በተመስገን ኡካሬ (የሐጌ ልጅ)
በማስተዋል የሚደመጥ አልበም! በየዘመኑ እንዲህ ዐይነት ክስተት ዘፋኞች ብቅ ይላሉ፣ በሙዚቃ መንገድ ታሽቶ የመጣ እንዲህ ያለ የሚስብ አቅም ያደርሰናል፡፡ ማስተዋል እያዩ ያለበት ደረጃ ሌላ የሱ ሙዚቃ ዓለም አለው፡፡ በትዝታ፣ በሀሳብ ላቅ ያለ የማስተዋል የድምፅ እርከን ስፋት፣ ቀለም፣ ሬንጅ፣ የቅኝት ባለቤት ጉሮሮው እንደ ፈለገ የሚተታጠፍ የመሳሰሉት ያየንበት ነው፡፡
አንድ ወዳጄ የፋና ላምሮት ፈርጥ ድምፃዊ ናሆም ነጋሽ ስለዚህ አልበም ስናወራ እንዲህ አለኝ ‹‹ወይን እያደር አይደል የሚጣፍጠው? ይህ አልበም እንዲያ ነው፡፡ ደሞ ከጣፈጠ በኋላ ደረጃውም ቦታውም ይልቃል›› አለኝ፡፡ ልክ ነው ከልብ ማድመጥ ጆሮ የሚሻ ሙዚቃ እና በአዕምሮዬ ሲዘዋወር የነበረውን ሐሳብ በሙሉ ቋንቋ ገልፆልኛል፡፡
ጠቅላላ ሙዚቃዎች ሲሰሩ በስሜታቸው እና በሥልተ ምቱ በአግባቡ መግለፅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የሙዚቃ ነፍሱ እሱ ስለ ሆነ፡፡ በነጠላ ሙዚቃዎቹ እና Ep ሙዚቃዎቹ አቅም እና ችሎታውን በሚገባ አሳይቶን ወደ አልበሙ ተከስቶ ተዓምራዊ አልበም ሰጥቶናል፡፡
‹‹እንዚራ›› አልበም
እንዚራ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙዚቃ መሳርያ ነው፡፡ በዚህ ስያሜ መምጣቱ አልበሙን በብዙ መንገድ እንዳስበው አድርጎኛል፡፡ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ተወዳጁን ማዲንጎ አፈወርቅን እንድናስታውስ የሚደርገን ብሎም አብዛኛው በዜማ የሰራው እራሱ ማስተዋል ሲሆን፣ ይህ ሌላኛው የማዳመጥ ክህሎት የመጣበት የሙዚቃ ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ ይነገርናል፡፡ የሙዚቃ ቫራይቲ (የተለያየ ዐይነት ሥልት እና ሐሳብ) ሬጌ፣ ሱዳኒክ፣ ትዝታ፣ ፎክ (ባህላዊ የሙዚቃ አዛዝያም)፣ የቅኝት ሙዚቃዎች ተሰርተዋል፡፡ 14 የሙዚቃ ክሮች ሲኖሩት ደጉ ትዝታ፣ መጥቼ ነበር፣ በምን ቃል፣ ደግሰን፣ ከፋኝ፣ እንዚራ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ከአልበሙ የገረመኝ እና የወደድኳቸው የሙዚቃ ሥራዎች ከአብዛኛው ጥቂቱን ልገልፅላችሁ፡፡
“ከፋኝ” (ትዝታ) የተሰኘ ሙዚቃ ሐሳብ የግጥም ውህደቱ ለዚህ ዓለም ጉዞ በሰውኛ አገላለፅ ሌላው መንገድ ሰውኛ እውነትን ሆኖ እዉነትነትን ሳይስት ይናገራል፡፡ በመከፋት፣ በህመም መደራረብ ውስጥ ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች አሉ፡፡ አብረን የኖርነው መልክ እያየነው ሲጠወልግ ዛሬ ላይ ያሉ ትናንትናዋን ያላወቁ ሰዎች በመልኳ ሲሳለቁ እሱ ግን ቆም ብሎ ‹‹ትናንት አውቃታለሁ፣ ለዚህ እንኳን ገላጋይ ዳኛ አያስፈልግም፣ እኔ ምስክር ነኝ! በምንም በሁሉም የትማርክ ነበረች፣ ጊዜ ጥሏት እንጂ›› ይላል፡፡ ግጥም ጥላሁን ሰማው፣ ዜማ አበበ ብርሀኔ፣ ቅንብር ታምሩ አማረ(ቶሚ)
