ሸህ ዑመር ገነቴ!!!

Date:

እንዲህ ወደ ደገር…
እንዲህ ወደ ገታ…
ደግሞም ወደ ዳና፤ጫሌ ገንደጎራ፤የተሰየማችሁ፤
ሰው መሆን…..
ሰው መውደድ፤የሚለውን ኪታብ፤ ውሉን የቀራችሁ፤
በሸዋ ከተማ፤ያገር ዋርካ ሲወድቅ ከቶ ምን አላችሁ???

የቦረናው አሊም የገነቴው ማርዳ፤
የደጋጎቹ ልጅ ፤የወሎ አይነ ኩሌ፤ቁመናው ዠርጋዳ፤
ፈትፍቶ ሚያጎርሰው ፤ኢልም እንደ ፍሪዳ፤
የተሽሞነሞነው፤ከታች በሃድራው ቤት፤ከላይ በዋሪዳ፤
አማናውን ሳይሸጥ…
ኪታቡን ሳይዘውር….
መንገዱ አማረለት፤ደግሞ እንደነ ጫሌ፤ ደግሞ እንደ ሸህ ኦዳ።

ወሎን ያህል አገር…
ቦረናን ያህል ቤት…
በመሻኢክ ኪታብ፤ አገርና ማጀት ሰርቶ እየሰጣችሁ፤
ከደባትይ ቀዬ…
እስከ ደገሮች ቤት ..
ሰው መሆን የሚሉት ፤የሰውነት ቂርአት እያስነበባችሁ፤
ምነው ጀማው ሁሉ ….
ቀለሙን ሳትይዙት፤ቀልብ እንደነካው ሰው፤ ተወጀበጀባችሁ???

ደረቅ ስብከትማ …
የቃላት ድርደራ፤ ነጫጭ ጥምጣም ጋር፤ ምልቷል በደጃችን፤
ሃጃ አልወጣ አለ እንጅ፤ አልተስማማ ሆኖ፤አፍ እና ቀልባችን።

በተውሶ ፊደል …
በወለድ አግድ ስንቅ…
እንኳንስ የሰማይ የምድሪቱም ህይወት ቁመናው ላይቀና፤
የአባቶቹን መንገድ…
ንቆ ያፈረሰው …..
ውራውሬው ሁሉ፤መሀል መንገዱ ላይ፤ቀረ በጅማሬ፤ቀረ በጉተና።

አፍ በረከሰበት ፤ፊደል ባረጠበት፤በዚህ ዱልዱም ዓለም፤
ሰውነት በራቀው…
በፀረ ሰብ ምላስ፤ኪታብ ቢዘረጋ፤መድረክ ቢሸላለም፤
የተነገረ እንጅ…
የተሰበከ እንጅ፤በግብር የፀና ፤ አንድም ህይወት የለም።

ከህይወት የሚፈልቅ …
ብእርና አንደበት…
ስብከትና ዳእዋ፤ በተጧሃረ ቀልብ፤ ትውልዱን ሲያበጃጅ፤
በዘመናት መሃል ….
በርግጥም ሰምተናል….
የሰው መሆን ኪታብ፤ በሰውነት ሚዛን፤ይችን ምድር ሲዋጅ፤
የጋለውን እሳት…
ቃንቄ ወላፈኑን…
ሲያበርደው አይተናል፤ የነ ሙፍቲ አንደበት፤ የነ ዑመር አዋጅ።

አዳ ምን ዋጋ አለው…
በጨለማው ወራት በተደናገረው፤
በቀኝ ጀምሮ በግራ በሚያድረው፤
በመውደድ ጀምሮ፤በጥላቻ መደድ በሚደመድመው፤
እሰጣለሁ ብሎ፤ነጥቆ በሚጥለው፤
በዚህ ክፉ ጊዜ…
ዘመኑን አኩርፎ…
ዙልሙን ተፀይፎ፤ደጋግ ሰው ሲሄድ፤ ውስጡን ቅር እንዳለው፤
አትጠራጠሩ፤ማለዳው ውሽንፍር፤ቀኑ ጨለማ ነው።

