሕይወታችን ምስቅልቅሉ ወጥቷል፡፡ ይሄ የፖለቲካ ስብራት ውጤት ነው ብለን እናስባለን፡፡ አሁን ላይ መጥቶ ሃይማኖታችን ውስጥ ሳይቀር ገብቷል፡፡ ይሄ መፈታት የሚችለው ፖለቲካው ሲታከም ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ተስፋ የላትም አክትሞላታል ማለት አደለም፡፡ አገዛዙ ስለሚፈራው ነው እንጂ ይሄ አስተሳሰብ ቢመጣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አስተሳስሮ የሃይማኖቱም፣ የፖለቲካውም፣ የኢኮኖሚውም ስብራት ፈውስ ይኾናል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ፡፡
ግዮን፡- አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ በዜግነትና በዘውግ ፖለቲካ መካከል አማካኝ መንገድ አለ ብለው ያምናሉ?
የሺዋስ፡- አዎ አማካኝ መንገድ አለ፡፡ በርግጥ ዳር የወጣና ሀገር ለማፍረስ የሚታገል የዘውግ ፖለቲካ አራማጅ ኃይል አለ፡፡ እነርሱን እንታገላቸዋለን፡፡ የክልል ወይም የክፍለ ሀገር ሥልጣን ግን የማዕከላዊ መንግሥቱን እንዲነቀንቀው አንፈልግም፡፡ የትኛውም የፌደራል አወቃቀርን የሚከተል ሀገርም ይህን አይፈቅድም፡፡ በፌደራል ሥርዓት የተዋቀረ ሀገር ወደ ሕዝቡ ለመቅረብና አስተዳደሩን ለማሳለጥ እንጂ ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመናድ አይሰራም፡፡ እኛም አንቀበልም፡፡ የፌደራል አወቃቀር ዘጠኝ ወይም ዐሥራ ዘጠኝ ክልል ማድረግ ብቻ ሳይኾን በየክልሉ የሚገኙ ወረዳና ቀበሌዎች ሁሉም ተቋማት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ እኛም ይሄ አንዱ የምንታገልለት ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው በተለያየ መልኩ እንደተማርኩት ከ60ዎቹ ጀምሮ ‹‹የብሔረሰቦች እኩልነት›› የሚባል ጥያቄ አለ፡፡ ይህን ጥያቄ ሕዝብን ተጠግቶና አማክሮ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እኔ በገባኝ ልክ በዚህ ዙሪያ ሊፈቱ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ የባሕል፣ የቋንቋ፣ የእምነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ እነዚህን ለመመለስ ኢትዮጵያ የምትበቃ ሀገር ነች፡፡ አማካኝ መንገድ የሚኾነውም ይሄ ነው፡፡ በትክክል የፌደራል አወቃቀር እንዲሠራበት ለማድረግ መጣር ያሻል፡፡ ይሄ ከኢትዮጵያውያን አቅም በላይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቅድሚያ የፖለቲካ ስብራቱን መጠገን ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- የሚጠቅሷቸውን አንዳንድ ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥብራቶች ለመጠገን ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚኖረው ሚና በእርሶ እንዴት ይገለጻል?
የሺዋስ፡- እኔ በሀገሬ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በሀገሬ ተቋማት ላይ ግን ያን ያሕል ተስፋ የለኝም፡፡ ተስፋ ማድረግ በጣም ይከብዳል፡፡ አሁን የተጣሉ የፖለቲካ ኃይሎች ‹‹ታረቅን›› ብለው ያልተጣላው የኢኮኖሚው፣ የባሕሉ፣ የኃይማኖቱ ባለቤት የኾነው ሕዝብ ግን ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ወደ ሁለት ዓመት ኾኖታል፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ በዚህ ችግር ውስጥ ኾና መዘግየት አልነበረበትም፡፡ እንኳን ሁለት ዓመት ሁለት ቀን መዘግየት አይቻልም ፤ የኢትዮጵያን ችግር ለተረዳ፡፡ ደፈር ያሉ እምጃዎች መውሰድ ነበረባቸው፡፡ አሁንም ግን በሀገሬ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ለሀገሬ መድህን እስከሆነ ድረስ ይኼን ድርጅት በምችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ ድርጅቱ ሥራውን ለመሥራት ያለው መንግድ ግን በጣም ቀጭን ነው፡፡ ለምሳሌ ሀገሪቱ የተለያየ አዘቅት ውስጥ ስትገባ በሃይማኖት፣ በብሔር እንዲሁም ክልሎች ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲፈፅሙ ለመንግሥት ችግሩ ኢትዮጵያ ሳይኾን ኬኒያ ወይም ታንዛኒያ የተፈጠረ እስኪመስል ነው ጆሮውን የሚደፍነው፡፡
ግዮን፡- የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ በመንግሥት እና በህወሓት መካከል እርቅ መውረዱ ይታወቃል፡፡ ኾኖም ግን በትግራይ እየኾነ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ የተፈታ ሳይኾን የተዳፈነ ረመጥ ነው ብለው የሚገልጹት ወገኖች አሉ፡፡ ምን አስተያየት አለዎት?
