ሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬ እና ሶለል

Date:

አንዳንድ ባህሎች በራሳቸው  ልዩ የሆነ ገጽታን ፈጥረው የሚታዩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ትርጓሜን አጣምረው ሲይዙ ይስተዋላሉ፡፡ የሻደይ አሻንዳ ሶለልና የአሸንድዬ  በዓላት የአከባበር ሥርአት ቀደምት የሆነ ሀይማኖታዊ መሰረት እንዳለው በሀይማኖት አባቶች ዘንድ በሰፊው ይገለጻል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዓላቱ ከሐይማኖታዊ ከዓልነቱ ባለፈ በክረምት ወራት የሚከበር የልምላሜና የመልካም ምኞት መግለጫ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

የባህል አጥኝዎች እንደሚገልጹት ከሆነም በዓሉ ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ የክረምቱን መውጣትና የበጋውን ወቅት መግባትን ምክንያት በማድረግ እንዲሁም ልጃገረዶች አዲሱን ዓመት በተስፋና በሀሴት ለመቀበል በብሩህ ተስፋ ውስጥ ሆነው የሚያከብሩት በዓል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜዎችን የያዘ ሲሆን በዋግህምራ “ሻደይ” ፣ በቆቦ “ሶለል” ፣ በላሊበላ “አሸንድዬ” ፣ በአክሱምና አካባቢው “አይነዋሪ” በአብዛኛዎች የትግራይ አካባቢዎች “አሸንዳ” የሚል ስያሜዎች ይሰጣቸዋል። ከልጃገረዶቹ አለባበስና ጸጉር አሰራር ውጭ በሁሉም አካባቢዎች ለበዓሉ የሚሰጠው ትርጉዋሜና የአከባበር ሥርዓቱ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡

የሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል መከባበርን ይቅርታ መጠያየቅንና አብሮ የመኖር ተስፋ የሚሰነቅበት በዓላት ናቸው፡፡

የበዓሉ ዝግጅት የሚጀምረው ከነሀሴ 1 ጀምሮ ነው፡፡ በልጀገረዶቹ መሀል የተጣላ ካለ እርቅ ይወርዳል ፡፡ ሴቶችን የምትመራዋ አለቃና የግጥምና የዜማ አውጪዋ የምትመረጠውም በዚያው ሰሞን ነው፡፡

አንድ ቡድን ከ12 እስከ 20 የሚደርሱ አባላትን በውስጡ ይይዛል። የባህላዊው ጨዋታ ተሳታፊዎች በየእድሜ እርከናቸው የሚሰባሰቡ ሲሆን ሕጻናት፣ ልጃገረዶች እንዲሁም እናቶች ከበዓሉ አስቀድመው ለጨዋታው ራሳቸውን በቡድን በቡድን ያደራጃሉ። የጨዋታው ዋንኛ ባለቤቶች ግን ያላገቡ ሴቶች ወይንም ልጃገረዶች ናቸው።

አንዱ የሴቶች ቡድን ከሌላው ተሽሎ ለመታያት ከበዓሉ አስቀድሞ ባሉት ቀናት ውስጥ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ የውይይቱ ፍሬ ነገር በአብዛኛው የሹሩባ አሰራራቸውን፣ የጆሮና የአንገት ጌጦቻቸውን፣ አልባሳቶቻቸው ምን መምሰል እንዳለበት የሚወስኑበት ዕለት ነው፡፡

ነሐሴ ወር በገባ በ15 ኛው ቀን ልጃገረዶች ወደ በርሃ ወርደው የሻደይ ቅጠልን የሚሰበስቡበት ቀን ነው፡፡ ቅጠሉ የሚሰበሰበው ገደላማ ከሆነ ስፈራ ላይ ነው፡፡ ልጃገረዶቹ አውሬ እንዳይተናኮላቸው ወይንም ሌሎች ጉዳቶች እንዳይድርስባቸው በሚል የአካባቢው ጎረምሳዎች ይጠብቁዋቸዋል፡፡

በ ነሐሴ 15 ምሽት ልጃገረዶች የሰበሰቡትን የሻደይ ቅጠል ሲጎነጉኑ ያመሻሉ ምናልባት እንኳን እንዴት እንደሚጎነጎን ካልቻሉ እናቶቻቸው ወይንም እህቶቻቸው እንዲሰሩ ያደርጋሉ፡፡

ነሀሴ 16 የበዓሉ አከባበር በይፋ የሚጀምርበት ዕለት ነው፡፡ ልጃገረዶች እርስ በእርስ ተጣራርተው ይሰባሰባሉ፡፡ በበዓሉ ሰሞን ስራ የምትታዘዝ ልጅ የለችም። ምክንያቱም እነዚህ ቀናት በይፋ ነጻነቱዋን የምታውጅበት ነው፡፡

በዕለቱም ሁሉም ልጃገረዶች ተጠራርተው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ደብር በማምራት ፈጣሪ በሰላም ለበዓሉ ስላደረሳቸው ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ከዚህች ቀን በሁዋላ ባሉት ተከታታይ 5 ቀናትም ልጃገረዶቹ ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ጨዋታቸውን ያቀርባሉ ፡፡

የሻደይ፣ አሸንዳ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓላት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይም በአማራና ትግራይ ክልሎች ከነሐሴ 16 – 21 ቀን ድረስ በልዩ ሀይማኖታዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች ታጅቦት ይከበራል ።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያን ከ500 በላይ ላመጡ ተማሪዎች ማበረታቻና እውቅና ተሰጠ

በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ500 በላይ...

በኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ

በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ...

ትራምፕ ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በንግድ እና ወሳኝ ማዕድናት ላይ ንግግር አደረጉ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ እለት የጃፓን የመጀመሪያዋ...

ኢንፊኒክስ ኢትዮጵያ እና ተግባረ-ዕድ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

በትራንስሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማ ባለቤትነት የተያዘው ኢንፊኒክስ እና የአዲስ አበባ...