የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ ኪዬቭ የአፍሪካ አገራት በዩክሬን ግጭት ዙሪያ በያዙት አቋም የተነሳ ልትብል እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡
ዩክሬን የአሸባሪነት ባህሪዋን በድጋሚ አረጋግጣለች ሲሉ ማሪያ ዛካሮቫ መናገራቸውን የዘገበው ስፑትኒክ ነው፡፡
“የኪዬቭ አገዛዝ ታጣቂዎችን በማሠልጠንና የኔቶ ሀገራት ለዩክሬን የሚያቀርቡትን መሳሪያ በማስታጠቅ ጥቃቶች እንዲፈጽሙ እገዛ ያደርጋል፤ ይህ ሁሉ በአውሮፓ ኅብረት የሚሸፈን ነው” ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት አንስተዋል።
የኪዬቭ አገዛዝ ደጋፊዎች የአፍሪካን አህጉር ከሩሲያ ጋር ወደ ግጭት ለመሳብ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ይመስላል ሲሉም ቃል አቀባይዋ ገልጸዋል።
“የኪዬቭ ባለሥልጣናት በዩክሬን ዙሪያ ባለው ሁኔታ በያዙት ተጨባጭ አቋም የተነሳ አፍሪካውያንን እየተበቀሉ እንደሆነ በግልጽ ይታያል” ብለዋል።
ሩሲያ በበኩሏ፤ ለአፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ አጋር በመሆን፤ ያለፖለቲካዊ ጣልቃገብነትና ድርብ መስፈርት ለአኅጉሪቱ ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ዛካሮቫ ማስታወቃቸውን ስፑትኒክ ዘግቧል፡፡