የሺዋስ፡- እኔ ባደኩበት አካባቢ አንድ በአባባል አለ፡፡ ‹‹እንኳን እናቴ ሞታ እንዲሁም አልቅስ አልቅስ ብሎኛል›› ይላሉ፡፡ እንኳን የህወሓትን፣ የብልፅግናም ጉዳይ ግልፅ አይደለም፡፡ ምን ላይ ስምምነት እንዳደረጉ አይነግሩንም፡፡ የፀቡ ጊዜ ደግሞ ‹‹ኑ እንሂድ›› ይላሉ፡፡ እኔ አንድ ስብሰባ ላይ ከባለሥልጣናቱ ጋር ተጋጭቼ ነበር፡፡ ምንድነው የሚያስጨንቅህ ሲሉኝ ‹‹እኔን የሚስጨንቀኝ ነገር እናተን አለማስጨነቁ ነው›› አልኳቸው፡፡ ሀገራችን ላይ እንዲህ ዐይነት ነገር ሲደረግ እንዴት እኔ አላውቅም እንደ ዜጋ? እሺ እንደ ዜጋ ማወቄ ይቅር፡፡ በሀገሪቱ የማኅበረሠብ አንቂዎች የኃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዴት ስለሀገራቸው አያውቁም? ትግራ ላይ ስለሚካሔደው፣ ስለሚወሰነው ነገር እንደ ዜጋ እኮ የማወቅ መብት አለኝ፡፡ ምንድነው የሚበሉት? ምንድነው የሚጠጡት? የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ወይ? አላውቅም፡፡ ይህን ሁሉ የማላውቀው የሀገሬ እንድ አካል ኾና ነው፡፡ ስለዚህ እንኳን እዚያ ያሉት ይቅርና እዚህ ያለነውም ራሱ በፍጹም ማወቅ አልቻልንም፡፡ ስለዚህ በቅንነትና በሥርዓት የሐሳብ አንድነት ይዞ መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ እኛም ሀገር እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ኾና ነገሮችን አመዛዝነን ለመሄድ እየጣርን ነው፡፡ በአንድ በኩል ሀገር ላይ አደጋ ሊያመጣ የሚችል የሚያስጨንቅ ነገር አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ የፖለቲካ ስብራት እንዳያጋጥም ጥንቃቄ የምናደርግበት ነገር አለ፡፡ ምን እየኾነ እንዳለ ግልፅ አይደለም፡፡ እኛ ባለን አቋም ትክክል አይደለም በምንለው አቋም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመን ለመታገል እየጣርን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በትግራይም ምን እየኾነ የሚለውን በማየት ለትግራይ ሕዝብም ለመጮህ ነው ሐሳባችን፡፡
ግዮን፡- አማራጭ የፖለቲካ ኃይል ኾናችሁ ለመውጣት እየተዘጋጃችሁ ያላችሁት ሰዎች፣ ስብስባቹ ምን እንደሚመስል ቢነግሩን?
የሺዋስ፡- አሁን ሀገራችን ላለችበት ሁኔታ፣ ተቃርኖዎችና ከታሪክ ከመጡ ተቃውሞዎች ተነስተን ምንድነው ማድረግ ያለብን? ያሉት ላይ ነው መግባት ያለብን? ንቅናቄ ነው መፍጠር ያለብን? የሚለውን በጋራ እንወስን የሚለው ላይ እየተወያየን ነው፡፡ ነገር ግን ትግሉ ላይ አለንበት፡፡ አካሄዱ እንዴት መኾን እንዳለበት ግን አብረን እንወስን የሚል ላይ ነው ያለነው፡፡ በአጭር ጊዜም ይህን ውይይት ቋጭተን ስብስቡ በአንድ መልክ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ግዮን፡- በስብስቡ ውስጥ ምን ዐይነት ሰዎች አሉበት?