በወሎዎች ዘንዳ…
በወሊዮቹ ቤት ፤ይኸው ዛሬም ድረስ፤እየተነገረ አለ ኪታባችን፤
የኢቅራችን ፊደል…
ሰው ነው መጀመሪያው ሰው ነው ማክተሚያችን።

ይኸ ገልቱ ዘመን…
እብቅና ፍሬው፤ስንዴና ገበሎው እየተዛነቀ፤
በየሰርጣ ሰርጡ፤እምባጮ ዋርካ ላይ እየተደለቀ፤
ዙልም አላይም ብሎ፤የዛውያው ሰንደቅ፤ምስለኔው ወደቀ።

የዘረኝነት ጉጥ…
የሃይማኖት ጠገግ፤የአድልዎ ክፉ ደዌ፤ ነግሶበት በአገሩ፤
ውሸት ጌጥ ተደርጎ….
ከድሃው ጭጎት ስር፤እስከ ንጉስ እልፍኝ በመስተናበሩ፤
ይኸው በዚህ ሰሞን…
የሃበሻ አሊሞች….
ዱንያን ተጠይፈው ፤ሞትን አቅፈው ሳሙት፤ለሃቂቃ አደሩ።

እኒያ ደጋጎቹ…
በየበረሃው ላይ…
በደረሳነት ሃቅ ፤አንጀታቸው ታስሮ በረሃብ ተወግሮ፤
ነበር ንየታቸው፤ከዱንያ ድግስ ጋር፤የተጣላ ኑሮ።
እነርሱ ተርበው..
ዛውያው እንዲቆም፤ኪታቡ እንዲፀና ነበር ምኞታቸው፤
እየተናነሱ ጀሊሉን ማተለቅ ነበር ንየታቸው፤
እየተሰደዱ …
እየተወገሩ ፤ጀማውን መካደም፤ነበር መንገዳቸው፤
ሰውን እየሰሩ፤ሰውን ማንገስ ነበር ነገረ ስራቸው፤
ጫሌ ገንደጎራ..
ቃሉ ጀማ ንጉስ፤ዑመር ዑመር ይላል፤ ዛሬም ኪታባቸው።

አባትነት ማለት…
ለሃገር የተሰጠ …
ለወገን ለዘመድ ፤ለመንገደኛ ሰው ለባዳ ድንገቴ፤
መሆኑን ነገረን ….
መሆኑን አስረዳን…
የደገሮቹ ልጅ፤የገታው ባለሟል፣ ሸህ ዑመር ገነቴ።

እንዲህ ወደ ራያ…
እንዲህ ወደ የጁ፤ደግሞ ወደ ቃሉ ደወይ ረህመቶ፤
ይኸ የጦቢያ ሰው…
ታሞ ከረመ አሉ ፤አሽረው እያለ፤ ዑመር ጋር ተኝቶ።

እሱ የቀደረው፤የወሰነው ነገር አይታለፍ ቀኑ፣
ምን ሰውን ቢወዱት፤ ከሞት አያስጥሉት፤ካለቀ ዘመኑ፤
ግን ደግሞ ግን ደግሞ…
ከኛ ጋር ይኖራል ፤የሙፍቲ ዑመር ቃል ነገረ ኪዳኑ፤
ዛሬም እንላለን፤ ሰዎች ሆይ ሰው ሁኑ!!!

ጃኖ መንግስቱ ዘገየ (ከዳና መንደራ እስከ ጫሌ ገንደጎራ ድረስ በዱኣ ያደገው)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጽሟል፡፡ በሥርዓተ...

የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አስክሬን ሽኝት በሚሊንዬም አዳራሽ ተካሂዷል

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ታየ አጽቀስላሴ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት...

እንኳን ሰው ሰማዩም አለቀሰላቸው

በተለምዶ ጥቅምት ወር ብረድ እንጂ እምብዛም ዝናብ አይታይበትም። ይኸውና...