‹‹የማለዳው ለምለም- ውበቷ ቄጤማው፣
ጠውልጎ አየሁ ዛሬ – ሲፈርድ እድሜ ዳኛው፣
አወይ ዘመን – ባዳ አቤት ጊዜ ክፉ፣
ለምልክት እንኳን – አንድ አለ ማትረፉ››…
‹‹(እቴ)›› (ሞደርን ፎክ) ባሕል ዘመናዊ የተሰኘው ሙዚቃ ቅንብሩ የዘጠናዎቹ/ሰባዎቹ ሙዚቃ ቅርፅ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ የሙዚቃ ቅንብሮቹ በምክንያት የተሰሩ፣ የማስተዋል የድምፅ እርከን ስፋት በሚገባው የድምፅ ጉልበት የተጠቀመበት ድንቅ ሙዚቃ ፤ ፅዱ ማንነት ገለጣ፡፡ ዜማ ምሕረት አብ ደስታ፣ ግጥም ናትናኤል ግርማቸው፣ ቅንብር ሚካኤል ኃይሉ (ሚኪ ጃኖ)፡፡
‹‹የቆንጆ ፍቅር – እና – ትንታ ያለበት፣
ሞት ቅርቡ ነው – እና – ውሀ አታርቁበት፣
ችዬው ልኑር እንጂ – ስራበው ወይ ስጠማሽ፣
መቼም ሰው አይድንም – ከሐመልማሎ ገላሽ››
‹‹ጉብልዬ (ቅኝት)›› የነፀብራቅ ድምፅ የሙዚቃ ጉልበቱ የታየበት የመጀመርያ ቅኝትን መቆጣጠር ፣ ሁለተኛው እየተቀባበሉ መዝፈን ፈተናው እና የውበት ፍሰቱን በመግለፅ ብዙ ነገሩ ስኬታማ አጫዋች ሆኖ ያየንበት ነው፡፡ ሐሳቡ ትዝታን ወደ ኋላ እየቃኘ ስለ አንድ ሰው እሱ በሌለበት ወዳጆቹ ሲነጋገሩ ሲጨዋወቱ፡፡ ግጥም ናትናኤል ግርማቸው፣ ዜማ የህዝብ እና ማስተዋል፣ ቅንብር ሚካኤል ኃይሉ፡፡
‹‹አጋርሽ መሆኑን ሰምቼ ፣ ያ የጥንት ወዳጅሽ ወዳጄ፣
እቴ ሙች ግራ ነው የገባኝ ፣ ሕይወት እንቆቅልሽ ሆኖ ባይ፣
እስኪ ግለጪልኝ ይሄን ነገር ፣ ያ ሰው የዛን ጊዜ ምንሽ ነበር››
‹‹እመጣለሁ›› የፍቅር ትርጉም አንዱ አገላለፅ ይህንን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ የግጥሙ ሐሳብ የምትወደው ሰው ሕመምን መዋዋስ ሳይሆን ሕመምን ብቻህን መጋፈጥ፣ ለምትጋፈጥበት ሰው ደስታውን ሁሉ መመልከት ምክንያቱም ፍቅር በስቃይ ይጣፋልና… ግጥም እና ዜማ አብዲ፣ ቅንብር ሚካኤል ኃይሉ፡፡
‹‹ከጀርባሽም ብሆንም – እንደ ዓይንሽ ልይልሽ፣
እንቅፋት ሲያይብኝ – እኔ እንድመታልሽ››
—-
‹‹እኔ አንቺን – ስለምወድ ስለምወድ፣
እመጣለሁ ሂጂ እና – በአንቺ መንገድ››
እነዚህ እና የመሳሰሉት ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎች ሰጥቶናል፡፡ ነፍስ እንዲዘራ ደግሞ የሙዚቃ ከያኒያን በዚህ ልክ አጥብቀው ሙዚቃ የሚፈልገውን ስሜት ሰተውታል፡፡ በቅንብር ብሩክ አፈወርቅ፣ ሚካኤል ኃይሉ(ሚኪ ጃኖ)፣ ታምሩ አማረ(ቶሚ) በግጥምና ዜማ ናትናኤል ግርማቸው፣ ፍሬዘር አበበ ወርቅ፣ ማስተዋል እያዩ፣ አብዲ፣ ጥላሁን ሰማሁ፣ ታመነ መኮንን፣ ብሬ ብራይት፣ እሱባለሁ ይታየሁ(የሺ)፣ አበበ ብርሀኔ፣ ቢኒያምር አህመድ፣ አንባቸው እሸቱ፣ ምሕረት አብ ደስታ፣ ማስተሪንግ ሰለሞን ኃይለማርያምና የመሳሰሉት ሰርተውታል፡፡
በዚህ አልበም ላይ እጃችሁን ያሳረፋችሁትን ሁሉ በግሌ ላመሠግናችሁ እወዳለሁ፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 የካቲት 29 2017 ዓ.ም