የሺዋስ፡- የቀድሞ ጓዶቻችን ወደ መንግሥት ሲገቡ ቀሪዎቻችን በሙሉ በትግሉ ውስጥ ነን፡፡ እኛ አሁንም መስመር ላይ ነን፡፡ በነገራችን ላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ እያደረግን ነው፡፡ የኢትጵያ ሕዝብ በአንድ ላይ በተለይ በዜግነት ጉዳይ ለሚያምነው ክፍል ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በየቦታው ከመቀመጥ አንድ ትልቅ ሀገራዊ ፓርቲ ማቆም ትግሉን ወደፊት ይገፋዋል፡፡ ለምሣሌ ኢሕአፓ፣ መኢአድ እና እናት ፓርቲ የፈጠሩት ስብስብ አለ፡፡ ጥሩ ጅምር ቢኾንም በቂ አይደለም፡፡ ሌሎችም መሰብሰብ አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡ ፈጽሞ የማናመቻምቻቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም የዜጎች እኩልነት ጉዳይ ናቸው፡፡ በእነኚህ ነጥቦች ዙሪያ አብረውን የተሰለፉ በርካታ ኃይሎች አሉ፡፡ እኔ ከምገልጻቸው ራሳቸው ወጥተው ቢናገሩ ይሻላል፡፡
ግዮን፡- ኢዜማ በነበራችሁ ሰዓት አንድ አዲስ ያላችሁት አደረጃጀት ፈጥራችሁ ነበር፡፡ ይኸውም ማንኛውም አባል ከወረዳ ሳይመረጥ የፓርቲው ጠቅላይ ምክር ቤት አባል የማይኾንበት አሠራር ነበር፡፡ በቀጣይ የትግል መሥመራችሁ ፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት ከኾነ ይኽንን ልምድ ይዛችሁ ትቀጥላላችሁ ወይስ ወደ ቀድሞ አሰራር ትመለሳላችሁ?
የሺዋስ፡- ይሄ ሐሳብ አሁንም አልቀረም፡፡ በመሠረቱ ታግሎ ለውጥ የሚያመጣው ሕዝብ ነው፡፡ ልማትም የሚያመጣው ሕዝብ ነው፡፡ አመራር ያስተባብራል መሠረት ያስይዛል እንጂ አንድ አንድ አመራር ሁለት እጅ እና እግር የለውም፡፡ በመኾኑም ማኅበረሠቡን ያሳተፈ ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ በመኾኾ ይኼ ጉዳይ አንዱ የምንወያይበት ሁኔታ ይኾናል፡፡ እንደሚታወቀው ለውጥ ሲመጣ ተስፋ ያለው መስሎን በጣም የሠለጠነ፣ በአውሮፓና አሜሪካ ብሎም በእስራኤል የፖለቲካ ኃይሎች የሚጠቀሙበትን አሠራር ነበር ኢዜማን ስንመሠርት ለመዘርጋት የሞከርነው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አልፎ ገዚውም ፓርቲ ይማርበታል የሚል ዕምነት ነበረን፡፡ በእኔ አስተያየት የፖለቲካ እድገት ወደ ላይ ስለኾነ አሁንም አሻሽለን የምንቀጥለው ይመስለኛል፡፡ ኾኖም ይኽን የሚወስነው ስብስቡ ተወያይቶ ስለኾነ የእኔ ምልከታ መኾኑ ይያዝልኝ፡፡
ግዮን፡- በዚህ ዘመን ሥርዓት ያለው የፓርቲ ፖለቲካ ለማካሔድ በብዙ መንገድ ‹‹አክቲቪዝም›› እንቅፋት ሲኾን ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ማኅበራዊ ሚዲያውን የሚመራ ፖለቲካ ለመፍጠር እና የአክቲቪዝሙንም ተጽዕኖ በምን መንገድ ለመቋቋም አስባችኋል?
