የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ማሊን ለመጎብኘት ወይም ለሥራ የሚመጡ የአሜሪካ ዜጎች ቪዛ ለማግኘት 10 ሺህ ዶላር እንዲያሲዙ የአገሪቱ መንግሥት ወስኗል።
ይህ የአገሪቱ ውሳኔ የመጣው የአሜሪካ መንግሥት በዜጎቿ ላይ ተመሳሳይ የሆነ እርምጃ ካስቀመጠ በኋላ ነው።
በማሊ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ክፍያው የተወሰነው “የአሜሪካን ድንበሮች እና የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለመከላከል” እንደሆነ አርብ ዕለት ገልጾ ነበር።
የማሊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እሁድ ዕለት የማስያዣ ገንዘቡ የተወሰነው በተናጠል መሆኑን አስታውቆ፤ለአሜሪካውያን ዜጎች “ተመሳሳይ የሆነ የቪዛ ፕሮግራም” እንዲኖር ያደርጋል ብሏል።
የቪዛ ፖሊሲ ለውጥ የመጣው ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እየጣሩ ባለበት ወቅት ነው።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ማሊን የጎበኙ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በፀረ ሽብር ትብብር፣ በኢኮኖሚ አጋርነት፣ እንዲሁም የማሊን የወርቅ እና የሊቲየም ማዕድናት ክምችትን መጠቀምን በተመለከተ ተወያይተው ነበር።
እ.አ.አ በ2021 በማሊ በጄነራል አሲሚ ጎይታ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተቀዛቀዘ መጥቷል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ማሊ በጂሃዲስቶች የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት ለመመከት ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጥብቃለች።
የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገራቸው ያባረሩት ጄነራሉ፤ በሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ስር የሚንቀሳቀሱትን የዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮች ወደ አገራቸው ጋብዘዋል።
ባለፈው ሳምንት የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መንግሥት አሜሪካ ለዜጎቹ ቪዛ መስጠት በማቆሟ የተነሳ ወደ አገሪቱ የሚላኩ ስደተኞችን እንደማይቀበል አስታውቆ ነበር።