የሺዋስ፡- ፓርቲዎች በትክክል መሥራት ካልቻሉ ፖለቲካው ከእነርሱ ይወጣል፡፡ ለዚህ ገዢው ፓርቲ በሁለት መንገድ ተጠያቂ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን የምናካሒድ ፓርቲዎች አጠገቡ እያለን እርሱ ለድርድር የሄደው ፕሪቶሪያ እና ታንዛኒያ ነው፡፡ ይሄ የተደራጀና ሃሳብ ያለው ፖለቲከኛ እንደኮሰምን ያደርገዋል፡፡ በሚዲያውም በኩል በግብር የሚተዳደሩ ትልቅ በጀት ያላቸው ሚዲያዎች የግለሰብ ፊስቡክ ገፅ ሼር የሚያደርጉ ከኾነ ሚዲያው ወደ አንድ ሞባይልና ወደ አንድ ካሜራ ይሄዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከእነርሱ የተሻለ ማኅበራዊ አንቂ ብዙ ተከታይ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ የመደበኛ ሚዲያው በትክክል የሕዝቡን ጉዳይ ያለመያዝ፤ ለምሳሌ የእስልምና፣ የክርስትና፣ አልያም ብሔረሰባዊ ችግሮች በሚኖሩበት ወቅት ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ጋራ እና ሸንተረር የሚያሳዩ ከኾነ፣ በተቃራኒው በዚያ ወቅት የግለሰብ ገፆች የሕብረተሰቡን ችግር የሚያሰተላልፉ ከኾነ ዋናዎቹ ሚዲያዎች ተቀባይነት ያጣሉ፡፡ እርግጥ ነው ማኅበራዊ ሚዲያው ወደ ሥርዓት መምጣት አለበት፡፡ ጋሽ መስፍን ወ/ማርያም (ፕ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ መንቀል ነው እንጂ መትከል አይችልም›› ይሉታል፡፡ ሥርዓት ለመትከል መደበኛው ሚዲያ ማደግና በትክክል መሥራት አለበት፡፡ አለበለዚያ ግለሰቦች እስከተከፈላቸው ድረስ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ መሪ ይኾናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኮ አንዳንዴ ለፌስቡክ ነው መልስ የሚሠጡት፡፡ አጠገባቸው ኾኖ ለጠየቀው ሳይኾን እዚያ ለተነበበው ነው መልስ የሚሰጡት፡፡ ሌሎችም የመንግሥት አካላት እንደ እሳቸው ነው የሚያደርጉት፡፡ ስለዚህ ይሄ እንዳይኾን ፖለቲካን የሙሉ ጊዜ ሥራው አድርጎ የሚሠራ ሰው ለንግግር፣ ለውይይት እና የፖለቲካ ስብራትን ለመጠገን ጊዜ ሊሠጠው ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ ያለዎትን ተስፋ በመንገር ብናጠቃልል?
የሺዋስ፡- ሁለት ተስፋ የማይቆረጥባቸው ነገሮች ሀገርና ፈጣሪ ናቸው፡፡ ምን ጊዜም፣ ምንም ዓይነት ምስቅልቅል ምንም ዓይነት ችግር ቢፈጠርብን በፈጣሪ ተስፋ አንቆርጥም፡፡ አንድ ቀን ይጎበኘናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በሀገራችንና በሕዝባችንም እንዲሁ ፈታኝ ሁኔታ ቢኖርም ተስፋ አንቆርጥም፡፡ ማሳሰብ ያለብን ኢትዮጵያ በብዙ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፈች ሁሉ ይህንንም እንደምታልፈው ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ማኅበረሰቡ ‹‹የእኔ ነፃነት በጎረቤቴ፣ አብሮኝ ባለሰው ላይ የተመሠረተ ነው›› የሚል አስተሳሰብ እንዲይዝ እንፈልጋለን፡፡ እንደዚያ ሲኾን ትልቁ እርምጃ ተጀመረ ማለት እንችላለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ተቋማት እንዲፈጠሩ በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠነክሩ እውነተኛ የኾኑትም ወደፊት እንዲመጡ ሁሉም መጣር አለበት፡፡ ዲሞክራሲ አቋራጭ መንገድ የለውም፡፡ ያለው የሚያለፋና በውጣ ውረድ የታጠረ መንገድ ነው፡፡ መተባበርን መተሳሰርን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ መገኘታችንን አውቀን እንተባበር ፤ እንሰባሰብ፡፡ ሚዲያዎችን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አስተባብረን ኢትዮጵያውያን አሁን ካለንበት ችግር በጋራ እንውጣ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